የኢቢሲ ታሪካዊ የጉዞ መልክ

 የትዝታ ወግ፤

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) በሀገሪቱ የሚዲያ መስተናገጃ ሞገድ ላይ በስፋት ሲናኝበት መሰንበቱን ትንሽ ትልቁ ያውቀዋል:: ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው:: ኢቢሲ ወይንም በቀድሞ ስያሜው ኢቴቪ (ETV) በተደራጀና የዘመናዊነትን ትጥቅ በማሟላት በ58 ዓመት የጉልምስና ዘመኑ ለአዲስ ጎጆ መብቃቱን ይፋ ያደረገው በቀደም በዕለተ ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ስለ ነበር ነው:: ለተቋምም “ቤት ለእምቦሳ ይባል ከሆነ” እነሆ “ቤት ሲሰፋ ለሰው ሁሉ ተስፋ” ነውና ሠራተኞቹንና የተቋሙን መሪዎች እንኳን ደስ ያላችሁ እንላለን::

ሬዲዮና ቴሌቪዥንን አጣምሮ ያቀፈው የመንታ እናቱ ኢቢሲ “ጎጆ ወጣ” ከማለት ይልቅ “ተመነደገ! አደገ!” ማለቱ ይቀል ይመስለናል:: ኋላ ላይ ብቅ ያለው ቴሌቪዥን (ከ1957 ዓ.ም ጀምሮ) የፊተኛውን ባለ ዘጠና ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንት ሬዲዮን ቀድሞ “ሽር ጉዱና እሶሶው” ቢበዛለትም፤ የታሪክ ንጥር አድልዎ ስለማያውቅ፡-

እንደ ዛሬ ሁሉ መኪና ሳይበዛ፣

በእኔ ትከሻ ነው ሀገር የተገዛ

አለች ምስኪኗ የጋማ ከብት እንዲሉ፤ የሬዲዮ ውለታ ከቶውንም ቢሆን በዘግይቶ ደራሹ በቴሌቪዥን አንጋፋ ታሪኩ እንደማይደበዝዝ ተስፋ እናደርጋለን:: “ዘግይቶ የወጣው ቀንድ ቀድሞ የተፈጠረውን ጆሮ ዘነጋው” እንዳይሆን ለማለት ነው::

የዘመኑ ዘመናይነት ግድ ብሎ ከሆነም እንደ በኩር ልጅ ቴሌቪዥንን ብቻ “ወፌ ቆመች” እያሉ ከማኩራራት ይልቅ “የሽበት ወጉ፤ ሺህ ውበቱ” የሚባልለት ሬዲዮም በእኩልነት “ተቀራራቢ የአክብሮት ወግ” ሊነፈገው እንደማይገባ የቤተኛነት ምክር ጣል አድርገን እናልፋለን:: ስለምን? ተብሎ ከተጠየቀ ቁጥሩ ከሰማንያ ከመቶ በላይ ነው የሚል አሃዝ የሚጠቀስለት አብዛኛው ሕዝባችን ዛሬም ቢሆን በቀዳሚነት የዜናና የወሬ ምንጩ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ወይንም መሰል የኤፍ ኤም ውላጆች መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል::

ዓለም አቀፍ እውነታውስ ቢሆን የሬዲዮ አድማጮች ቁጥር እያሻቀበ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ በጥናቶች እየተረጋገጠም አይደል:: ይህንን አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ጥናት በጥቂቱ እናፍታታው:: በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚኖሩት እጅግ በርካታ የሰው ዘሮች የግል መጓጓዣ መኪና የማግኘት ፍላጎት የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን የግድ አስፈላጊ እየሆነ የመጣበት ዘመን ነው::

በተለይም በማደግ ላይ ባሉ እኛን መሰል ሀገራት የግል መኪና መኖር ለዜጎች የግዴታ ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል:: የሕዝቦች ጥያቄ እየተመለሰ የመኪና ማግኘት ጉዳይ እንደኛው ሀገር የስኬት መገለጫ መሆኑ ቀርቶ አስፈላጊ መሆኑ የሚታመንበትና ዜጎች በቀላሉ ተሽከርካሪ መግዛት የሚችሉ ከሆነ አውቶሞቢላቸውን እያሽከረከሩ የሚያደምጡት የሬዲዮ ፕሮግራሞችን እንጂ ቴሌቪዥን ልመልከት ወይንም በሆሊውድ ፊልም እየነዳሁ ልዝናና ብለው አይዳፈሩም:: ስለዚህም ነው በሥልጣኔ እየገሰገሰች ካለችው ዓለማችን ጋር የሬዲዮ አገልግሎትም እየሰፋ መሄዱ አይቀርም ተብሎ የሚታመነው::

ቴሌቪዥን ለመመልከት ረጋ ብሎና ተዝናንቶ መቀመጥን ግድ ይሏል:: የኑሮ ጫና ዕለት በዕለት እንደ መርግ እየከበደ በሚሄድባትና የማሕበራዊው ሚዲያ የውጥር በያዛት ዓለማችን ላይ የሰው ልጅ ሕይወትን ለማሸነፍ ሲከንፍ ውሎ ሲከንፍ እንዲያድር ይገደዳል እንጂ እፎይ ብሎ እንዲዘናጋ ዘመኑ አይፈቅድለትም:: የመኪናውን ሞተር እያስገሳና እየከነፈ ሲውል ደግሞ ብቸኛ አጫዋቹ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ናቸው:: ለዚህም ነው ሬዲዮ ተስፋ አለው የሚባለው::

ለማንኛውም በአስደማሚ መሻሻልና ለውጥ ወደ አዲሱ የሸጎሌ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ስለተዘዋወረው ኢቢሲ ወደ ኋላ ግድም ተመልሼ አድናቆቴን ስለምገልጽ፤ ከዚያ በፊት የኢትዮጵያ ሬዲዮን ውለታ በተመለከተ አንዳንድ ግለ ትዝታዎችን በማስታወስ መንደርደሩን መርጫለሁ::

የትዝታ ወግ አንድ፡ ይህ ዐምደኛ ከሬዲዮ ጋር የወዳጅነት ቁርኝት የፈጠረው ገና በታዳጊነት ዕድሜው ነበር:: ሰበበ ምክንያቱ ደግሞ የአንዳንድ የቀድሞ የሬዲዮ ጋዜጠኞችንና የንግድ ማስታወቂያ ተናጋሪዎችን ድምጽ በማስመሰል በየምሽቱ ቤተሰቡንና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውሪ ጓደኞቹን ያዝናና ስነበረ ነው:: ዘመኑስ? ተብሎ ከተጠየቀ ግማሽ ክፍለ ዘመን ይዘላል መልስ ይሆናል:: ቀጥሎ ከሬዲዮ አድማጭነት ወደ ተሳታፊነት ከፍ ያለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በነበረበት ዘመን ወጎችንና አጫጭር መጣጥፎችን በማስነበብ ተሳትፎ በማድረግ ነበር::

ከፍታው እየጨመረ የሄደው ግን ወደ ሥራ ዓለም በገባበት ሰሞን በተዋወቀው የማለዳ የእሁድ ፕሮግራም አማካይነት ነው:: ብዙ ጽሑፎቹ በሬዲዮ ተተርከውለታል:: እራሱም ቢሆን ከመጻሕፍት ዓለም ትረካ ሲጠናቀቅ በበርካታ መጻሕፍት ላይ ሂሳዊ ትንታኔ በመስጠትና ቴያትሮችን በመሄስ ቤትኛነቱን አጠናክሯል::

ጥቂት ማስረጃዎችን ማቅረብ ካስፈለገ እነሆ የተቆነጠሩት አብነቶች፡- በኃይለ ሥላሴ መሐሪ የተተረጎመውን “ሳቤላ” መጽሐፍ፣ በአንዳርጌ መስፍን የተደረሰውን “ጥቁር ደም” እና ሌሎች በርካታ የልቦለድና የግጥም ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና ተሰጥቶባቸዋል:: በቴያትርም ዘርፍ እንዲሁ በራስ ቴያትር መድረክ ላይ የቀረበውን “ላጤ”፣ የብሔራዊ ቴያትሩን “አንድ ጡት”፣ የማዘጋጃ ቤቱን “የሰው ሰው”፣ የሀገር ፍቅሩን “ባልቻ አባ ነፍሶ” (ዝርዝሩ ብዙ ነው) በሂሳዊ ግምገማ ለመቃኘት ተሞክሯል::

ዛሬም ድረስ በዚህ አንጋፋ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ዳግላስ ጴጥሮስ የሚጽፋቸው ጽሑፎች በብሔራዊ የሬዲዮ ጣቢያ የእሁድ ፕሮግራሞች ላይ እየተተረኩ ይገኛሉ:: በኢቲቪ ፕሮግሞችም ላይ ቢሆን ደጋግሞ በእንግድነት በመቅረብ ሃሳቡንና እወቀቱን አጋርቷል ወደፊትም ግንኙነቱ የሚቋረጥ አይመስልም::

የትዝታ ወግ ሁለት፡ ኢቢሲ ከመሃል አዲስ አበባ እምብርት በደን ወደ ተከከበበው ወደ ሸጎሌ ታሪካዊ ሠፈር “የተንቆጠቆጠ” ኮምፕሌክስ አንጾ ለመግባት ማሰቡ ሲገለጽ አንድም የቦታው ርቀት፣ አንድም “ምኞቱ ወደ ተግባር ሊለወጥ ይችል ይሆንን!?” በሚለው ስጋት የተጠራጠርነው ብዙዎች ነበርን::

ሃሳቡ ቢሳካለት እንኳን የፍጥነት እንቅስቃሴ ለሚጠይቀው የሚዲያ ሥራና ለታዳሚ እንግዶች የቦታው ርቀትና የትራፊክ ጭንቅንቁ ጉዳይ “ፈታኝ መሆኑ አይቀርም” በማለት “በቶማሳዊ ጥርጣሬ” እምነት አጥተን በየውሏችን እንዳማነው መሸሸጉ አይበጅም:: “ቃል በተግባር ተለውጦ” በማየታችን ግን አለማመናችንን ራሱን ታዝበነዋል::

የትዝታ ወግ ሦስት፡ የዚህ ዐምደኛ መኖሪያ ቤት ይገኝ የነበረው አዲሱ የኢቢሲ ኮምፕሌክስ በተገነባበት አካባቢ “በቡና አጣጭ” ርቀት ላይ ስለነበር የሠፈሩን ታሪክ በሚገባ ያውቀዋል:: ለአራት አሠርት ዓመታት ያህል ዳግላስ ጴጥሮስ እያለ የሚጠቀምበት የብዕር ስሙ ኢቢሲን የተጎራበተው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኝበትን አካባቢ ለመጥቀስ መሆኑ ተደጋግሞ መልስ ተሰጥቶበታል::

ስለዚህም ኢቢሲ በጉርብትና ቀረብ ያለው ወደ ወዳጆቹ ሰፈር መሆኑን ልብ ይሏል:: ከጸሐፊው ከዳግላስ በተጨማሪ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ላይ እጅግ አዝናኝ ጽሑፎችን በማቅረብ ይታወቅ የነበረው ሻለቃ አባይነህ አበራ፣ የዕድገት በኅብረት ዘማቾችን ስም ለንቅናቄ በመጥራትና የዘፈን ምርጫ በማዘጋጀት ስሙ ገንኖ የነበረው የአበራ ማሞ መኖሪያ የሚገኘውም ከሚዲያው ኮምፕሌክሱ ግርጌ ነው::

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእንግሊዝኛ ዜና አንባቢነቱ ስሙ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ጋዜጠኛ ልዑል ሰገድ ኩምሳ ትንሽ ፈቅ ቢልም የዚያው አካባቢ ነዋሪ ነበር:: ስለዚህ ኢቢሲ በባልደረቦቹና በወዳጆቹ ሠፈር በመክተሙ እንኳን ደህና መጣህ ብለው የሚቀበሉት አድማጭና ተመልካች ወዳጆቹና ቤትኞቹ ብዙዎች ስለሆኑ ለአካባቢው ባዕድነት ሊሰማው አይገባም::

የሼህ ጎሌ (ሸጎሌ) ስም ከተነሳ አይቀር ግን የኢቢሲ ኮምፕሌክስ የወረሰውን ግቢ ቀዳሚ ታሪክ አስታውሶ ማለፉ የግድ ይላል:: ቦታው በዘመነ ደርግ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ዴፖ የነበረበት መሆኑን ድፍን ሀገር ያውቀዋል:: ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ዕለት በጦር ማከማቻ ዴፖው ላይ የተፈጠረው አሰቃቂ የፍንዳታ ታሪክና የንጹሐን እልቂት ገና ከትዝታችን ስላልደበዘዘ ስሜቱን ላለመቀስቀስ እንዲሁ የጥቁምታ ያህል አስታውሰን እናልፋለን::

የኢቢሲ አዳዲሶቹ ሕንጻዎችና በርካታ መሠረተ ልማቶች የቆሙት በዚህ ባለታሪክ ግቢ ውስጥ ነው:: ስለዚህ ከኢቢሲ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞች ሊናኙ የሚገባቸው ዜናዎችና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ለሕዝባችን የልብ ትርታ ምላሽ የሚሰጡና ተስፋን የሚያመላክቱ እንጂ ሌላ “የስሜት ምሬት፣ ቁጣና የቅሬታ ድማሚት” የሚያፈነዱ ሊሆኑ አይገባም:: ኢቢሲ ሆይ ይህንን የቤተኛ ወዳጅ ምክር ልብ ማለቱ መልካም ይመስለናል::

ታሪክን የኋሊት

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ርምጃ የወሰዱት በነገሡ በመጀመሪያዎቹ ወራት ነበር:: በጣሉት የመሠረት ድንጋይ ላይ መልእክቱ እንዲህ ይነበባል፡- “ግርማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በነገሡ በሁለተኛው ዓመት ኢትዮጵያን ከዓለም መንግሥታት ጋር የሚያገናኝ ያለ ሽቦ ቃል የሚያስተላልፍ መኪና የሚቆምበት ቤት ሲመሠረት በሐምሌ 14 ቀን 1923 ዓ.ም የመጀመሪያውን የማዕዘን ድንጋይ አኖሩ” የጣቢያው ሥራ ተጠናቆና ተመርቆ አገልግሎቱን የጀመረው ታህሳስ 24 ቀን 1927 ዓ.ም ነበር::

በዓመቱ መስከረም 7 ቀን 1928 ዓ.ም የፋሽስት ወረራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ደመናው ከብዶ ስለነበር የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ፕሮግራሞችና ቀስቃሽ ሀገራዊ ሙዚቃዎች ለአዲስ አበባ ሕዝብ በአደባባይ ይቀርቡ ነበር:: ራሳቸው ንጉሡም በዚያው ዓመት መስከረም 13 ቀን የወረራውን አስጊነት በመግለጽ ለሕዝብ ንግግር አድርገዋል::

ንጉሡ ብቻም ሳይሆኑ ግርማዊት እቴጌ መነንም ለዓለም እናቶች በሙሉ ያስተላለፉትን የስጋት መልእክት በልጃቸው በልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተሰራጭቶ ነበር:: የልዑል አልጋ ወራሽ መልእክትም በሦስተኛነት ተላልፏል::

የተፈራው የወረራ ስጋት እውን ሆኖ ፋሽስቶች አዲስ አበባ ከመድረሳቸው አስቀድሞ የሬዲዮ ጣቢያውን እንዳይጠቀሙበት የኢትዮጵያ ጦር እንዳፈረሰው የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ:: በወረራው ወቅትም ፋሽስቶች ራሳቸው ለፕሮፓጋንዳቸው እንዲረዳቸው የሬዲዮ ጣቢያ አቋቁመው ነበር:: ኋላም በ1933 ዓ.ም ጠላት ተሸንፎ እየተባረረ በነበረበት ወቅት ያቋቋመውን የሬዲዮ ጣቢያ አፈራርሶ ለመሸሽ ተገዷል::

ከነፃነት ማግሥት በመንግሥት ትኩረት የተሰጠው ተቀዳሚ አጀንዳ የሬዲዮ ጣቢያ ማቋቋም ስለነበር የጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ በተከታታይም ጣቢያው እየተጠናከረ በመሄድ በጅማ መንገድ ጣሊያን ትቶት የሄደውን ባለ 7.5 ኪሎዋት ጉልበት ያለው የማሰራጫ መሣሪያ በመጠቀም የሬዲዮ አገልግሎት መስፋፋቱን ቀጠለ::

የሬዲዮው ጣቢያ ይበልጥ እመርታ አሳይቶ መመንደግ የጀመረው በ1953 ዓ.ም ከተከሰተው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ነበር:: “ሥርጭቱንም እጅጉን በማስፋት ለምዕራብና ለሰሜንናዊ ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት፣ አንዲሁም ለምዕራብ አውሮፓ በፈረንሳይኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች፣ ለሰሜን አፍሪካና ለመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በዓረብኛ፣ ለምሥራቅና ለመካከለኛው አፍሪካ ሀገራት በስዋሂሊኛ የማያቋርጥ አገልግሎት ወደ ማቅረብ ተሸጋገረ::” (የዜና ማሰራጫ ዘዴ በኢትዮጵያ፣ 1959 ዓ.ም):: እንዲህ እንዲህ እያለ በከፍታ የተጓዘው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዛሬ ከስልሳ ዓመታት በኋላ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የምናውቀው ስለሆነ አጅግም ጫን አንልም::

33ኛው ዓመት የንጉሡ የዘውድ በዓል ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም ሲከበር ውልደቱ የታወጀለት የቴሌቪዥን ጣቢያም በብቁ ባለሙያዎች ተደራጅቶ ስላልነበር ያስተላልፋቸው የነበሩት ፕሮግራሞች በአብዛኛው የውጭ ሀገራትን ፊልሞች ነበር:: ከ1958 ዓ.ም ጀምሮም የመደበኛ ትምህርት ፕሮግራሞችን በተከታታይ ዓመታት በማስተላለፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን በከፍተኛ ትጋት አገልግሏል:: ይህ ዐምደኛም የዚያ ትሩፋት ተጠቃሚ ከሆኑት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው:: በዘመነ ደርግ 1977 ዓ.ም የኢሠፓ ምሥረታ ምክንያት ሆኖ ከጥቁርና ነጭ ወደ ከለር የተለወጠው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የጉዞ እድገቱ እጅግም ፈጣን ነው ባይባልም ዘመኑን እንደ ዘመኑ በሚገባ በመግለጹ ሊመሠገን ይገባል::

ዛሬ ኢቢሲ እመርታ ጨምሮ ያስገነባው ኮምፕሌክስ በምንም መሥፈርት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለው ነው:: የስቱዲዮው ብዛትና ጥራት አበጀህ የሚያሰኝና የሚያስመሰግን ነው:: ተጓዳኝ የግቢው አገልግሎቶችም አዲስ ምዕራፍ የተከፈተላቸው ማሳያዎች ናቸው::

የኮምፕሌክሱ ውበት ያማረውን ያህል ይዘቱም ከሕዝብ ልብ እንዲደርስና የአድማጭ ተመልካቹን ስሜት እንዲያረካ ብዙ ሊሰራ እንደሚገባው ተደጋግሞ ስለተገለጸ የምናጸናው ይህንኑ ማሳሰቢያ ነው:: ምንም እንኳን የመንግሥት ልሳንነቱን መጋፋት ባይቻልም ዋናው ባለጉዳይ ሕዝብ ስለሆነ መልእክቱም ሆነ አዝናኝነቱ፣ መረጃ አቅርቦቱም ሆነ አሳዋቂነቱ በሕዝብ ጠረን እንዲታጠን አደራችንን ደግመን ደጋግመን እናስተላልፋለን:: በምስጋና ጀምረን በምሥጋና ማጠቃለሉ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ስለሚገባውም ኢቢሲ ሆይ እንኳን ደስ ያለህ! ገለቶማ:: ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ::

በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ/

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *