የዋሊያዎቹ ትጥቅ አቅራቢ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ትጥቆችን ለአጭር ጊዜ በገባው ውል መሠረት ሲያቀርብ የቆየው ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቆች አምራች ጎፈሬ እንደነበር ይታወቃል። ጎፈሬ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተዋውሎ የነበረው ለኮትዲቯሩ የአፍሪካ ዋንጫ ለተወሰኑት ጨዋታዎች በትጥቅ ለመደገፍ ነበር።

ከጎፈሬ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ የዋናውን ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ የሚያቀርብ ዓለም አቀፍ ተቋም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ለዓለም ዋንጫ ለሚያደርገው የማጣሪያ ውድድር ትጥቅ ለማቅረብ ከዋናው ትጥቅ አምራች ጋር ስምምነት ተፈጽሟል።

የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን፤ የእግር ኳስ ስፖርትን የማልማት፣ የማሳደግና የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በሁሉም የእድሜ እርከኖች ያሉ ብሔራዊ ቡድኖችን በማዋቀር ለእግር ኳስ ልማቱ እየሠራ ይገኛል። ብሔራዊ ቡድኖቹ በአሕጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ ለማድረግ የሚደረገው ጥረትም ይጠቀሳል። ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ጨምሮ በተለያዩ የእድሜ እርከኖቹ የወንድና ሴት ቡድኖች የመጫወቻና ሌሎች ትጥቆችን ለማቅረብ ከተለያዩ ሀገርና ዓለም አቀፍ የትጥቅ አምራቾች ጋር ሲሠራም ቆይቷል።

ዋልያዎቹ ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ባለፉበት ወቅት ከጣሊያኑ ትጥቅ አምራች ‹‹ኤሪያ›› ጋር ሠርቷል። ከኤሪያ ጋር የነበረው ውል ሲጠናቀቅ ‹‹አምብሮ›› ከተባለ የደቡብ አፍሪካ የትጥቅ አምራችና አቅራቢ ድርጅት ጋር በተገባ ውል ትጥቆቹን ለብሔራዊ ቡድኑ ሲያቀርብ ቆይቶ ፌዴሬሽኑ ከእሱም ጋር ውሉን ሳያድስ ወደ ሀገር በቀል የትጥቅ አምራቾች ፊቱን በማዞር ስምምነቶችን ፈጽሞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከወራት በፊት በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ተካሂዶ በተጠናቀቀው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረጉ ጥቂት የማጣሪያ ጨዋታዎች ትጥቆችን ለማቅረብ ከሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ጎፈሬ ጋር በተገባው ውል መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያና የወዳጅነት ጨዋታዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ሙሉ የመለማመጃ፣ የጨዋታ ማልያን ጨምሮ በርካታ ትጥቆችንም ማቅረብ ችሏል። የትጥቅ አቅርቦቱ ዋናውን የሴትና የወንድ ብሔራዊ ቡድኖችን ጨምሮ የተወሰኑ የእድሜ እርከኖችን ያካተተም ነበር።

ከጎፈሬ ጋር የነበረው ውል ይታደስ ወይም ይቋረጥ ግልጽ የሆነ ነገር ባይኖርም ለዋልያዎቹ ትጥቅ የሚያቀርብ ድርጅት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ፌደሬሽኑ አስታውቋል። ዋሊያዎቹ ከፊታቸው ላሉባቸው ጨዋታዎች ከአንድ ዓለም አቀፍ የስፖርት ትጥቆች አምራች ጋር ስምምነት እንደሚፈጸምም ተጠቁማል። በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ በዘላቂነት የትጥቅ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የራሱን የስፖርት ትጥቅ ማምረቻ ለመጀመር እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አመላክቷል።

ፌዴሬሽኑ ከሰሞኑ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ላሉበት የመማሪያ ጨዋታዎች የትጥቅ አቅርቦት ከሌላኛው ሀገር በቀል አምራች ‹‹ዋናው›› ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈጽሟል። ስምምነቱን የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን እና የዋናው ስፖርት ባለቤት አቶ ሀብተሥላሴ ገብረክርስቶስ ተፈራርመዋል። ተቋሙ የ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ይፋዊ የትጥቅ አቅራቢ በመሆኑም ኩራት እንደሚሰማው ገልጿል።

የተገባው ውል ብሔራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርጎ እስኪያጠናቅቅ እንደሚቆይ የተገለጸ ሲሆን፤ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫው የሚያልፍ ከሆነ ከትጥቅ አቅርቦቱ በተጨማሪ ቡድኑ በዓለም ዋንጫው የተሻለ ተሳትፎና ውጤት እንዲኖረው የሚያደረግ ድጋፍንም ያካትታል።

በስምምነቱ መሠረት የቡድኑን መሠረታዊ እሳቤ ማዕከል ባደረገ መልኩ በጨዋታዎች ወቅት በሜዳና ከሜዳ ውጪ የሚለበሱ የተለያዩ የማልያ ዲዛይን መዘጋጀቱ ተገልጿል። በዚህም መሠረት ሙሉ የመጫወቻ ትጥቆችን፣ የማሟሟቂያ፣ የጂምናዚየምን ጨምሮ 10 የሚደርሱ የትጥቅ አይነቶች 1ነጥብ3 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ትጥቆች ይቀርባሉ። በተጨማሪም ቡድኑ እጥረቶች የሚያጋጥሙት ከሆነ ሃምሳ በመቶ ቅናሽ ተደርጎ በሽያጭ ያገኛል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ መሠረት ሀገር በቀል የስፖርት ትጥቅ አምራቾች እንዲበረታቱ ስለሚያደርግ ከመሰል ተቋማት ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ስምምነቱ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ባያልፍም የኮንትራት አፈጻጸሙ ታይቶ ለሌሎች የማጣሪያ ውድድሮች ዕድል ሊኖረው ይችላል። በእድሜ ደረጃ ቡድኖቹ የትጥቅ አቅራቢ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዋሊያዎቹ ከወራት በኋላ ለሚኖሩባቸው ጨዋታዎች ከአንድ ዓለም አቀፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች ጋር ለመሥራት በቅርቡ ስምምነት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡ ዋናው ትጥቅ አምራች የተሻለ ነገርን በመሥራት ፌዴሬሽኑ ወደ ውጪ ማማተር ያስቀራል ብሎ እንደሚያምኑ ዋና ጸሐፊው የተናገሩ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑ ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት ብዙ አማራጮችን እየፈለገ ይገኛል ብለዋል፡፡ የራሱን ትጥቅ የማምረትና መለያ መፍጠር የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱንም አመላክተዋል።

የዋናው ስፖርት ትጥቅ አምራች ባለቤት አቶ ሀብተሥላሴ ገብረክርስቶስ በበኩላቸው፣ የታዳጊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ የሚበቃ ከሆነ የአሁኑን ያህል ዋጋ ሊያወጣ የሚችል ማልያ በነፃ ለማቅረብ በውሉ መካተቱን ገልጸዋል። የዋሊያዎቹንም ትጥቅ በጥራት በመሥራት ፌዴሬሽኑ ወደ ውጪ እንዳይሄድ ለማድረግ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You