በክልሉ 52ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 75 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው

– 60 በመቶ የሚሆኑትም ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው

አዲስ አበባ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር 52ሺ ሄክታር መሬት ላይ 75 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ ከችግኙ 60 ከመቶ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን አመለከተ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ባባከር ኃሊፋ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በዚህ ዓመት በክልሉ ከ75 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 45 ሚሊዮን ችግኝ ማፍላት ተችሏል፡፡ ከችግኙ 60 በመቶ የሚሆነው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው፡፡

52ሺ ሄክታር መሬት ላይ ችግኞቹን ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 42ሺ ሄክታሩ ላይ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ቀሪው 10ሺ ሄክታር መሬት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ እስኪጀመር እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል፡፡

ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመናበብ ችግኞቹ በሚተከሉባቸው ኮሚናሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት በየዓመቱ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ችግኝ ሲተከል መቆየቱን የተናገሩት አቶ ባባከር፤ ከተተከሉት 350 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ጸድቋል፡፡

በዚህም በክልሉ ያለው የደን ሽፋን እና የዝናብ መጠን ጨምሯል፡፡ ለመብልነት መዋል የሚችሉ ፍራፍሬዎችም ለምተዋል፡፡ ሕዝቡም በዚህ ተጠቃሚ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡

ቢሮውም የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ተገቢውን ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀው ክትትል የማድረግ ሥራ እየሠራ መሆኑንም አመልክተው፤ ከተተከሉ ችግኞች ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ጠቁመዋል።

በኮሚናል የተደራጁ ወጣቶችም ችግኞቹን በመንከባከብ ሥራ ውስጥ በዋንኛነት ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አብዛኛው ችግኞች የሚፈሉት ወጣቶችን ባቀፉ ማሕበር በመሆኑም፤ ወጣቶቹ ከልማቱ የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You