“የሕዝባችንን እንግልትና ወጪ የሚቀንስ ሁለንተናዊ የለውጥ ሥራ እየሠራን ነው” – አቶ ዓለምአንተ አግደው

– አቶ ዓለምአንተ አግደው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት

የዛሬው ወቅታዊ አንግዳችን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው ናቸው:: በትምህርት ዝግጅት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሕግ፤ በተመሳሳይ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በወንጀል ፍትሕ አስተዳደርና በሰብዓዊ መብቶች ሕግ በከፍተኛ ውጤት አጠናቀዋል::

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት የባሕር ዳር ከተማ ዐቃቢ ሕግ፣ የፌዴራል ዐቃቢ ሕግ፣ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ የመጀመሪያው ዳይሬክተር ጀነራል፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም በሚኒስቴር ዴኤታ ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሕግ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል:: ከአቶ ዓለምአንተ አግደው ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል::

አዲስ ዘመን፡- ወደ ሕግ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የነበርዎ ቆይታ ምን ይመስላል?

አቶ ዓለምአንተ፡- ወደ ሕግ ሙያ የሥራ ዓለም የገባሁት በ1997 ዓ.ም. የባሕር ዳር ከተማ ዐቃቢ ሕግ በመሆን ነው:: ከዚያም በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በክልል ዐቃቢ ሕግነት ለአምስት ዓመታት አገልግያለሁ:: በዚህ ወቅት የክልሉን የፍትሐብሔር ፍትሕ አስተዳደርና የሕግ ማርቀቅ እንዲሁም ጥናትና ምርምር ዘርፎች ማሻሻያ ሥራዎችን ከመሥራት በተጨማሪ እንደገና በማደራጀት የራሴን አስተዋፅዖ አበርክቻለሁ::

ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ፍትሕ ሚኒስቴር ከክልሎች የተሻሉ ዐቃቢያነ ሕጎችን በዝውውር ሲወስድ፤ የፌዴራል ዐቃቢ ሕግ በመሆን ተሹሜያለሁ:: በፌዴራል ዐቃቢ ሕግነት በምሠራበት ጊዜ በሙያዬ እስከ ረዳት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ደረጃ ደርሼ የነበረ ሲሆን፤ ትላልቅ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮችን ስከታተል ነበር:: በኋላም የሕግ ኦዲትና ኢንስፔክሽን የሚባል የሥራ ክፍልን በዳይሬክተርነት መርቻለሁ::

በመቀጠል በዚያው ፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ የመጀመሪያው ዳይሬክተር ጀነራል በመሆን አገልግያለሁ:: ከዚያም በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ለሁለት ዓመታት አገልግያለሁ::

አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ደግሞ በሚኒስቴር ዴኤታ ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሕግ አማካሪ ሆኜ ሠርቻለሁ:: በዚህ ወቅት በሕግ ጉዳዮች ከማማከር ኃላፊነቴ በተጨማሪ በግል እና የመንግሥት አጋርነት (Public Private Partnership (PPP) የሚሠሩ ፕሮጄክተሮች ማኔጅመንት ቲም ሰብሳቢ በመሆን እሠራ ነበር:: በመጨረሻም ከሰባት ወራት በፊት አሁን ወዳለሁበት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት መጥቻለሁ::

አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የተካሄዱት እርስዎም የተሳተፉባቸው ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች እና የዳኞች ጉባዔ የተሰኙት መድረኮች ፋይዳ ምንድን ነው ?

አቶ ዓለምአንተ፡- የሕግ ተርጓሚዎች ጉባዔ የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችን እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና እና ምክትል ፕሬዚዳንቶችን የያዘ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሚመራ ነው:: መድረኩ እንደ ሀገር የዳኝነት ሥርዓቱን እንዴት ከፍ ወዳለ ደረጃ እናድርስ በሚል ሰፊ ውይይት የተደረገበት ነው:: ለተገልጋዮቻችን ፈጣን እና ፍትሐዊ ነፃ ዳኝነትን በትክክል የሚገልጹ አገልግሎቶችን እንስጥ በሚል የተካሄደ፤ በሕግ አተረጓጎም ረገድ ወደ አንድ ተመሳሳይ የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ለመድረስ የሚያግዝ እጅግ ጠቃሚ መድረክ ነበር:: እግረ መንገዱን በክልሎች መካከል እንዲሁም በፌዴራል እና በክልሎች መካከል ከፍተኛ የሆነ መደጋገፍ እንዲኖር ዕድል የሚሰጥ ነው::

እንደሚታወቀው ፍትሕ ድንበር ያለው ስላልሆነ ለዜጎቻችን ፍትሐዊ የሆነ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ተገማች አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተን አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል::

ሁለተኛው መድረክ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ተጋባዥ ሆነው የተገኙበት የፌዴራል ዳኞች ጉባዔ ነው:: በመድረኩ በዋናነት የመከረው በክልልም ሆነ በፌዴራል ፍ/ቤቶች የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች እንደገና በሰበር የሚታዩበት ሥርዓት በምን መልኩ ሊመራ ይገባል በሚለው ላይ ነው:: በአንድ በኩል በሕገ መንግሥት የተቀመጠው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በመገንባት ረገድ የዳኝነት አካሉ ያለው ሚና በሌላ በኩል የክልል ፍ/ቤቶች በክልል ጉዳዮች ያላቸው የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን እንዴት በተጣጣመ መንገድ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል? በሚለውና እንደ ሀገር ወጥ የሆነ የሕግ አተረጓጎም እንዲኖር በሚያግዙ ጉዳዮች የመነሻ ጽሑፎች የቀረቡበት ነው:: ይህም እንደ ጅምር የሚበረታታ እና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በአማራ ክልል የፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው ?

አቶ ዓለምአንተ፡- የአማራ ክልል በፍርድ ቤት ከሚታዩት የመዛግብት የጉዳዮች ፍሰት ብዛት አንጻር በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው:: ሰፊ ጉዳዮች የሚታዩበት ክልል ከመሆኑ አኳያ አገልግሎት አሰጣጡን በአግባቡ ማሻሻል ያስፈልጋል:: እንደ ሀገር የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው:: በክልላችንም በተመሳሳይ የሦስት ዓመት የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን እቅድን እየተገበርን እንገኛለን:: አሁን ትግበራው ከተጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ሆኖታል::

በዚህ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በሀገር ደረጃና በክልላችን በተሠሩ የፍትሕ ማሻሻያ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች አሉ:: ነገር ግን አሁንም በተደረጉ ጥናቶች በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሰፊ ክፍተቶች በመኖራቸው ማኅበረሰቡ እርካታ የለውም:: ስለዚህ እነዚህን ክፍተቶች መሠረታዊ በሆነ መልኩ የሚቀይር የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቷል:: ከዚህ ውስጥ አንደኛው የሰው ኃይል ግንባታን የሚመለከት ነው:: በክልላችን ዳኞችን፣ ዓቃቢያን ሕጎችን እና መርማሪዎችን የሚያበቃ ተቋም እንደገና አደራጅተናል:: የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት በሚል የተቋቋመው ይህ ተቋም በክልሉ ውስጥ በሕግና ፍትሕ ጉዳዮች የልኅቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል፣ የዳኞች እና ዓቃቢያነ ሕግ የሙያ እና የሥነ ምግባር አቅምን እንዲገነባ ተልዕኮ ተሰጥቶት በአዲስ መልክ ሥራ ጀምሯል:: ይሄ በጣም ትልቅ እርምጃ ነው:: አዋጁ እንደገና እንዲፀድቅ የተደረገው በዚህ ዓመት ነው::

በተጨማሪም ፍርድ ቤት ላይ የተጀመሩ የትራንስፎርሜሽን ሥራዎች አሉ:: አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝድ ማድረግ አንዱ ነው:: ሌላው የዳኝነትና የፍትሕ የጋራ መድረኮች የፍትሕ ጉዳይ በአንድ ተቋም ተጀምሮ እዛው የሚቋጭ አይደለም:: እንደ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ዐቃቢ ሕግ እና ማረሚያ ቤት ያሉ ተቋማትን የሚያገናኝ ነው:: ተቋማት የየራሳቸውን ነፃነት ጠብቀው ነገር ግን ተቀናጅተው የማይሠሩ ከሆነ፤ አንድ ወይም ሁለት ተቋም በመቀየር የሚሳካ ነገር አይኖርም:: የቅንጅት አሠራሩን በደምብ ፈትሸን የነበሩ ችግሮችን ለይተን ክልሉ ላይ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ አቋቁመናል:: የፍርድ ቤት ነፃነት በጠበቀ መልኩ መመራት ስለሚገባውም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ነው:: ጽሕፈት ቤት አደራጅተን ኃላፊዎች ተመድበዋል:: ቻርተርም ተፈርሞ ወደ ሥራ ተግብቷል::

ከዚህ ቀደም በሌሎች ክልሎችም በነበረው አሠራር ቻርተር የሚፈረመው በበጎ ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነበር:: አሁን ላይ ይህን አሠራር በሚቀይር መልኩ የሕግ መሠረት ሰጥተነው የፍርድ ቤት ማጠናከሪያ አዋጅ በዚህ ዓመት አውጥተናል:: አዋጁ ከያዛቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ የሕግ እውቅና እንዲኖረው የተደረገበት ነው:: በዚህም እያንዳንዱ አባል ተቋም ፍርድ ቤት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ እና ማረሚያ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሠሩ፤ አፈፃፀማቸውን እየገመገሙ እና ውጤታቸውን እየለኩ የሚሄዱበትን እግረ መንገድም ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የሕግ ማሕቀፍ ተግባራዊ ተደርጓል:: አሠራሩ ለሌሎች ክልሎችም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነገር ነው::

አዲስ ዘመን፡- ቴክኖሎጂን በመጠቀም አሠራሮችን በማዘመን ረገድ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ዓለምአንተ፡– የክልሉ መንግሥት ካለው ውስን በጀት ላይ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ፍርድ ቤቶችን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየሠራ ነው:: የዲጂታላይዜሽን ሥራው በቀጣይ ሁለት እና ሦስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል:: ፕሮጀክቱን እየሠራን ያለነው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ነው:: ተገልጋዮች ወጪያቸውን እና ጊዜያቸውን በሚቆጥብ መልኩ ባሉበት አካባቢ ሆነው ክርክር እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው:: በተጨማሪም ባሉበት አካባቢ ሆነው መዝገብ ማስከፈት የሚችሉበትና ክርክሩ ወደሚካሄድበት ቦታ የማይሄዱበትን ሁኔታን የሚፈጥር ነው:: የለሙት መተግበሪያዎች በአጠቃላይ የክልሉ ዳታ ቤዝ ላይ ተጭነዋል:: የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ተጠናቋል:: ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሕንጻዎቻችንን ለዲጂታላይዜሽን በሚመች መልኩ አድሰናል፤ አዳዲስ ሕንጻዎችንም ገንብተናል::

ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ የሕዝባችን እንግልትና ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል:: የሥራ አካባቢ ሁኔታን ምቹ ማድረግም ለፍርድ ቤት ትልቅ ትርጉም አለው:: ሌሎች ተቋማት እንደሚያደርጉት ቢሮዎችን ምቹ ማድረግና ማስዋብ ብቻ ሳይሆን ዜጎች በግልጽ ችሎት የመዳኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሚያረጋግጥ ነው:: ከዚህ በፊት አብዛኞቹ ክርክሮችን የሚመሩት በቢሮ ውስጥ ነበር:: ይህን ችግር በሚቀርፍ መልኩ ማንኛውም ሰው ገብቶ መታዘብ በሚችልበት በግልጽ ችሎት ክርክሮች እንዲመሩ ለማድረግ በዞን ደረጃ የአዳዲስ የከፍተኛ ፍርድ  ቤት ሕንጻዎች ግንባታ ተካሂዷል:: በጠቅላይ ፍርድ ቤትም የእድሳትና የማስፋፊያ ግንባታዎች እያካሄድን ሲሆን፤ አብዛኞቹ እየተጠናቀቁ ነው:: ይሄ እንደ አንድ ትልቅ ርምጃ የምንወስደው ነው::

አዲስ ዘመን፡- አዳዲስ የሕግ ማሕቀፎችን በማፅደቅ እና ነባር ሕጎችን በማሻሻል የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች አሉ?

አቶ ዓለምአንተ፡- በዚህ ግማሽ ዓመት አምስት የሕግ ማሕቀፎችን ማጠናቀቅ ችለናል፤ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ፀድቀዋል:: የዳኝነት ውጤትን ከሚጨምሩ ጉዳዮች መካከል አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን መከተል በጣም መሠረታዊ ነው:: ይሄን መነሻ በማድረግ ባለፉት ስድስት ወራት የአማራ ክልል የባህል ፍርድ ቤቶችን በሕግ አቋቁመናል:: ክልሉ ጉዳዮችን በሽምግልና የሚፈታበት ከፍተኛ የሆነና የዳበረ ባህልና እሴት አለው:: ባህሉን በጠበቀ መልኩ በየአካባቢው ያሉ የሽምግልና ሥርዓቶች በአግባቡ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ርምጃ ተወስዷል:: አሁን ላይ ዐቢይ እና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ተቋቁመው የትግበራ ዝግጅት እየተደረገ ነው:: በክልሉ መንግሥት ጭምር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለ ትልቅ ሥራ ነው::

በፍርድ ቤቶቻችን የፍርድ ቤት መር አስማሚነት የሚባል ከንግድና ኢንቨስትመንት የሚመነጩ ክርክሮችን በፍርድ ቤቶች ከመቅረባቸው በፊት በስምምነት የሚታዩበትን ሥርዓት ዘርግተናል:: ለዚህም የተመደቡ ዳኞችን የማብቃት ሥራ እየተሠራ ይገኛል:: ሌላው አጋር አካላትን፣ ባለድርሻዎችን እና ማኅበረሰቡን በዳኝነት ሥርዓት ውስጥ በደምብ ማሳተፍ ላይ ትኩረት አድርገናል::

በወንጀል ጉዳይ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ፍትሕ እንዳይዛባ መንግሥት ተከላካይ ጠበቆች የማቆም ኃላፊነት አለበት:: ይሄን የሚመለከት የሥራ ክፍል ፍርድ ቤት ውስጥ አለ:: ነገር ግን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጪ አካል ስለሆነ ሌላ የሚከራከር አካል በአደረጃጀት እዛው ተቋም ውስጥ መኖር የለበትም:: ስንወክልም አቅም የሌላቸውን በትክክል እየለየን ዜጎቻችን ስለሆኑ ለይስሙላ ሳይሆን በአግባቡ ሳይከራከሩ ቀርተው ፍትሕ እንዳይዛባ፤ አዲስ የተከላካይ ጠበቆች ማቋቋሚያ አዋጅ አርቅቀን ጨርሰናል:: ግብዓቶች እየሰበሰብን ነው:: በዚህ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ለጉባኤ የሚቀርብ ይሆናል::

በዚህ በጀት ዓመት ከፀደቁ አዋጆች አንዱ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል የዳኞችን ያለመከሰስ መብት ይመለከታል:: በሕገመንግስቱ የዳኝነት ነፃነት ተረጋግጧል:: ፍርድ ቤቶች ነፃ የዳኝነት አካላት ሆነው ተቋቁመዋል:: ስለዚህ ነፃነታቸውን ማስጠበቅ ስለሚያስፈልግ የክልሉ ምክር ቤት በአግባቡ ጉዳዩን አይቶ ያቀረብነውን ሕግ አፅድቋል::

አሁን ላይ በጣም የተለወጡ አሠራሮች አሉ:: ለምሳሌ ሰበር ላይ የሚቀርቡ ጉዳዮች አጣሪ ችሎት ላይ ሲቀርቡ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን ለማየት እስከ ስድስትና ሰባት ወር ይቀጠር ነበር:: ይህን አሠራር ቀይረን አሁን በእኛ ፍርድ ቤቶች መዝገቡ በቀረበበት ቀን ሰበር ያስቀርባል አያስቀርብም የሚለው ጉዳይ በዕለቱ እንዲወሰን አድርገናል:: ለውሳኔ የተቀጠሩ መዝገቦችም በአብዛኛው መዝገብ አልተመረመረም እየተባለ ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ይሰጥባቸው የነበረውን አሠራር መቅረፍ ችለናል:: አሁን ለውሳኔ መዝገብ የቀጠሩ ዳኞች በቀጠሩበት ቀን ውሳኔውን ወስነው መምጣት አለባቸው:: ጉዳዩን ለመወሰን የማያስችል አሳማኝ የሆኑ ሲመረምሩ የሚያጋጥሟቸው ማየት፣ ማጣራት እና ማስረጃ መጠየቅ የሚፈልጉ ጉዳይ ካልገጠማቸው በቀር እንደ በፊቱ ጉዳዩ አልተመረመረም እየተባለ የሚሰጥ ቀጠሮ የለም:: ይህ በጣም ትልቅ እመርታ ነው::

ዳኞቻችን በጣም ተነሳሽነት ይታይባቸዋል:: ምንም የተለየ ነገር ተደርጎላቸው አይደለም:: ነገር ግን ምቹ የሥራ ከባቢ ተፈጥሮላቸው ነፃ ሆነው እንዲሠሩ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ስለሆነ ብቻ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በአማራ ክልል የዳኞች እስር እንደነበር ስንሰማ ቆይተናል:: የዳኞች ያለመከሰስ መብት አዋጅ በመፅደቁ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል?

አቶ ዓለምአንተ፡– አልፎ አልፎ ክልሉ ላይ በአንዳንድ አስፈጻሚ አካላት ይታዩ በነበሩ ጣልቃ ገብነቶች ከዳኞች እስር ጋር የሚያያዙ ችግሮች ይገጥሙ ነበር:: አሁን ላይ ከዳኞች እስር ጋር የተያያዘ ችግር የለብንም:: እንደ ሀገርም አብዛኞቹ ክልሎች ሕጉ አላቸው:: በቅርቡ በተካሄደው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤ ላይ ስንገመግም እንዳየነው የዳኞችን ያለመከሰስ መብት ያላፀደቁት ሁለት ክልሎች ብቻ ናቸው::

ጉባኤው ባወጣው የአቋም መግለጫም ለዳኞች ያለመከሰስ መብት እውቅና ያልሰጡ ከልሎች እውቅና እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል:: እኛ ክልል ላይ በዋናነት የነበረው ችግር ተቀርፏል:: ብዛት ያላቸው ዳኞችም ሾመናል:: ካለው የፍትሕ ፍላጎት አንጻር ቶሎ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ አሁንም ሥልጠና እየሰጠን እንገኛለን::

አዲስ ዘመን፡- እንደ ክልል ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት ተሳትፎ ታደርጋላችሁ ?

አቶ ዓለምአንተ፡- አሁን ባለንበት ዘመን ወንጀል የመከላከል ኃላፊነት ከፖሊስ እና ዓቃቢ ሕግ ጋር ብቻ የሚያያዝ ነው ብሎ ማሰብ ባህላዊ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል:: ፍርድ ቤትን ጨምሮ ወንጀል መከላከል የማይመለከተው አካል የለም:: ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች በአግባቡ ተመርምረው ትክክለኛ ውሳኔ ከተሰጠና ወንጀል የፈጸመ ሰው ተገቢውን ቅጣት ከተቀጣ ራሱ ግለሰቡ ይማራል እንዲሁም የእሱን መቀጣት ያዩ ሰዎች ከወንጀል ይታቀባሉ:: ይህ በራሱ በፍ/ቤት የሚደረግ ወንጀል መከላከል ተግባር ነው:: በክልላችን ፍርድ ቤቶች በዚህ መረዳት ውስጥ ሆነው የወንጀል ጉዳዮችን በአግባቡ ለማየት ጥረት ያደርጋሉ::

በተጨማሪም በዳኝነትና የፍትሕ አካላት የጋራ ትብብር ጥምረት ውስጥ ቁልፍ አጀንዳ አድርገን የያዝነው የወንጀል መከላከል ጉዳይን ነው:: መጀመሪያ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት ካለው መከላከል ጀምሮ ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ ተገቢውን ቅጣት በመስጠት ወንጀልን ለመቀነስ እየሠራን ነው:: በፌዴራል ደረጃ የወንጀል መከላከል እስትራቴጂ አለ:: በክልላችንም ተመሳሳይ የወንጀል መከላከል እስትራቴጂ መውጣት አለበት ተብሎ እየተሠራ ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን አጠቃላይ የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በፖሊስና በሌሎች ተቋማት ከፍተኛ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው::

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ውስጥ ያለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጫና አሳድሯል?

አቶ ዓለምአንተ፡– ክልሉ ውስጥ ግጭት እንዳለ ይታወቃል:: አሁን እኛ እንደ ፍርድ ቤት ለማድረግ እየሞከርን ያለነው ሰዎች አለመግባባታቸውን፣ ግጭታቸውን እና ክርክራቸውን በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚያቀርቡበትን ሥርዓት ማጠናከር ነው:: ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት መኖሩን በማሳየት ኅብረተሰቡ አመኔታ እንዲያሳድር ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን:: በክልሉ ውስጥ ከተከሰተው ግጭት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ፖለቲካዊ ሊሆኑ ስለሚችሉ፤ በዚያ መንገድ የሚሰጣቸው መፍትሔ እንዳለ ሆኖ በዘላቂነት ግን ዜጎች አለመግባባቶቻቸውን ወደ ፍርድ ቤት እያመጡ መፍታት አለባቸው የሚል የጸና አቋም አለን:: ይህም ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ብቸኛ መፍትሔ ነው:: ትክክለኛውም መንገድ ይሄ ስለሆነ የሚመጡትን ጉዳዮች በትክክል ለማየት እና ጠንካራ ፍርድ ቤት ለመገንባት እየተንቀሳቀስን ነው::

በክልሉ ውስጥ የሚካሄዱ ግጭቶች በዜጎች ሰብዓዊ መብት ላይ ጫና ያሳድራሉ፤ አንዳንድ የወደሙ የዞንና የወረዳ ፍርድ ቤቶችም አሉ:: በዚህ ችግር ውስጥ ሆኖ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣው ሰው በብዙ እንግልት አልፎ ስለሚመጣ፣ በተቻለ መጠን እኛ ጋር ሲደርስ አስፈላጊ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት በፍጥነት በመስጠት ጫናውን ለመቀነስ ጥረት እያደረግን ነው::

አዲስ ዘመን፡- ክልሎች በፌዴራል ደረጃ የዳኞች ምደባ ላይ በሚኖራቸው ኮታ አንዳንድ ጊዜ የፍትሐዊነት ጥያቄዎች ሲቀርቡ ይደመጣል:: አማራ ክልል ተገቢውን ውክልና አግኝቷል?

አቶ ዓለምአንተ፡- ፍርድ ቤት ሙያዊ አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም ነው:: ባለሙያዎች በሙያዊ ብቃታቸው ተመዝነው በውድድርና በሹመት የሚይዙት ቦታ መሆን አለበት:: የፍትሕ አገልግሎትም ዓለም አቀፍ ባሕሪ ያለው ነው:: በዚህ ምክንያት በብዙ ሀገራት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ጭምር በዳኝነት ሲያገለግሉ ማየት የተለመደ ነው:: በሌላ በኩል በሀገራችን የምንከተለው የፌዴራል ሥርዓት እንደመሆኑ የጋራ በሆኑ የፌዴራል ተቋማት ሁሉም ተገቢውን ውክልና እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ስለሆነም እነዚህን ጉዳዮች ማለትም ሙያዊ አቅም፣ የዳኝነት አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ ባሕሪ እና ውክልናን አማክሎና አጣጥሞ መሄድ ያስፈልጋል:: ከዚህ አንጻር ከተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ቅሬታዎች ካሉ በአግባቡ እያዩ መፍታትና ግልጽ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል::

አዲስ ዘመን፡- እንደ አማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በፍትሕ ዘርፉ ላይ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባሉ የሚሏቸው ጉዳዮች አሉ ?

አቶ ዓለምአንተ፡- የፌዴራልም ሆነ የክልል ፍርድ ቤቶች የሚሠሩባቸው መሠረታዊና የሥነ ሥርዓት ሕጎች በአብዛኛው ተመሳሳይነት አላቸው:: ስለዚህ ፌዴራል ላይ የሚወጡ ሕጎች ጥራት የዳኝነት አካሉን ውሳኔ አሰጣጥ ይወስናሉ:: በጣም የበሰሉና ፍትሐዊ ሕጎች መውጣት ይኖርባቸዋል::

አሠራሮችን ሊያሻሽሉ የሚችሉ አንዳንድ ሕጎች በተለይ የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱን ሊቀይሩ የሚችሉ እንደ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ያሉት ከ20 ዓመታት በላይ በማርቀቅ ሂደት ውስጥ አልፈዋል:: ለተወካዮች ምክር ቤት ከተላኩ በኋላ ግን እስከ አሁን በምክር ቤቱ አልፀደቁም:: በመሆኑ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ የሚያመጡ አዳዲስ ጉዳዮችን ተግባራዊ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል::

የፍትሕ ተቋማቱም እንደ ሀገር ከ60 ዓመት በላይ በወጡ ሕጎች እንዲሠሩ ተገደዋል:: ስለሆነም ለእዚህ ጉዳይ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በአፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት ወደ ሥራ መግባት አለባቸው:: የሚወጡ ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎች እንዲሁም የሕግ ማሕቀፎች ጥራት እና ጊዜውን ጠብቀው፤ መውጣት ለዳኝነትና አጠቃላይ ለፍትሕ አገልግሎት አሠጣጥ መሠረታዊ ናቸው::

በፌዴራል ጠቅላ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጡ ውሳኔዎች አስገዳጅነት ያላቸው ስለሆኑ፤ የውሳኔዎቹ ጥራት እና የተሰጡበት አግባብ በክልል ፍርድ ቤቶች ላይ የራሳቸው ተፅዕኖ ይኖራቸዋል:: የፌዴራል በሆኑ ጉዳዮች የክልል ፍርድ ቤቶች ተወክለው ይሠራሉ:: በዚህ ረገድ ከበጀት ጀምሮ ያለው መደጋገፍና መተጋገዝ በደምብ መፈተሽ አለበት::

አዲስ ዘመን፡- ጊዜ ወስደው ለጥያቄዎቻችን የተብራራ ምላሽ ስለሰጡን እናመሰግናለን!

አቶ ዓለምአንተ፡ እኔም አመሰግናለሁ!

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You