
ዲጂታላይዜሽን ቴክኖሎጂ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው:: በተለይ የሁሉም ዘርፍ መሠረት ለሆነው ትምህርት ጉልህ አበርክቶ አለው:: በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ እንደ ሀገር በኦንላይን የሚሰጡ ሦስት ትላልቅ ፈተናዎች ከመኖራቸው አንፃር አስተዋፅዖው በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: በከፍተኛ ደረጃ ለወረቀት የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንዲሁም የፈተና ስርቆትን ይቀንሳል:: እንዲሁም ከፈተና ደኅንነት ጋር ተያይዞ በዚህ በኩል ተጠቃሚ የሆኑና ወደ ሥርዓቱ ቀድመው የገቡ በርካታ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተሞክሮ መጥቀስ ይቻላል:: ለትምህርት ሚኒስቴር በላክነው ሪፖርት እንዳየነው አክሱም ዩኒቨርስቲ በዚህ በጀት ዓመት የሁለተኛ ግማሽ ዓመት ሦስተኛ ትምህርት አጋማሽ ፈተናን ብቻ በኦንላይን በመስጠቱ ከወረቀት ግዥ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ማዳን ችሏል::
በአጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ተወስኖ የተገባበትን ተግባር ያለ ቴክኖሎጂ በጭራሽ ለስኬት ማብቃት እንደማይቻል ብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል:: ኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽንን እውን ለማድረግ ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘውም ይሄን ታሳቢ በማድረግ መሆኑ አንዱ ነው::
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርቱን ዘርፍ ለማዘመን የሚሰጣቸውን ፈተናዎች ሁሉ ዲጂታላይዜሽን ለማድረግ ሲሠራ የቆየበት ሁኔታ መኖሩን በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር ) ይናገራሉ::
ኤባ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲው ዋና ተልዕኮ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምቹ ሥነ-ምኅዳር በመፍጠር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሁሉም መሠረት ለሆነው የትምህርቱ ዘርፍ እድገት ወሳኝ ሚና መጫወት ነው:: የትምህርት ሥራን ከማቀላጠፍና ከማዘመን በተጨማሪ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም ዓይነተኛ መሣሪያ ነው:: በአጠቃላይ የሁሉም መነሻ በሆነው የትምህርቱ ዘርፍ ዲጂታላይዜሽን መተግበሩ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ አካታች ብልፅግና ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ አቅም ይፈጥራል::
መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት ትምህርት ሚኒስቴር ይሄን ታሳቢ በማድረግ ፈተናዎችን በዘመነ መልኩ የሚሰጥበትን የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ለመተግበር ሲያቅድ ቆይቷል:: ወደ ትግበራ እንዲገባ ያስገደዱት በመጀመሪያ ዲግሪ የሚሰጣቸው 317 የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ናቸው:: ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የነዚህን ሁሉ ፕሮግራሞች ፈተና በወረቀት መፈተኑ በብርቱ አስጨንቆት ነበር::
“እንዴት እንፈትን እያልንም ራሳችንን ስንጠይቅ ቆይተናል” የሚሉት ኤባ (ዶ/ር) ብዙ ሲያሰላስሉ ቢቆዩም በወረቀት ይቻላል ወይ ለሚለው ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ ሊያገኙ ስላለመቻላቸውም ያስታውሳሉ:: ባለው ወረቀት መፈተን የሚችሉበት ዕድል ጠባብ መሆኑንና በምንም ተዓምር አለመቻሉን መረዳታቸውንም ይጠቅሳሉ:: በወረቀት መፈተን የማይችሉበትን ምክንያት መሪ ሥራ አስፈፃሚው ሲያስረዱም ፦ራሱ ፈተናው ብሔራዊ ፈተና ነው:: ከዚህ አንፃር ጥያቄው ብቻ እስከ መቶ ይደርሳል:: የገጽ ብዛቱም እስከ 20 ይሆናል:: እያንዳንዱን የትምህርት ዓይነት ፈተና የሚወስድ ተማሪ ቁጥርም በጣም ብዙ ነው::
የማይቻልበት ምክንያት አንድ ፈተና ራሱ ብሔራዊ ፈተና በመሆኑ እስከ መቶ ጥያቄ የሚይዝ ሲሆን እስከ 20 ገጽ ይሄዳል:: ያን የሚወስደው ተማሪ ቁጥር ደግሞ ለአብነት አካውንቲንግ ቢወሰድ እስከ 40ሺ ነው:: የፈተና ወረቀቱ በዚህ ተማሪ ልክ ሲባዛ በወረቀት መፈተን አይታሰብም:: ይሄን ሥራ ላይ ማዋልም በራሱ የሚሞከር አይደለም ይላሉ::
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው 317ቱን አካዳሚክ ፕሮግራሞች ፈተና በወረቀት መፈተን በመቻሉና ባለመቻሉ ላይ፤ በተለይም በወረቀት መፈተን በማይቻልበት ላይ የትምህርት ሊሂቃንን ሰብስቦ ብዙ ሲመክር ቆይቷል::
የማይቻልበት ምክንያት አንደኛ ብዙ ፕሮግራሞች መሆናቸው፤ ሁለተኛ ይሄን ወረቀት ራሱ ማን ነው የሚያባዛው፤ የት ነው የሚባዛው፤ ዩኒቨርሲቲ ነው የሚባዛው፤ ትምህርት ሚኒስቴር ተባዝቶ በጆንያ ልንጭነው ነው እያለም በዝርዝር ሲያይ፤ ሲመክርና ሲለይ ከርሟል::
“በስተመጨረሻም ይሄ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አይታሰብም፤ አናደርገውምም:: በመሆኑም የምንሰጠውን ፈተና ዲጂታላይዝ ማድረግ አለብን በሚል እልህ ወደዚሁ ገባን” ሲሉም ተቋማቸው የሄደበትን ርቀት ያስታውሳሉ::
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት ወደ ትግበራው ከመግባቱ በፊት ልምድ የቀሰሙበት ሂደት ነበር:: አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ልምድ ከቀሰመባቸው ተቋማት ውስጥ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ:: ልምዱን ከተቋማቱ ለመቅሰም ያነሳሳው ምክንያት ደግሞ ተቋማቱ ቀደም ብለው ወደ ዲጂታላይዜሽን በመግባት ከ8 ሺህ እስከ 11 ሺህ ለሚደርስ ተማሪ የመግቢያ ፈተና መስጠታቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም የመግቢያ ፈተና ለመስጠት ዲጂታላይዝ ሲስተሙን እንዴት ተጠቀማችሁ፤ ምን ዓይነት ሲስተም ነበር የተጠቀማችሁት ብሎ መጠየቅ ትምህርት ሚኒስቴርን ግድ ብሎታል::
እነዚህን ጥያቄዎች መነሻ ያደረገው ትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄውን ወደ ውይይት እያሰፋ መጣ:: ዲጂታል ፈተናውን ከመጀመሩ በፊት ከሁለቱ ትምህርት ተቋማት በተጨማሪም የዲጂታል ሥርዓቱን (ሲስተሙን) የሠሩ የተለያዩ የአይሲቲ ባለሙያዎች እና የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች በመጥራት ጥልቅ ውይይት አካሄደ::
ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናውን ከመጀመሩ በፊት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችን፤ ዲጂታላይዝ ሲስተሙን የሠሩ የአይሲቲ ሰዎች፤ የአካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቶችን፤ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች አገልግሎትን፤ ከራሱም ከትምህርት ሚኒስቴር አሉ የሚባሉትን ምሑራን ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ በመጥራትም በጉዳዩ ትግበራ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርጓል፤ መክሯል::
“በዚህም ፈተናዎቻችንን ዲጂታል ለማድረግ የማያስችሉ ብዙ ተግዳሮቶች ለይተናል” ይላሉ ኤባ (ዶ/ር):: ከተግዳሮቶቹ የመጀመሪያው በየጊዜው የሚቋረጠው ኔትወርክ ጉዳይ ነው:: ሌሎች ፈተናውን ዲጂታላይዜሽን ማድረግ የማይቻልባቸውና የማይታሰብባቸው ተግዳሮቶችም ተነስተው ነበሩ:: ትምህርት ሚኒስቴር በተለይ የዲጂታል ሥርዓቱን ወደ መሬት አውርዶ ለመተግበር ዋነኛ እንቅፋት ነው ተብሎ ለተለየው ኔትወርኩ የሚሠራበትን ጉዳይ መላ እፈልጋለሁ እንጂ ፈተናውን ከዲጂታል ውጭ አልፈትንም ወደሚል ሀሳብ እና ጽኑ አቋም ያዘ::
“ከዲጂታል ውጪ ፈተናውን መፈተን የምንችልበት ሁኔታ አልነበረም” የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው ዲጂታል ትግበራውን እንዴት ማስኬድ እንደሚችል በባለሙያዎች ለማስጠናትም ከሰበሰባቸው የትምህርት ምሑራን ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ይናገራሉ::
እንዲሁም ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሯል:: አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ ወላይታ ሶዶ፤ ደብረ ብርሃን፤ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር መምህራን በኮሚቴው ከተካተቱት መካከል ይጠቀሳሉ:: መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንደሚያብራሩት ትምህርት ሚኒስቴር እንዳሰበው ጥናቱንም አስጠና፤ ኮሚቴም አዋቀረ:: ሥርዓቱን ዴቨሎፕ ወደ ማድረግ (ወደማጎልበት) ሄደ:: “ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዲጂታል ፈተናው ትግበራ ስንገባ ብዙ ችግር ይገጥመናል ብለን ፈርተን ነበር” ሲሉ የሚያስታውሱት ኤባ (ዶ/ር) እንዲህም ሆኖ ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሥርዓቱ ከገባ በኋላ እያየ፤ እያጠና እና እያሻሻለም የሚሄድበት ዕድል እንደሚኖር ተስፋ አድርጎ እንደነበር ይናገራሉ::
በዚህ የዲጂታላይዜሽን ሽግግር ስኬት ሂደት መካከልም ትምህርት ሚኒስቴርን ከአዳማ እና ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች የቀሰመው ልምድ ያገዘው ስለመሆኑ ሳያነሱ አላለፉም:: ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሁለቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቀሰመው ከኔትወርክ ጋር የተያያዘ ችግርን ለመቋቋም ቴሌኮምን እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ልምድ ተጠቀመ::
“የቤት ሥራችን ይሄ ብቻ አልነበረም:: ፈተናዎቹን ዲጂታል ከማድረጋችን በፊት ምን ያህል ኢንተርኔት ኮኔክትድ የሆኑ ኮምፒውተሮች እንዳለን ዳታ መሰብሰብ ነበረብን” ይላሉ:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድ ጊዜ 33ሺ ተማሪን በኦንላይን ፈተና መፈተን የሚያስችል ኮምፒውተር ማግኘቱንም ያወሳሉ:: ትምህርት ሚኒስቴር አሠራሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዲጂታል ሲያስገባ፤ በተለይ በ2012 በኢትዮጵያ እምብዛም ያልተለመደውን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመተግበር ሲነሳ ከአራት መቶ ሺህ በላይ የመፈተኛ ታብሌት ኮምፒውተሮችን ከውጪ ሀገር ግዢ እስከመፈፀም ተጉዟል::
ያም ሆነ ይህ ፈተናውን ዲጂታል ለማድረግና የዘርፉን አሠራር ለማዘመን የትምህርት ሚኒስቴር፤ ሠራተኞች፤ አመራሮች፤ በተለይም ከተለያዩ ተቋማት በመውጣጣት ለዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ትግበራው ተዋቅሮ የነበረው ኮሚቴ 24 ሰዓት ሠርቶ ወደ ሥራ መግባት ቻለ:: መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአንድ ቀን የዘለለ ድጋፍ ሳይሰጡት ራሱን ችሎ ቆመ:: መሪ ሥራ አስፈጻሚው ኤባ (ዶ/ር) እንደሚሉት አሁን በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ የፈተና ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ወደ ዲጂታል ተሸጋግሯል::
እንደ ሀገር አቀፍ የሚሰጡ ሦስት ፈተናዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ መስጠትም ተችሏል:: እነዚህም የሪሚዲያል፤ የድህረ ምረቃ መግቢያ እንዲሁም የመውጫ ፈተናዎች ናቸው:: ትምህርት ሚኒስቴር የመውጫ ፈተናን በቴክኖሎጂ በመደገፍ በኦንላይን መስጠት የጀመረው በ2015 ዓ.ም ሰኔ ላይ ሲሆን የድህረ ምረቃውን፤ በ2016 ዓ.ም፤ ሪሚዲያልን ፈተና ደግሞ በ2016 ዓ.ም ነው:: የፈተና ሥርዓቱ ዲጂታል ከሆነ በኋላ የሪሚዲያል ፈተና (ድጋፍ ተደርጎላቸው ሁለት ሦስት ሴሚስተር ተምረው የሚወጡ ተማሪዎች የሚወስዱት) አንድ ጊዜ ሲሰጥ “የጋት” ወይም የድህረ ምረቃው ፈተና በተለይ ከተጀመረ ጀምሮ ተደጋግሞ የተሰጠበት ሁኔታ ስለመኖሩም ይገልጻሉ:: ከዚህ ልምድ በመውሰድም በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን መፈተን ተችሏል::
ሌሎችን በዚሁ ሥርዓት የሚሰጡ ፈተናዎችን ለመውሰድ የሚደረገው ምዝገባም እንዲሁ በኦንላይን ወደሚደረግ ሂደት ተሸጋግሯል:: ይሄ የራሱ የጊዜ ሰሌዳ አለው:: ሥርዓቱ በራሱ ከዚህ ጊዜ ሰሌዳ ውጭ ማስተናገድ አይችልም:: በሰባት ቀኑ ውስጥ 176 ሺ ተማሪዎችን መመዝገብ ተችሏል። በዚህ የአሠራር ሥርዓት ትምህርት ሚኒስቴር ውጤት አግኝቶበታል:: ‘ልምድ ወስደንበትና ተምረንበታል:: ኩረጃን ለመቀነስ፤ የፈተናዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ፤ ያለውን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም ለወረቀት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ የሚያስችልና ሌሎች ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች አግኝተንበታል’ ይላሉ መሪ ሥራ አስፈፃሚው:: አሁን ላይ ከፈተና አልፎ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሙሉ በሙሉ በዚህ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተደግፎ መሄድ አለበት ብሎ እየሠራ ይገኛል:: ይሄን ለመፍጠር እንዴት መደገፍ እንደሚችል ጠቋሚ የሆነ ጥናት፤ ጠንካራ የክትትል ስልት፤ ጠንካራ ፖሊሲ እንዲኖረው እየተሠራ መገኘቱን ያወሳሉ፤ በተጨማሪም የኦንላይን ዲጂታል ሥርዓት ፈተና ለመውሰድ የሚመዘገቡ ተማሪዎች በምዝገባው ማጠናቀቂያ ሰባተኛ ቀን በተጨናነቀ ሁኔታ ከመመዝገብ ይልቅ በመጀመሪያው ቀን ቢመዘገቡ መልካም መሆኑን ያስባሉ።
‘አሁን ዓለም በቴክኖሎጂ ረቃለች፤ መጥቃለች:: በያዝነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከዲጂታላይዜሽን ቴክኖሎጂ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ውጤታማ አይሆንም:: ከዚህ አንጻር ለሁሉም ሙያዎችና ዘርፎች መሠረት የሆነው የትምህርቱ ዘርፍ ከቴክኖሎጂ ጋር መራመድ ግድ ይለዋል” ያሉን ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዳይሬክተር ገብረክርስቶስ ኑርዬ (ዶ/ር) ናቸው:: እሳቸው እንደሚናገሩት፤ የትምህርቱ ዘርፍ አሠራሩን ወደ ቴክኖሎጂ በማስገባት ካዘመነ ዓመታት አስቆጥሯል:: በተለይ ፈተና በዚህ መልኩ መሰጠቱ ከፈተና ጋር ተያይዞ የሚገጥሙ የደኅንነት ችግሮች እና ኩረጃን ከመቀነስ ባሻገር ብዙ ጥቅሞች አሉት:: በተለይ እንደ ሀገር ያሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካለባቸው የየራሳቸውን ፈተና ከመስጠት፤ በተለይ በዓመቱ አጋማሽ የቀጣይ ሴሚስተር ምዝገባ ከማካሄድ፤ ትምህርት ማስተማር፤ ጥናትና ምርምር ማድረግና ሌሎች ብዙ ሥራዎች አኳያ ፋይዳው የጎላ ነው::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም