የቦስተን ማራቶን ድል የማስጠበቅ ፍጥጫ

የሰባቱ የዓለማችን ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች (ቶኪዮ፣ ለንደን፣ ሲድኒ፣ በርሊን፣ ቺካጎና ኒውዮርክ) ማራቶኖች አካል የሆነው የቦስተን ማራቶን ዛሬ ይካሄዳል።

ለ129ኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ከ32 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ። የርቀቱ የዓለማችን ከዋክብት አትሌቶች ሲፋለሙ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያንም የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል።

ከወትሮው የተለየ ፉክክር በሚጠበቅበት ውድድር በ42 ኪሎ ሜትር ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻሉ በርካታ አትሌቶች እንደሚሳተፉ የቦስተን አትሌቲክ ማህበርን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በወንዶች መካከል በሚደረገው ፉክክር ማራቶንን ከ2:09 ሰዓት በታች ያጠናቀቁ ሃያ ሁለት አትሌቶች ለአሸናፊነት ይፋለማሉ። ከነዚህ ውስጥ አስራ ሦስት ያህሉ ርቀቱን ከ2:07 በታች ያጠናቀቁ ናቸው።

በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በሚደረገው ውድድርም ርቀቱን ከ2:23 ሰዓት በታች መፈፀም የቻሉ አስራ ሰባት አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸው ተጠቁሟል። ከነዚህም መካከል አምና የውድድሩ አሸናፊ የሆኑት ኢትዮጵያዊው አትሌት ሲሳይ ለማና ኬንያዊቷ አትሌት ሔለን ኦቢሪ ይገኙበታል።

የውድድሩ ቻምፒዮን ሲሳይ ለማ አምና ተፎካካሪዎቹን በፍፁም የበላይነት ሲረታ 2:06:17 ሰዓት ነበር ያስመዘገበው። በዚያ ውድድር ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አትሌት ከባለድሉ ሲሳይ ጋር የአርባ አንድ ሰከንድ ልዩነት ነበረው። በማራቶን 2:01:48 የሆነ ፈጣን ሰዓት ያለው ሲሳይ ለማ የአምና የበላይነቱን ዘንድሮም በቦስተን ጎዳናዎች ለመድገም ወደ ውድድሩ መመለሱ ተዘግቧል። ይህ ድንቅ የማራቶን አትሌት ባለፈው 2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለመወከል ቀዳሚው ተመራጭ ቢሆንም ፓሪስ ከደረሰ በኋላ ጉዳት እንዳጋጠመው ገልፆ በተጠባባቂነት ወደ ሥፍራው ያመራው አትሌት ታምራት ቶላ እንዲወዳደር እድሉን አሳልፎ መስጠቱ ይታወሳል። በዚህም ታምራት ቶላ በኦሊምፒኩ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ በቅቷል።

ቦስተን ላይ በዋናነት የሲሳይ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ኬንያውያን አትሌቶች ናቸው። የውድድሩ የሁለት ጊዜ አሸናፊ ኢቫንስ ቺቤት አምና ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ አትሌት ሲሆን ዘንድሮም ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል። ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ጆን ኮሪር በማራቶን 2:02:44 የሆነ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ሲሆን ባለፈው ዓመት የቺካጎ ማራቶን አሸናፊም ነው። ይህም ዛሬ ቦስተን ላይ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ከባድ ሚዛን ተፋላሚዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል። የፓሪስ ኦሊምፒክ የአሜሪካውያን የማጣሪያ ውድድር ላይ ከአንድ እስከ ስድስት ባለው ደረጃ ካጠናቀቁ አትሌቶች መካከል ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻሉ አራቱ አትሌቶች በዛሬው የቦስተን ማራቶን ተፋላሚ መሆናቸውም ፉክክሩ ቀላል እንደማይሆን ፍንጭ የሰጠ ነው።

በፓሪስ ኦሊምፒክ ከወራት በፊት በማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረችው ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት ኮከብ አትሌት ሔለን ኦቢሪ ዛሬ በቦስተን ማራቶን የምትፋለመው የተለየ ታሪክ ለመፃፍ ጭምር ነው። ያለፉትን ሁለት የቦስተን ማራቶን ውድድሮች በድል የፈፀመችው ኦቢሪ ዘንድሮ ሐትሪክ ለመሥራት ተዘጋጅታለች። ይህን ማሳካት ከቻለችም እኤአ ከ1999 ወዲህ በሦስት ተከታታይ የቦስተን ማራቶን ውድድሮች ማሸነፍ የቻለች አትሌት በመሆን ደማቅ ታሪክ ለመፃፍ ትበቃለች። በቦስተን ማራቶን ከአንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ታሪክ አራት አትሌቶች ሦስት ውድድሮችን በተከታታይ የማሸነፍ ታሪክ ያላቸው ሲሆን ኦቢሪ አምስተኛዋ አትሌት የመሆን እድሉ አላት።

ከቤት ውስጥ ቻምፒዮና እስከ ዋናው አትሌቲክስ ቻምፒዮና፣ ከኦሊምፒክ እስከ ዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮናዎች በማሸነፍ ብቸኛዋ አትሌት የሆነችው ኦቢሪ ዛሬ ቦስተን ላይ ሐትሪክ ለመሥራት የሁለት ከዋክብት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ብርቱ ፉክክር በድል መወጣት ይጠበቅባታል።

የ2023 የቡዳፔስት ዓለም ቻምፒዮና የማራቶን ባለድሏ አማኔ በሪሶ የኦቢሪን የሦስታ ድል ለመግታት አቅሙ፣ ልምዱና ብቃቱ ያላት ኮከብ ናት። የ2022 የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ያለምዘርፍ የኃላውም የፉክክሩ ግንባር ቀደም የአሸናፊነት ግምት ከሚሰጣቸው አንዷ ነች።

ጠንካራዋ የማራቶን አትሌት አማኔ 2023 ላይ በዚሁ የቦስተን ማራቶን በኦቢሪ የተሸነፈችው ለጥቂት ነበር። ያንን ቁጭትም ዘንድሮ በድል ትወጣለች ተብሎ ይጠበቃል። 2022 ቫሌንሲያ ማራቶን ላይ ያስመዘገበችው 2:14:58 የሆነ የርቀቱ ፈጣን ሰዓቷም በርቀቱ የዓለማችን አምስተኛው ፈጣን ሰዓት ነው።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You