የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት አዲስ የቅመማ ቅመም የጥራት እና የግብይት መመሪያ አውጥቷል:: መመሪያው አምራቹ የቅመማ ቅመም ምርቱን ከተለመደው አመራረት በተለየ መንገድ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና በጥራት እንዲመረት ማድረግ የሚያስችል እንደሆን ያለመ ነው፤ በተጨማሪም ምርቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ተደራሽ በመሆኑ ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም መሆን እንዲችል ማድረግን ታሳቢ አርጓል::
አዲስ ከወጣው የጥራትና የግብይት መመሪያ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ ሻፊ ኡመር እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ በቅመማ ቅመም ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው:: የቅመማ ቅመም ዘርፍ ልማትና ግብይቱን በማስፋት አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አበክሮ እየሠራ ይገኛል::
ኢትዮጵያ በቅመማ ቅመም ዘርፍ ሰፊና ዕምቅ አቅም አላት:: ይህንን ዕምቅ ሃብት ለመጠቀም አንደኛ ልማቱን እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል ጥናት በማድረግ ከተለያዩ ክልሎች ጋር ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠራ ነው:: በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የቅመማ ቅመም ምርቶችን በስፋት በማልማት ወደ ገበያ ለማምጣት በሚሠራው ሥራ በተለይ አዝሞሪኖ ተጠቃሽ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሻፊ፣ በዚህ ላይ በተለይ በደቡብ ክልል በስፋት እየተሠራበት እንደሆነ ጠቁመዋል:: ከደቡብ ክልል በተጨማሪ በአማራ ክልልና በሌሎች አካባቢዎችም በስፋት እንዲመረትና ህዝቡም ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል እየተሠራ ነው ብለዋል::
ከልማቱ ባሻገር በግብይቱ በኩል ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሻፊ በአሁኑ ወቅት 34 የሚደርሱ የቅመማ ቅመም አይነቶች ወደ ውጭ ገበያ እየተላኩ እንደሆነም ይገልጻሉ:: ከ34ቱ የቅመማ ቅመም አይነቶች መካከል 16 የሚደርሱት ቅመማ ቅመሞች ወደ ውጭ ገበያ በስፋት እንደሚላኩም ተናግረዋል:: እነዚህ ቅመማ ቅመሞች ምርታቸው ብቻ ሳይሆን ግብይታቸው እንዴት መሆን አለበት የሚለውን ጥያቄ በመመለስ ምርቱ በስፋትና በጥራት ለውጭ ገበያ ተልኮ አገሪቷ ከዘርፉ ተገቢውን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሆነ አመላክተዋል::
እሳቸው እንደተናገሩት፤ የቅመማ ቅመም ዘርፉ ከዚህ ቀደም መመሪያ አልነበረውም፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቅመማ ቅመም ምርትና ግብይት ዙሪያ የሚሠራቸውን ሥራዎች በመመሪያ መደገፍ ያለበት እንደሆነ በማመን መመሪያ አዘጋጅቶ እንድጸድቅ ተደርጓል:: ከዚህ ቀደም ዘርፉ መመሪያ ያልነበረው በመሆኑ በአገሪቱ የሚመረቱ የቅመማ ቅመም ምርቶች ተሰብስበው ምርመራ ተደርጎባቸው ብቻ ወደ ውጭ ገበያ ይላኩ ነበር:: ይሁንና አሁን ተገቢ በሆነ መንገድ ምርቱም ሆነ ግብይቱ በአዋጅና በመመሪያ እንዲመራ አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናዎችን እየሰጡ ናቸው::
መመሪያው ውስጥ አዳዲስ ነገሮች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ሻፊ፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ ምርትና ምርታማነትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል የሚለው ነው፤ በተለያየ አግሮ ኢኮሎጂ የሚመረቱ ቅመማ ቅመሞች እንዴት ናቸው፤ የአመራረቱ ሁኔታ እንዴት ነው፤ የሚሉ ነጥቦችን የሚመለከት ነው::
ሁለተኛው ከተመረተ በኋላ ወደ ገበያ የሚወጣበትን መንገድ ይመለከታል:: ምርቱ ለገበያ የሚቀርበው በሁለት መንገድ ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ የአገር ውስጥ ገበያ ነው:: የአገር ውስጥ ገበያ ግብይቱ እንዴት መመራት አለበት የሚለውም በመመሪያው ተካትቷል:: ለአብነትም የአርሶ አደሩን የቅመማ ቅመም ምርት በመጀመሪያ ግብይት እንዴት ማቅረብ ይችላል፤ የቀረበውን ምርትስ እንዴት ማገበያየት ይቻላል የሚለው በሚገባ ተመላክቷል::
ሁለተኛው የውጭ ገበያ መሆኑን አቶ ሻፊ ጠቅሰዋል፤ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ምርቶች ተደራሽ ከሆኑባቸው አገራት በተጨማሪ መዳረሻዎችን እንዴት ማስፋት አለብን የሚሉት በመመሪያው ከተካተቱት መካከል ይገኝበታል ይላሉ:: በተጨማሪም ከላኪዎች፣ ከአቅራቢዎችና ከአምራች አርሶ አደሮች ምን ይጠበቃል የሚለውን እያንዳንዱ ግዴታና መብቶች የተካተቱበትና ሁሉም ነገር በህግ መታሰር የቻለበት ሁኔታ በመመሪያው ተፈጥሯል ብለዋል::
የቅመማ ቅመም ምርትና ግብይት ከዚህ ቀደም በመመሪያ የታሰረ አልነበረም ያሉት አቶ ሻፊ፤ አሁን ላይ ዘርፉ ህግና መመሪያ ተዘጋጅቶለት በመመሪያ እንዲደገፍ መደረጉ ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኝ እንደሆነ ነው ያስረዱት:: ለአብነትም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ራሱን ችሎ በራሱ የሚመረትና የራሱ የሆነ አግሮ ኢኮሎጂ የሚፈልግ አለ ሲሉም ጠቅሰው፣ በተጓዳኝ የሚመረት ቅመማ ቅመምም እንዳለም ይናገራሉ:: መመሪያው እነዚህ የቅመማ ቅመም ምርቶች በጥራት እንዲመረቱ ለማድረግ ስልጠና የመስጠትና በኤክስቴሽን በኩል የመደገፍ ሥራዎችን መሥራት ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል::
ምርቱን በጥራት ማምረት ከተቻለ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆኑን አቶ ሻፊ ጠቅሰው፣ ይህ ሲሆን ከዘርፉ ተገቢውን ውጤት ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል:: ለዚህ ተግባር መመሪያው እንደሚያግዝ ገልጸው፣ የመመሪያው ውጤትም በቀጣይ ዓመታት እንደሚታይ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል::
እንደ አቶ ሻፊ ማብራሪያ፤ መመሪያው መውጣቱ ብቻ በቂ አይደለም፤ እያንዳንዱ ባለሙያ ስለመመሪያው ግንዛቤ እንዲያገኝ መደረግ አለበት:: ለዚህም ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጀምሮ ስልጠና እየተሰጠ ነው:: ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ጭምር ስለመመሪያው ምንነትና ምን ምን ጉዳዮችን አካቷል የሚለውን በተመለከተ ግንዛቤ ተሰጥቷል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘም በቀጣይ ወደ እያንዳንዱ ክልል በመውረድ ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሰራል:: በተለይም በዝግጅት ምዕራፉ በትኩረት ተሰርቶ ወደ ተግባር የሚገባ ይሆናል::
አዲስ የወጣውና እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን የተነገረለት መመሪያው የምርት ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ የግብይት ስርዓቱንም ሊያሳልጥና ዘመናዊ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን አቶ ሻፊ ይናገራሉ:: በተለይ የዘርፉ ተዋናዮች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲከበር አንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ውጤታማ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ብለዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ መመሪያው ከዚህ ቀደም በዘፈቀደ ሲመረቱ የነበሩ የቅመማ ቅመም ምርቶችን ሙሉ አቅምን አውጥቶ መጠቀም እንዲቻል ያስችላል:: በተለይም አግሮ ኢኮሎጂ ወይም የሚመረቱበት ቦታ ላይ እንዲስፋፉ የማድረግ ሥራዎችን በመሥራት ኢትዮጵያ ከቡና ብቻ ሳይሆን ከቅመማ ቅመም ምርትም የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ በማድረግ የአገሪቱንና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይረዳል::
ከመመሪያው በተጨማሪም መመሪያውን ሊደግፍ የሚችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ሻፊ ጠቁመው፤ አዋጁ በቀጣይ ዓመት እንደሚጸድቅ ተናግረዋል::
በቅመማ ቅመም ምርት ዙሪያ ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን ያነሱት አቶ ሻፊ፤ በየተለያየ ጊዜ ኤግዚቢሽኖችን የማዘጋጀትና የማስተዋወቅ ሥራ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ጭምር መሠራቱን ይጠቅሳሉ:: በቀጣይም ይህንኑ የማስተዋወቁን ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል በቡና ላይ የተደረገውን ሪፎርም በቅመማ ቅመም ዘርፍ በማምጣት አገሪቷና አምራቹ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ይፈጠራል ነው ያሉት::
ኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ምርት በብዙ ሄክታር መሬት ላይ ይመረታል፤ የሚገኘው ምርትም በተመሳሳይ ብዙ ነው ሲሉ የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ ምርቱን በአገር ውስጥ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥርም ሰፊ እንደሆነ ጠቁመዋል:: ወደ ውጭ ሲላክ ደግሞ በግብርና በኩል ጥራቱ እየታየ የሚላክ እንደሚላክ ጠቅሰው፣ ይሁንና አጠቃላይ የቅመማ ቅመም ምርት ጥራቱን መመርመር እንዲቻል ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል:: ይህም በጀት እንደሚፈልግ ተናግረው፣ በጀቱ ሲገኝ የቅመማ ቅመም ምርቱ ስፋት ባለው መንገድ ተመርምሮ ለውጭ ገበያ የሚላክበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ለአብነትም ቅመማ ቅመሞች የአዘገጃጀት ችግር ሲገጥማቸው የአፍላቶክሲን ችግር ይፈጠራል:: ይህ ደግሞ ገበያ ላይ ችግር ያመጣል:: መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ምርመራው ብቻ በቂ አይደለም፤ ምርቱ ሲመረት ጀምሮ እንዴት መመረት አለበት በሚለው ላይ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው:: ለዚህም ምርቱ እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት ለአርሶ አደሩ የአግሮፕሮሰሲንግ ስልጠና ለመስጠት ማንዋል ተዘጋጅቶ ወደ አርሶ አደሩ ተልኳል::
ከዚህ በተጨማሪም የቡና፣ የሻይና የቅመማ ቅመም አመራረትን በተመለከተ ከውጭ ድርጅት ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሩ የሶስት ወር ስልጠና እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት:: ስልጠናው እያንዳንዱ አርሶ አደር ዘንድ ተደራሽ መሆን እንዲችልም የተለያዩ አማራጮች መፈጠራቸውን ጠቅሰው፣ ለአብነትም በአካል ወርዶ በማሰልጠንና በአፕሊኬሽን ተደራሽ በማድረግ አርሶ አደሩ ተመልክቶ መማር የሚችልበት ሁኔታማ ተፈጥሯል ብለዋል::
ይህም የቅመማ ቅመም ምርቶች በጥራትና በብዛት እንዲመረቱና በገበያው ተወዳደሪ እንዲሆኑና የተሻለ ዋጋ እንዲያስገኙ ያስችላል ሲሉ አቶ ሻፊ አስታውቀዋል:: በተለይም በአሁኑ ወቅት የቅመማ ቅመም ምርት በስፋት እየተመረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በስፋት የተመረተውን ምርት ሊቆጣጠር እንዲቻልና ምርመራውም በተሻለ ጥራት እንዲከናወን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር እየተመከረበት መሆኑን ገልጸዋል::
የቡናና ሻይ ባለስልጣን በቡና ምርት ላይ ያደረገውን ሪፎርም በቅመማ ቅመም ምርትም ተግባራዊ በማድረግ እንደ ቡና ሁሉ የቅመማ ቅመም ምርቱ ውጤታማ መሆን እንዲችል በመመሪያ መደገፉ አዋጭና የሚበረታታ ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ምርት በውጭ ገበያ በስፋት ተደራሽ መሆን መቻሉንም ይጠቅሳሉ::
እሳቸው አንዳሉት፤ ምርቱ በአሁኑ ወቅት ምርቱ ወደ 43 አገራት እየተላከ ይገኛል:: በአብዛኛው ወደ ኤዥያ አገሮች የሚላክ ሲሆን፤ ለአብነትም ህንድ፣ ሳውዳረቢያ፤ ኬኒያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ባንግላዲሽ፣ እስራኤል፣ አሜሪካ ጅቡቲ ይጠቀሳሉ:: የቅመማ ቅመም ምርቶቹ ለውጭ ገበያ በሁለት መንገድ ነው የሚላኩት:: በጥሬውና እሴት ተጨምሮበት:: በስፋት በጥሬው የሚላክ ቢሆንም፣ በከፊል እሴት ተጨምሮበት የሚላክም አለ:: ለምሳሌ እርድ ታጥቦና በመጠኑ ተሰባብሮና ደርቆ ይላካል::
የቅመማ ቅመም ምርት በአብዛኛው በጥሬው ወደ ውጭ ገበያ የሚላክ ሲሆን፤ ነገር ግን እሴት ተጨምሮ የሚላክ ቢሆን የተሻለ ዋጋ እንደሚያስገኝ ይታወቃል:: ለዚህም እንዴት መሰራት እንዳለበት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ታች ካለው አርሶ አደር ጋር እየሠራ ይገኛል::
እሳቸው እንዳሉት፤ አንዳንድ አልሚ ባለሀብቶች ምርቱን ፕሮሰስ ማድረግ የሚችሉበትን ማሽን አስገብተው እየሠሩ ናቸው:: ይህንን ትኩረት አድርጎ ለመስራትም በዋናነት መመሪያው ይደግፋል::
የገበያ ፍላጎትን በተመለከተም በጥሬው፣ እሴት የተጨመረበትና በከፊል እሴት የተጨመረበት የቅመማ ቅመም ምርት በገበያው እንደሚፈለግ ያነሱት አቶ ሻፊ፤ አንዳንድ አገራት በከፊል እሴት የተጨመረበትን ምርት ከሌሎች ቅመማ ቅመሞች ጋር በማዋሃድ የሚፈልጉትን አይነት ውጤት በማምጣት እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል:: በመሆኑም ገበያው በሁለቱም መንገድ ይፈለጋል ብለዋል::
በአጠቃላይ አዲሱ የግብይትና የጥራት መመሪያ በአገሪቱ ያለውን እምቅ የቅመማ ቅመም ሃብት ማውጣትና አሟጦ መጠቀም የሚያስችል ነው:: ይህም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና በጥራት እንደሚረትም ያስችላል ያሉት አቶ ሻፊ፤ መመሪያው በአገሪቱ ካለው የቅመማ ቅመም ሃብት በተጨማሪ አግሮ ኢኮሎጂው የሚፈልጋቸውን አካባቢዎችና ምርቶች እነማናቸው የሚለውን ለይቶ ማወቅ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል::
ሌላው የግንዛቤ ፈጠራን በማሳደግ አርሶ አደሩ ምርቱን በስፋት ማምረት እንዲችል እንደሚያደርገውም አስታውቀዋል:: በስፋት የሚመረቱትን ምርቶችም በጥራት እንዲመረቱ በማድረግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ገልጸዋል:: በብዛትና በጥራት የተመረቱት ምርቶች የእሴት ሰንሰለታቸውን ጠብቀው እንዴት ወደ ውጭ ገበያ ይላካሉ የሚለውን ጭምር የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ መመሪያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውና በእጅጉ የሚደግፍ ነው ብለዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም