
ከሰሞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በጋራ ባዘጋጁት መርሐ-ግብር በሐረሪ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የተከናወኑ የልማት ሥራዎች በጋዜጠኞች ተጎብኝተዋል:: በሌማት ትሩፋት፣ በከተማ ግብርና፣ በተፋሰስ ልማት፣ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና በሌሎች ዘርፎችም የተከናወኑ ተግባሮችን መመልከት ተችሏል::
ጉብኝቱ በተለይ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ከተፋሰስ ልማት ጋር ተያይዞ የተከናወነው ተግባር አካባቢውን በእጅጉ የለወጠ መሆንን ያስገነዘበ ነው:: በበርካታ ቦታዎች ላይ ምንጮችና ውሃ አዘል ቦታዎች በመፈጠራቸው አርሶ አደሩ የመስኖ ሥራን እንዲያስፋፋና ምርትና ምርታማነቱን ይበልጥ እንዲያሳድግ ዕድል እንደፈጠረለት አስታውቋል::
ቀደም ሲል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ለውሃ እጥረት እና ለድርቅ ተጋላጭ መሆኑን ተከትሎ በርካታ አርሶ አደሮች ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች (ቦረና ዞን፣ ወለጋ ዞን) እንዲሰፍሩ የተደረገበት ሁኔታ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ያስታውሳሉ:: የግብርና ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በየጊዜው በሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ፤ ማኅበረሰቡ በራሱ ተነሳሽነት በተፋሰስ ልማቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ::
የተሠራው የተፋሰስ ልማት ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በበጋው ወራት በልምላሜ ፈክታ እንድትታይ አድርጓታል:: በየቦታው የሚፈልቀው ውሃ ለልማት እየዋለ መሆኑ እንዲሁም ለአካባቢው ምርትና ምርታማነት መለወጥም ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑ በጉብኝታችን ወቅት ያየነው እውነታ ነው::
አርሶ አደሩ ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ የግብርና ፓኬጆች ጥቅም ላይ የሚያውል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስትን) የመጠቀም አዲስ ልምምድም እያደረገ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል::
የዛሬው ጽሑፋችን በአካባቢው በዋናነት የተፈጥሮ ማዳበሪያን እያመረተ ጥቂት እርሾ የሚሆን ነገር ለአርሶ አደሮች በመስጠት ወደ መንደራቸው እየወሰዱ እና እያባዙ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ስለሚያደርግ አንድ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማበልፀጊያ ማዕከል የምናስቃኛችሁ ይሆናል:: የማዕከሉ ምርምሩ በችግኝ ማፍያ ጣቢያ ውስጥ የሚካሄድ በመሆኑ ስለችግኝ ጣቢያው ዋና ዋና ሥራዎችም ጥቂት ማለት ያስፈልገናል::
በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን እውን ለማድረግ እስከ 70 የሚደርሱ ችግኝ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል:: እነዚህ የችግኝ ጣቢያዎች በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በስፋት እየተካሄደ ያለውን የተፋሰስ ልማት ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር አያይዞ ለመተግበር ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የዞኑ ኃላፊዎች ይገልጻሉ::
ቢን በረድ ችግኝ ማፊያ እና የኮምፖስት ማበልፀጊያ ማዕከል ይባላል፤ የሚገኘውም በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ ነው:: ችግኝ ጣቢያው ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ለአፈር እና ውሃ ጥበቃ በሚል ከሚያፈላቸው ችግኞች ውስጥ አብዛኛዎቹ ለምግብነት የሚያገለግሉ እንደ አቦካዶ፣ ማንጎ፣ ዘይቱና፣ ቴምርና ሮማን የመሳሰሉት ናቸው::
በ2017 በጀት ዓመት እንደ ዞን በ87 ሄክታር መሬት ላይ ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታስቦ እየተሠራ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል:: እነዚህ ችግኞች በቢን በረድ ችግኝ ማፊያ ጣቢያ ውስጥ በተፈጥሮ ማዳበሪያው እየታገዙ እንዲያድጉ ይደረጋል፤ በዚህም በአንድ በኩል ችግኞችን ማፍላት፤ በሌላ በኩል የተፈጥሮ ማዳበሪያውን የውጤታማነት ደረጃ የመለካት ሥራዎች ይከናወናሉ::
በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ ግብርና ቢሮ የአፈር ማሻሻያ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶፊያን አሕመድ እንዳስረዱት፤ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የዝናብ እጥረት የሚታይበት እንደመሆኑ ድርቅ የሚያጠቃው አካባቢ ነው:: በዚህም የተነሳ አርሶ አደሩ አምርቶ መጠቀም ባለመቻሉ በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት አካባቢውን ጥሎ እስከ መሰደድ የደረሰበት ሁኔታ ነበር::
‹‹የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን እና እስከ ቀበሌ ድረስ በተዋረድ ያሉ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች በተለይም በተፋሰስ ልማት ላይ ንቅናቄ በማድረግ አርሶ አደሩን ያሳተፈ ሥራ በመሠራቱ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት የጨመረበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ርጥበታማና ረግረጋማ ቦታዎች ተፈጥረዋል፤ ምንጮችም እዚህና እዚያ መፍለቅ ጀምረዋል ››ሲሉ አብራርተዋል::
እያደገ የመጣውን የውሃ ሀብት ከመሬት ጋር አዋዶ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የተለያዩ ተጨማሪ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ አቶ ሶፊያን ጠቅሰው፣ ከነዚህም አንዱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ( ቬርሞ ኮምፖስት)ን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገው ምርምር መሆኑን ጠቅሰዋል::
በምርምር ማዕከሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ስልሳ የአፈር ማብላያ ሳጥኖች መዘጋጀታቸውን አመልክተው፣ እነዚህ ሳጥኖች ወይም ገንዳዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሜትር ኪዩብ ናቸው ይላሉ:: በደንብ ከተሞሉ እስከ 12 ቁምጣ ለብዜት የሚሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መያዝ እንደሚችሉም ተናግረው፣ የሚብላላው አፈር ወደ ማዳበሪያነት እንዲቀየርና የተፈጥሮ ይዘት እንዲኖረው የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮች እንደሚጨመርበት አስታውቀዋል:: ለአፈር ለምነት ሚና ያላቸው ትላትሎችም እንዲሁ ይካተቱበታል ብለዋል::
የሚመረተው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በቀጥታ ጥቅም ላይ እንደማይውል ጠቁመው፣ እንደ እርሾ የሚያገለግል በመሆኑ የተወሰነ መጠን እየተቆነጠረ ለአርሶ አደሩ ከተሰጠው በኋላ አርሶ አደሩ ያን በመውሰድ በሚያርሰው መሬት አካባቢ የማባዛት ሥራ እየሠራ እንደሚጠቀምበት ይገልጻሉ::
በየቀበሌው የገበሬዎች ማሠልጠኛ ጣቢያ እንዳለ የተናገሩት አቶ ሶፊያን፣ እስከ አሁንም በወረዳው ባሉ 32 ቅርንጫፍ ማሠልጠኛ ጣቢያዎች ስለ ተፈጥሮ ማዳበሪያው ግንዛቤ ተሰጥቶ አርሶ አደሩ ወደ ሥራ እየገባ እንደሚገኝ ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፣ ቴክኖሎጂውን በ39ኙም የገጠር ቀበሌዎች ማድረስ ተችሏል:: በወረዳዋ በተያዘው ዓመት 853 አባወራዎችን የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እስከ አሁን 790 የሚሆኑትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል::
ይህ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አንድ መሬት መያዝ ያለበትን ንጥረ ነገር በሙሉ አመጣጥኖ የሚይዝ በመሆኑ፣ የምርታማነትን ደረጃ የሚያሳድግ ነው:: የተፈጥሮ ማዳበሪያው እንደ አርቴፊሻል ማዳበሪያው በየዓመቱ እህል በተዘራ ቁጥር የሚደረግ ሳይሆን፣ አንድ ጊዜ ከተደረገ እስከ ሦስትና አራት ዓመት ድረስ ጥቅም መስጠት ይችላል::
የአካባቢው አርሶ አደሮች ጥቅሙን በደንብ እየተረዱ መምጣታቸው ጠቅሰው፣ በየማሳቸው ላይ በተጠናከረ መንገድ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በማስፋፋት ሥራ ላይ መጠመዳቸውን አስረድተዋል:: የግብርና ቢሮውም እንዲሁ እያንዳንዱን አርሶ አደር የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በማድረግ ማርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል::
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሜታ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አባዲር አሚኖ፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን የማስፋፋቱ ዋና ዓላማን ሲያብራሩ የአፈርን ለምነትን መጠበቅ እንደሆነ ይናገራሉ:: አርቴፊሻል ማዳበሪያ ምንም እንኳን ለምርታማነት ያለው አስተዋፅዖ ባይካድም፣ የመሬትን ንጥረ ነገሮች ይጎዳል ይላሉ:: የመሬት ለምነት እየቀነሰ ሲሄድ ደግሞ ምርታማነትም ቢዚያው ልክ እየቀነሰ ይሄዳል የሚሉት አቶ አባዲር፣ የተጎዱ መሬቶች በተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያገገሙ በማድረግ የምርታማነታቸውን ደረጃ ማሳደግ እንደሚቻል በክልል ደረጃ ሥልጠናዎች እንደተሰጡም አስታውሰዋል::
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ በሰጠው ሥልጠና መሠረት የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ቬርሞ ኮምፖስት) ወደ ማምረት እንደተገባ አስታውሰው፣ ማዳበሪያው ለተክሎች የሚያስፈልጉ እንደ ናይትሮጂን እና ኦክሲጂን ያሉ ንጥረ ነገሮችን ከማይክሮ ኦርጋኒዝም ጋር አመጣጥኖ ይዟል ይላሉ::
የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በማልማቱ ሂደትም በቅርበት የሚገኘው የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍና ትብብር እያደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ተጨባጭ ውጤት የታየባቸው ሥራዎች እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከዩኒቨርሰቲው ዓላማዎች አንዱ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዲሁም ግብርና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፤ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎች ጉዳዮችም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል:: የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የስንዴ ምርጥ ዘር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር፣ የዓሣ ዘር እና ሌሎችንም ለአካባቢው አርሶ አደሮች እንደሚያቀርብ ተናግረዋል::
በእስከ አሁኑ ሥራ በወረዳው ባሉ በእያንዳንዳቸው የገጠር ቀበሌዎች ቴክኖሎጂው ደርሶ በርካታ አርሶ አደሮች ወደ ማሳቸው ወስደው እያባዙት እንደሚገኙ አስረድተዋል:: የተፈጥሮ ማዳበሪያውን አባዝቶ የመጠቀሙ ቴክኖሎጂ በሁሉም የወረዳዋ ገጠር ቀበሌዎች መዳረሱን አስታውቀው፣ በአባወራዎች ደረጃ ግን ሁሉም ተግባራዊ እያደረጉት እንዳልሆነም ጠቁመዋል:: በቀጣይ ሁሉም አባወራ ተግባራዊ እንዲያደርገው በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል::
እንደ ሀገር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግሥት የያዛቸው መርሐ-ግብሮች በወረዳዋ በተለያዩ ሥራዎች እየተተረጎሙ መሆናቸውን የተናገሩት ወረዳ አስተዳዳሪው፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን የማዘጋጀቱ ሥራም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል አንዱ አቅም ነው ብለዋል::
የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ሸምሰዲን በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ በሜታ ወረዳ ኢፋ ቢፍቱ ቀበሌ የሚገኘው የቢን በረድ ችግኝ ማፍያ እና ኮምፖስት ማዘጋጃ ማዕከል የአፈርን ደኅንነት የሚያስጠብቅና ምርታማነትን የሚያሳድግ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ( ቬርሞ ኮምፖስት) እያዘጋጀ ለተመረጡ 20 ወረዳዎች ለ25ሺ አርሶ አደሮች ለማሰራጨት እየሠራ ነው::
‹‹መሬት ለም እንዲሆን ተፈጥሯዊ ይዘቱን መጠበቅ ይኖርበታል፤ ቢያንስ 5 በመቶ የሚሆን ማይክሮ ኦርጋኒዝም ሊኖረው ግድ ይላል›› የሚሉት አቶ ኤሊያስ፣ በጣቢያው የመሬት ለምነትን የሚያስጠብቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እየተባዛ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: ጣቢያው ከሚያመርተው ኮምፖስት ለአርሶ አደሮች እየተቆነጠረ ከተሰጣቸው በኋላ ወደ መሬታቸው ወስደው እንደ እርሾ እየተጠቀሙ እንዲያባዙት ሥልጠናዎች እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል::
የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈርን ጤንነት ለመጠበቅ፣ የአፈሩን ውሃ የማዘል አቅም ለማጎልበት እና በአፈር ውስጥ መኖር ያለባቸውን አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚረዳ አብራርተው፣ ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ አቶ ኤሊያስ አስታውቀዋል:: በአሁኑ ሰዓት የአካባቢው አርሶ አደሮች ውጤት እያገኙበት መሆናቸውን አስታውቀው፣ እርሾውን ወደ ማሳቸው በመውሰድ እያራቡት እንደሆነ ገልጸዋል:: ይህን ሥራ አስፋፍቶ በመሥራት የዞኑን የምርታማነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ በእቅድ የተያዘ ጉዳይ መሆኑን የዞኑ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ሸምሰዲን አስረድተዋል::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም