
የፋሽን ኢንደስትሪ በዓለም ላይ ትልቅ ኢኮኖሚ ይንቀሳቀስበታል። በዚህም ከዘርፉ ተዋናይ አልፎ እንደ ሀገርም ያለው ጥቅም ቀላል አይደለም። ፋሽን ለሚከተሉ ግለሰቦችም የራሱ ጥቅም እንዳለው ይታወቃል።
ፋሽን መከተል ቁመና እንደሚያሳምርና በራስ የመተማመን ስሜት እንደሚያዳብር ምንም ጥርጥር የለውም። የሚያምርብንን ልብስ መልበሳችን አንዳንድ ጉድለታችንን የሚሸፍን ከመሆኑም በላይ በውበት ላይ ውበት ሊጨምርልን ይችላል። በተጨማሪም ሌሎች ለእኛ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል።
ይሁን እንጂ የፋሽኑ ዓለም ችላ ሊባል የማይገባው ጎጂ ገጽታም አለው። ሸማቾች አዳዲስ ልብስ በመግዛት ማለቂያ የሌለው አዙሪት ወይም ሱስ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። የፋሽኑ ኢንዱስትሪ አዳዲስ ስታይሎችን ማውጣት እንደማያቆም የታወቀ ነው። ምክንያቱም ፋሽኖች ጊዜያቸው ቶሎ ባለፈ መጠን ፋሽን አውጪዎችና ልብስ ነጋዴዎች የሚያጋብሱት ትርፍ የዚያኑ ያህል ይበልጥ ይጨምራል። ፋሽን አውጪ የሆኑ ባለሙያዎች “አንድ ፋሽን የሚወጣው እንዴት እንደሚያልፍበትም ታስቦበት ነው” በማለት ይናገራሉ። ስለዚህ ጥንቁቅ ያልሆነ ሸማች ከጊዜው ጋር እኩል ለመራመድ ሲል ብቻ አዳዲስ ልብሶችን መግዛት እንደሚኖርበት ይሰማዋል።
በተጨማሪም ማስታወቂያዎች ለሚያሳድሩት ጫና የመሸነፍ አደጋም አለ። የፋሽን ኩባንያዎች ብዙውን ጊዜ ልብሶቻቸውን በመልበስ ደስታ እንዳገኙ ለሚያሳዩ ማስታወቂያዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያጠፋሉ። እነዚህ መልዕክቶች ጠንካራ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ። በስፔይን የሚኖር አንድ መምህር “ለወጣቶች በወቅቱ ተወዳጅ የሆነውን ጫማ ለማድረግ አለመቻልን ያህል ቅስማቸውን የሚሰብር ነገር የለም” ብለዋል።
አንዳንድ ቡድኖች አንድን ዓይነት አለባበስ የሚመርጡት ማንነታቸውን ለማሳየት ነው። የሚለብሱት ልብስ የማኅበረሰቡ ተቃዋሚዎች፣ ልቅ የሆነ አኗኗር የሚከተሉ፣ ሌላው ቀርቶ ዓመፀኞች ወይም ዘረኞች መሆናቸውን ሊያመለክት ይችላል። ከእነዚህ አለባበሶች አንዳንዶቹ በጣም ቅጥ ያጡ ወይም የሚያስጠሉ ቢሆኑም እርስ በርስ ለመመሳሰል ሲሉ የቡድኑ አባሎች በሙሉ ይለብሱታል። የቡድኑን አስተሳሰብ የማይከተሉ እንኳን በአለባበሳቸው ሊማረኩ ይችላሉ። እነዚህ በቡድኑ አለባበስ የተማረኩ ሰዎች የቡድኑ አባል ባይሆኑም እንኳን መሠረታዊ እምነቶቻቸውን እንደሚከተሉ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ።
ፋሽኖች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከጥቂት ወራት ያለፈ ዕድሜ አይኖራቸውም። ጀማሪው አንድ የታወቀ ሙዚቀኛ ወይም ሌላ ታዋቂ ሰው ሊሆን ይችላል። ጥቂት ፋሽኖች ግን ዘላቂ ሆነው ይቀራሉ። ለምሳሌ ያህል ሰማያዊ ጂንስ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ዓመታት ማኅበረሰቡን የሚቃወሙ ወጣቶች የሚያዘወትሩት ልብስ ነበር። አሁን ግን በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች በተለያየ ወቅት የሚለብሱት ልብስ ሆኗል።
ለፋሽን ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ስለ መልካቸውና ስለ ቁመናቸው ከሚገባው በላይ መጨነቅ ሊጀምሩ ይችላሉ። የፋሽን አስተዋዋቂዎች አብዛኛውን ጊዜ ለግላጎችና ቀጭኖች ሲሆኑ ቁመናቸውንና መልካቸውን በያለንበት እንድናይ እንደረጋለን። “ትክክለኛ” እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው ቁመና ከመኪና እስከ ከረሜላ የሚደርሱ የተለያዩ ሸቀጦችን ለማሻሻጥ ይውላል። የብሪታንያ የማኅበራዊ ጉዳዮች ምርምር ማዕከል “በአሁኑ ጊዜ ወጣት ሴቶች በአንድ ቀን ውስጥ የሚያዩአቸው ቆነጃጅት ቁጥር እናቶቻችን በወጣትነት ዕድሜያቸው በሙሉ ካዩአቸው ይበልጣል” ይላል።
ይህ ዓይነቱ የማስታወቂያ ውርጅብኝ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ በኒውስዊክ መጽሔት ላይ የሠፈረ አንድ ጥናት ከነጭ ወጣቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በመልካቸውና በቁመናቸው እንደማይደሰቱ አመልክቷል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ መልካቸውንና ቁመናቸውን ለማስተካከል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ሆኖም የማኅበራዊ ጉዳዮች ምርምር ማዕከሉ እንደገለጸው ከጠቅላላዎቹ ሴቶች መካከል በመገናኛ ብዙኃን የሚወደሰው የክብደትና የቁመት መጠን ላይ የሚደርሱት 5 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ለቀጫጭን ሴቶች ከፍተኛ አድናቆት መሰጠቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ለሥነ ልቦና ችግር ዳርጓቸዋል። አንዳንዶቹ ለመክሳት በሚያደርጉት ጥረት አኖሬክሲያ የተባለ የአመጋገብ ሥርዓት ቀውስ ገጥሟቸዋል። የአመጋገብ ሥርዓት መቃወስ የገጠማት ኒአቨዝ አልቫረዝ የተባለች አንዲት ስፔይናዊት የፋሽን አስተዋዋቂ “መወፈር ከሞት ይልቅ ያስፈራኛል” ትላለች።
እርግጥ እንደ አኖሬክሲያ እና ቡሊሚያ የመሰሉት የአመጋገብ ሥርዓት መቃወስ በሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ሊመጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የሕክምና ባለሙያዎች “በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለዚህ ምክንያቱ ቅጥነትን ማምለክ ነው” ይላሉ።
ፋሽን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ገጽታ እንዳለው ግልጽ ነው። መሠረታዊ የሆነውን አምሮ የመታየትንና አዲስ ልብስ የመልበስን ሰብዓዊ ፍላጎት ያሟላል። ይሁን እንጂ ቅጥ ያጡ ፋሽኖችን መከተል መጥፎ ስም ሊያሰጠን ይችላል። ለመልካችንና ለቁመናችን ከመጠን በላይ የምንጨነቅ ከሆነ ማንነታችን በውስጣዊ ባሕርያችን ሳይሆን በውጪያዊ ገጽታችን ላይ የተመካ ነው ብለን እንደምናምን ሊያስመስልብን ይችላል። ለዚህም ነው የሥነ ልቦና ባለሙያዎች “ለአንድ ሰው ውጪያዊ መልክና ቁመና ሳይሆን ለችሎታውና ለውስጣዊ ማንነቱ የበለጠ ዋጋ መስጠት ይኖርብናል” የሚሉት። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የአመለካከት ለውጥ በቅርብ ጊዜ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ ለፋሽን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ግድ ይላል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም