
ባሌ ሮቤ- ባለፉት ስምንት ወራት በባሌ ዞን የሚገኙ የቱሪዝም ሥፍራዎችን ከጎበኙ ከ34 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ከ84 ሚሊዮን በላይ ገቢ ማግኘቱን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ገለፀ፡፡ ዞኑ የሰላም እና የልማት አምባሳደር መሆኑን አመለከተ።
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ወ/ሮ ህንዲያ ሁሴን በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ፤ የባሌ ዞን በየዓመቱ ብዙ ጎብኚ የሚያስተናግድ የድንቅ ተፈጥሯዊ ሥፍራዎች እና የድንቅ ባህሎች መገኛ ነው፡፡ በተለይም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሀገሪቱ ቀዳሚ ከሆኑት የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች አንዱ ነው፡፡
የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ ወደ ዞኑ የሚጓዙ ቱሪስቶች በእጥፍ ጨምሯል ያሉት ኃላፊዋ፤ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከ31 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ3,400 በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ዞኑን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
ዞኑን ከጎበኙ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከ71 ሚሊዮን በላይ እና ከውጭ ቱሪስቶች ደግሞ ከ13.3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ያሉት ወ/ሮ ህንዲያ፤ ዞኑ በስምንት ወራት ውስጥ ከ84.3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የቱሪስት ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መነቃቃት መታየቱን ጠቁመዋል ፤የግል ባለሀብቶች በባሌ ሮቤ ከተማ እና በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ አዳዲስ ሎጆች፣ መዝናኛ ማዕከላት እና የእንግዳ ማረፊያዎችን እየገነቡ መሆኑን አመልክተዋል።
የዞኑ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት ለቱሪስት መዳረሻ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ያሉት ወ/ሮ ህንዲያ፤ በሰላም በኩልም አስተማማኝ ዋስትና ያለው ሰላም የሰፈነበት እና ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
‹‹ምንም እንኳን ባሌ ብሔራዊ ፓርክ የቱሪስት መዳረሻ መሆን ከጀመረ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም በመሠረተ ልማት በኩል አካባቢው ወደ ኋላ የቀረ ነበር›› የሚሉት ኃላፊዋ በተለይ ፓርኩ በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ ግን ሰፋፊ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹ባሌ ዞን የሰላም እና የልማት አምባሳደር ሆኗል›› የሚሉት ኃላፊዋ፤ የውስጥና የውጭ ጎብኚዎች በተለይ የግብርና ልማትን እና ቀልብ ሳቢ የሆኑ ብርቅዬ ዕፅዋትን እና እንስሳትን የያዙ ድንቅ ተፈጥሯዊ ቦታዎችን በመጎብኘት መንፈሳቸውን አድሰው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የባሌ ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገረመው መብራቱ በበኩላቸው ፣ አሁን ላይ ባሌ ብሄራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር በእጥፍ አድጎ በአማካይ ከ37 ጎብኚ በላይ በቀን ፓርኩን ይጎበኛሉ ብለዋል፡፡
የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው የሚሉት አቶ ገረመው፤ ፓርኩን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በቀን በአማካይ ወደ 181 ለማሳደግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ፤ ዕቅድን ለማሳካትም በዋናነት የቱሪስት መዳረሻ ልማትን እና የመዝናኛ እና ማረፊያ ማዕከላት እየተሠሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም በ45ኛ የቅርስ አስተዳደር ኮሚቴ ጉባዔው የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ መስከረም 2016 ዓ.ም የዓለም ቅርስ ብሎ መመዝገቡ የሚታወስ ነው፡፡
ዳርጌ ካሕሳይ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም