
አዲስ አበባ፦ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት በሁለት የሥልጠና መስኮች የፒ.ኤች.ዲ ፕሮግራም በቅርቡ ሊጀምር መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) አስታወቁ ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ጸድቋል። የቴክኒክና ሙያ ዘርፍን በስምንት ደረጃዎች ከፍሎ አስቀምጧል። በዚህም ደረጃ ስምንት ማለት “ፒ.ኤች.ዲ”፣ ደረጃ ሰባት “ማስተርስ”፣ ደረጃ ስድስት “ዲግሪ” ማለት ነው ።
ይህንን መሠረት በማድረግ ኢንስቲትዩቱ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የ “ፒ.ኤች.ዲ” ፕሮግራም ለመጀመር ከአንድ ዓመት በላይ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው ፤ የ “ፒ.ኤች.ዲ” ፕሮግራሙ በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እና በቲቪቲ ሊደርሺፕና ማኔጅመንት የሥልጠና መስኮች የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሮግራሙን ለመጀመር የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን እውቅና እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ይህም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ትምህርቱን የተመለከተ ሥርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን፤ የኢንስቲትዩቱ ቦርድም ሥርዓተ ትምህርቱን መርምሮ ማጽደቁን አመልክተዋል።
አንድ ሰው በ “ፒ.ኤች.ዲ” ለመመረቅ በትንሹ አራት ዓመት እንደሚያስፈልገው የገለጹት ብሩክ (ዶ/ር)፤ የ “ፒ.ኤች.ዲ” ፕሮግራም በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት በቅርቡ ማለትም በያዝነው ዓመት ለማስጀመር በቂ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በዚህም የሕግ ማሕቀፍ፣ የሥልጠና ቦታ፣ የአሠልጣኞችን ብቃት የመመዘን ሥራዎች ተዘጋጅተዋል። ይህን ዘርፍ የሀገርን ኢኮኖሚ በተገቢው ልክ እንዲደግፍ ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋልም ብለዋል፡፡
ቴክኒክና ሙያ የአዕምሮና እጅ ጥበብ ውጤቶች የሚፈልቁበት ዘርፍ ነው ያሉት ብሩክ (ዶ/ር)፤ በየጊዜው እየጨመረ ለመጣው የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የሰው ኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሥልጠና ዘርፉን ማጠናከር የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ለቴክኒክና ሙያ የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ ከቀጠለና የአመለካከት ለውጡ ላይም የበለጠ ከተሠራ ዘርፉ በሀገር እድገት ላይ መጫወት የሚገባውን ሚና በሚገባ የመወጣት እድል እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም