የበዓል ማግስት

የሥራ እና የንባብ ባህላችን ደካማነት ብዙ የተባለበት፣ ብዙ የተወቃቀስንበት ነው:: አሁንማ ጭራሽ ተስማምተንበት የተውነው ሁሉ ይመስላል:: ያልተጻፈ ሕግ አድርገነው እየተዳደርንበት ነው ማለት ነው:: ለምሳሌ፤ ‹‹የሐበሻ ቀጠሮ›› የሚለው አባባል እንደዋዛ መደበኛ አባባል እየሆነ ነው:: አንድ ሰው ምንም ሥራ ሳይኖረው፣ ወደተያዘው ፕሮግራም መሄድ እየቻለ ‹‹ሂድ እንጂ!›› ሲባል ‹‹የሐበሻ ቀጠሮ ቶሎ አይጀመርም!›› እያለ ይቆያል:: ተስማምተንበታል ማለት ነው::

ልክ እንደዚህ ሁሉ የተለመደ የሆነው ነገር የበዓል ማግስት የትምህርት ቤቶች እና የሥራ ተቋማት መዘጋት ነው:: እዚህ ላይ አንድ ነገር ሊባል ይችላል፤ ምናልባትም አንዳንዶች በዓሉን እንደመቃወም ሊቆጥሩት ይችላሉ:: ግልጹን እንነጋገር ከተባለ ግን ስንፍና ነው! ስንፍና መሆኑን የምታውቁት የሥራ መዘጋቱን የሚፈልጉት የእምነቱ ተከታይ ያልሆኑት ሁሉ ናቸው:: ባለፈው የሙስሊሞች የኢድ አልፈጥር በዓል ‹‹እሁድ ባልሆነ!›› እያሉ ብዙ ክርስቲያኖች በቀልድም በቁም ነገርም ሲናገሩ ነበር:: ሰኞ ቀን ከሆነ ሥራ ላለመግባት ማለት ነው:: እሁድ የታወቀ የእረፍት ቀን ስለሆነ ተደርቦ እንዳይውልና አንድ ሌላ ተጨማሪ የሥራ ቀን እረፍት እንዲሆን ተፈልጎ ማለት ነው:: ይህ የስንፍናችን ማሳያ ነው::

የፋሲካ በዓል እሁድ ነው:: እንደ ሥራው ሁኔታና ባሕሪ ፈቃድ መውሰድ ይቻላል:: በዚህም ምክንያት የዓመት እረፍታቸውን ለበዓል የሚያደርጉ አሉ:: ቤተሰብ ጋ ይሄዱበታል ማለት ነው:: እነዚህ ሰዎች ሥራቸውን አልበደሉም፤ የዓመት እረፍታቸውን ለሚፈልጉት ጊዜ አደረጉት ማለት ነው:: ከዚያ ውጭ ያሉት ግን ሰኞ የሥራ ቀን ነው፤ የሥራ ቀን ስለሆነ በቀን መቁጠሪያ መዝገብ ውስጥ እንደ እረፍት ቀን አልተቆጠረም፤ ስለዚህ ሥራ መግባት ግዴታ ይሆናል ማለት ነው::

እዚህ ላይ እንደ ማኅበረሰብ አንድ መግባባት ያለብን ነገር አለ:: ለምሳሌ፤ እኔ የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ:: የመንግሥት ሠራተኛ የአሠራር ሕግና ደንብ ይታወቃል:: ስለዚህ እኔ ጠርቸው የሚመጣ ጓደኛ ሰኞ ቀን ሥራ ስገባ ቅር የሚለው ከሆነ አይወደኝም ማለት ነው፤ መቀጣቴን ይፈልገዋል ማለት ነው:: ስለዚህ አክብሮኝ ሊመጣ የሚገባው የበዓሉ ዕለት ነው:: ሰኞ ቀን ከእሱ ጋር የምውልበት ምክንያት የለም፤ ከሆነም ማታ ከሥራ በኋላ መገናኘት ነው::

ይህ ሲባል የማኅበራዊ ሕይወት ፋይዳው ጠፍቶኝ አይደለም:: ማኅበራዊ ሕይወት አንድነትንና አብሮነትን በማጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፤ የኢትዮጵያ አኩሪ ባህል ተብሎ የሚገለጸውም በዋናነት ይህ ጠንካራ ማኅበራዊ ሕይወታችን ነው:: ጨዋታዎች፣ ፍልስፍናዎች፣ እሴቶች ከእንዲህ አይነቱ መስተጋብር የተቀዱ ናቸው:: የመረዳዳት እና የመተጋገዝ ባህላችን የዚህ ውጤት ነው:: የመተዛዘን እና የሰብዓዊነት የሞራል ዕድገት ማሳያዎች የእንዲህ አይነቱ መስተጋብር ውጤቶች ናቸው:: እነዚህ እሴቶች ራሳቸውን ችለው ሊጠኑ የሚገባቸው አኩሪ ባህሎቻችን ናቸው::

ዳሩ ግን ይህ መሆን ያለበት መደበኛውን የመንግሥት የሥራ ሰዓት በማይበድል መንገድ መሆን አለበት:: የበዓል ቀን ካላንደር ዝግ እንዲሆን የተደረገው እኮ ለዚሁ ሲባል ነው:: እንቁጣጣሽ ሰኞ ቀን ቢውል ሥራ ዝግ ይሆናል:: መስቀል ማክሰኞ ቀን ቢሆን ሥራ ዝግ ይሆናል:: ጥምቀት እሮብ ቢሆን ሥራ ዝግ ይሆናል፤ ገና ሐሙስ ቀን ቢሆን ሥራ ዝግ ይሆናል:: ኢድ አልፈጥር ወይም መውሊድ ወይም አረፋ በሥራ ቀን ቢሆን ሥራ ዝግ ይሆናል:: ዝግ የሚሆንበት ምክንያት የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ እሴት ስለሆነ ነው:: በባህላዊና ማኅበራዊ እሴቱም የአብሮነት ሚና ስላለው ነው::

ለበዓላት በዚህ ልክ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ፤ ለሥራም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: ብዙ ነገራችን ባህላዊ ስለሆነ ለዘመናዊ አሠራሮችና ሕጎች ትኩረት አንሰጥም:: ለምሳሌ፤ እንደ ግብርና እና ንግድ ባሉ በግለሰቡ መልካም ፈቃድ ብቻ በሚመሩ ሥራዎች ስለመድን አገልግሎት ለሆኑ የተቋማት ሥራዎች ብዙም ትኩረት አንሰጥም:: የሚጎዳ መስሎ አይሰማንም፤ እንደ ቀላልና ተራ ነገር እናየዋለን::

ብዙ የመንግሥት ሥራ እንደ ቀላል የሚታይበትን አመለካከት እንታዘባለን:: ማንም ሰው የግሉ ሥራ ላይ የማያደርገውን መዘናጋት፣ የመንግሥት ሥራ ላይ ሲሆን ግን ከልክ ያለፈ ግዴለሽ ይሆናል:: የቤቱን ዕቃዎች ከነፍሱ እኩል የሚሳሳላቸው ሠራተኛ፣ ቢሮ ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች ግን እንደ ትርፍ ያያቸዋል:: ቤቱን እንደ እንቁላል በጥንቃቄ የሚይዝ ሰው የቢሮውን መፀዳጃ ቤት ግን ያበላሸዋል:: ይህ የስንፍና ብቻ ሳይሆን ያለመሠልጠን ችግር ነው::

በበዓል ማግስት ሥራ አልገባም የሚል ሁሉ ጮማ እና ቁርጥ ተርፎት አይደለም፤ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ከሥራ ለመገላገል ጭምር ነው:: ይሄ ማለት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ፣ እንግዳ ያለባቸው የሉም ማለት አይደለም፤ ዳሩ ግን ሥራ ነዋ! ያም የመጣው እንግዳ ወደ ሥራው ይሂድ!

የበዓል ማግስት ወደ ሥራ ከማይገባባቸው ምክንያቶች አንዱ ድካም እና ሕመም ጭምር ነው:: ይህ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ጥፋት ነው:: ሥራ መበደሉ ሳያንስ ተጨማሪ አካላዊ ጉዳት እያስተናገደ ነው ማለት ነው:: ይህ ሰው ሥራ ቢገባም ታማሚ ስለሚሆን ተገቢውን ሥራ በተገቢው አግባብ አይሠራም:: አብዝቶ ባለመመገብ እና አብዝቶ ባለመጠጣት ጤናውን መጠበቅ የግለሰቡ መብት ነው:: መንግሥት ለምን ይህን ያህል በላ ብሎ ሊቆጣጠረው አይችልም፤ ለምን ከሥራ ገበታህ ቀረህ ብሎ ግን መቆጣጠር ይችላል:: ተገቢውን ርምጃም መውሰድ ይችላል::

መንግሥት ሲባል ያው ሕዝብ ማለት ነው:: ስለዚህ አንድ ሠራተኛ ሰበብ እየፈለገ ሲቀር የሕዝብ ሥራ እየበደለ ነው ማለት ነው::

በትምህርት ቤቶች አንድ የተለመደ የሰነፎች ሕግ አለ:: ሰነፍ ተማሪ ‹‹አስተማሪዎች ዛሬ አይገቡም›› በሚል ይቀራል:: ሰነፍ አስተማሪም ‹‹ዛሬ ተማሪዎች አይመጡም››› በሚል ይቀራል:: ሁለቱም ሰበብ ፈልገው ይቀራሉ:: መማር አለብኝ ብሎ የሚሄድ ጎበዝ ተማሪ መምህር አያገኝም ማለት ነው:: ማስተማር አለብኝ ብሎ የሚሄድ መምህርም ተማሪ አያገኝም ማለት ነው::

እነዚህ ተማሪዎች አድገው ነው ዛሬ ሥራ ይዘውም ‹‹ባለጉዳይ አይመጣም›› በሚል ከሥራ ገበታቸው ላይ የሚቀሩት:: ባለጉዳዩ ቢቀርም የራሱ ጉዳይ ነው፤ ሌላ ቀን አስፈጽመዋለሁ ብሎ ካሰበ መብቱ ነው:: የሥራ ኃላፊውና ፈፃሚው ግን መብታቸው አይደለም:: አስቸኳይ ጉዳይ ኖሮት ለሚመጣ ሰው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አለባቸው:: አለበለዚያ በሕዝብ በጀት እየቀለዱ ነው ማለት ነው::

የበዓል ማግስት ሥራ የለም የሚለውን ያልተጻፈ ሕግ እንደዋዛ መተዳደሪያ እያደረግነው ነው:: ይህ ልማድ ሊስተካከል ይገባዋል! በአንድ በኩል ኑሮ ተወደደ እያልን፣ በሌላ በኩል ሥራ እየበደልን አይሆንም!

የሥራ ባህላችን አብዮት ያስፈልገዋል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You