‹‹አብዛኞቹ የሽብር ጥቃቶች ማንነትን የሚገልጹ ሰነዶችን በማጭበርበር የሚፈጸሙ ናቸው››

አቶ ዮናስ አለማየሁ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ላለፉት 80 ዓመታት የከተማዋን ነዋሪዎች በማገልገል ላይ ያለ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም ለከተማዋ ነዋሪዎች በዘርፉ ያለውን የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በተለይም ለከተማዋ ነዋሪዎች የወሳኝ ኩነት መረጃዎችን በመመዝገብና ማደራጀት ላይ የሚሰራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትግበራ እንዲሁም ወሣኝ ኩነት መረጃዎች እንዴት እያደራጀ እንደሆነ፤ በሥራው ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን እንዲሁም አጠቃላይ የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ አዲስ ዘመን ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

 አዲስ ዘመን፡የከተማዋ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ዮናስ፡ ተቋሙ 1935 ዓ.ም የመጀመሪያ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ሥራውን ጋብቻ በማፈራራም ጀምሮ አሁን ላይ 80 ዓመቱን እያስቆጠረ ነው::

እንደ አንድ ሕጋዊ ተቋምም በሕግ የተሰጡት ሁለት ሥልጣንና ተግባር አሉት :: አንደኛው በከተማ ውስጥ የሚከሰቱ ሁነቶችን መመዝገብና ለሚመለከተው የፌዴራል ተቋም ማስተላለፍ ሲሆን ፣ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ሁነቶችን መመዝገብ ነው:: ዘርፉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ እና ክልል አቀፍ ደረጃ በተቋሙ እንዲመራ ከተደረገ ጀምሮ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ነው:: የኩነት ዘርፍ ሥራ በአዋጅ 760/2004 በወጣው መሠረት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና ብሄራዊ መታወቂያ አዋጅ መነሻ በማድረግ እየተተገበረ ነው::

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም አብዛኞቹንና በዓለም አቀፍ ወሳኝ ኩነት የሚባሉትን በመቀበል እየተገበረች ወይንም እየመዘገበች ነው:: ከነዚህ ውስጥ አንዱ የነዋሪነት አገልግሎት ዘርፍ ነው ። በዚህ ውስጥ ብዙ ዓይነት አገልግሎት አሉ:: ለአብነት አንድ ሰው አዲስ አበባ ውስጥ መጥቶ ነዋሪ ሆኖ ለመመዝገብ ማመልከቻ ሲያስገባ ነዋሪ ሆኖ ይመዘገባል:: በዚህ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት ያገኛል:: ያላገባ፣ ያገባ፣ ዝምድና ማረጋገጥ፣ ወዘተ የመሳሰሉትን አገልግሎት ማግኘት ይችላል::

አንድ ሰው ከተማ ውስጥ ሲኖር መሠረታዊ የሚባሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ይረዳው ዘንድ የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ይጠይቃል:: በመሆኑም ተቋሙ እነዚህን አገልግሎቶች በስፋት እየሰጠ ይገኛል::

 አዲስ ዘመን፡በወሳኝ ኩነት ምዝገባ አሁናዊ አሃዛዊ መረጃዎች ምን ያመለክታሉ?

አቶ ዮናስ፡ የእኛ ኩነት ምዝገባ እንደ ሀገር መቶ በመቶ ባለመሆኑ የሞተውን፣ የተፋታውን፣ የተወለደውን ሙሉ ለሙሉ ማስቀመጥ አይቻልም:: በመሆኑም የተከሰተውን ሪፖርት ሙሉ በሙሉ ሪፖርት እያደረግን አይደለም:: ልደትን ለአብነት ብናነሳና ከዚህም ውስጥ ወቅታዊ ልደት ስንመለከት የ2015 ዓ.ም ከ2014 ዓ.ም አኳያ ሲታይ በሽፋን ደረጃ በ112 በመቶ አድጓል::

የፍቺ ምዝገባ ቁጥርም ጨምሯል:: በዓማካይ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀን 60 ፍቺዎች እየተመዘገቡ ነው:: ፍቺን ስንመለከት ፍቺ ከተከሰተ በኋላ ዘግይተው የሚያስመዘግቡ አሉ፤ ከዓመት በኋላ አልፎ፤ ከ10 ዓመት በኋላ የሚመጡ አሉ::

ልደት በዓማካይ በቀን 500 ይመዘገባል:: ሰዎች ይህን የልደት ምዝገባ በብዛት የሚያደርጉት ለኤምባሲ እና ለውጭ ጉዞ ለመሳሰሉት ነው:: አሁን የሚስተዋለው ለምንፈልጋቸው ነገሮች ስንል ብቻ እናስመዘግባለን:: ይሁንና አብዛኞቻችን አልተመዘገብንም:: በብዛት ‹‹ባክሎግ›› ነው:: በአንፃራዊነት ሲታይ ግን ባለፉት አራት ዓመታት ለልደት ምዝገባ የሚመጣው እየጨመረ ነው::

ይህ ማለት በወቅቱ መመዝገብ ያለባቸው እየተመዘገቡ ጊዜ ገደቡ ያለፈበት ምዝገባ ደግሞ እየቀነሰ መሆኑን ያሳያል:: ይህ የሚያሳያው ለውጥ እየመጣ ነው:: ለዚህም በትምህርት ቤቶች ጭምር እየገባን እየመዘገብን ነው::

 አዲስ ዘመን፡በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማካሄድ እንደ ሀገር ትርጉሙ ምንድን ነው? አሃዛዊ መረጃዎች ምን ያመለክታሉ?

አቶ ዮናስ፡ በሌላው ዓለም ይህ ሥራ ከብዙዎች የልማት ሥራዎች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የቀደመ ነው:: ትርጉሙም ዘርፈ ብዙ ነው:: አንድ ሀገር ዘመናዊ የመንግሥት ሥርዓት አላት ለማለት በመጀመሪያ የህዝብ ቁጥር ማወቅ ግዴታ ነው:: ይህ ማለት ከሚወለደው እስከ የሚሞተው ድረስ ያለውን ቁጥር ማወቅ አስገዳጅ ነው::

በትንሹ በአንድ ሀገር የሚወሰኑ ውሳኔዎች በትክክለኛ አሃዝና መረጃ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ያግዛል:: የህዝብና ቤት ቆጠራ ትክክለኛነትም እጅግ በጣም የተረጋጋጠ እና ሁነኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ እንዲሆንም ያስችለዋል::

ይህ ካልሆነ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከህዝብ ቆጠራ ጋር የተዛመደ አይሆንም ማለት ነው:: የሚወለደውንና የሚሞተውን በአግባቡ ከመዘገብን በአምስት እና አስር ዓመት ቆጠራ ማካሄድ አስገዳጅ ላይሆን ይችላል:: በእርግጥ ህዝብና ቤት ቆጠራ አስፈላጊ ነው:: ሆኖም እነዚህ መረጃዎች በአግባቡ ከተመዘገቡና መረጃዎች ከተደራጁ ቆጠራው ባለመካሄዱ ይህን ያክል ክፍተት አይፈጥርም::

ይህ ምዝገባ ሦስት መሠረታዊ ጠቀሜታዎች አሉት:: ለሕጋዊ፣ አስተዳደራዊ እና ስታስቲክሳዊ ጉዳዮች ፋይዳው የላቀ ነው:: ለሕጋዊ ጉዳዮች ስንል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተዘረጋ በኋላ ኩነቱን ያስመዘገበው ሰው ማስረጃውን ከወሰደ በየትኛው የሕግ ማስረጃ ሁኔታዎች ላይ ያለምንም ተጨማሪ ማስረጃ አሳማኝ ሆኖ ይቀርባል::

የጋብቻ ማስረጃ በሁለት ሰዎች መካከል ያለውን

 ሁኔታ ያለ ተጨማሪ ማስረጃ በቂ ሆኖ መቅረብ ይችላል:: ሰዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳያቸውን ፍትህ ሊያስገኙበት ወይንም ፍትህ ለማግኘት በሚያስቡበት ወቅት በሕግ ፊት ይህ ማስረጃ አስረጂ እና አሳማኝ ሆኖ መቅረብ ይችላል::

አዲስ ዘመን፡የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አስተዳደራዊ ሁኔታዎች ላይ ፋይዳው እስከ ምን ድረስ ነው?

አቶ ዮናስ፡ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ በአስተዳደራዊ ጉዳዮችም ላይ ወሳኝ ሚና አለው:: በተለይ ለፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ እቅድና ፕላን ለማውጣት፣ ለመወሰን ብሎም ለተያያዥ ጉዳዮች ፋይዳው የጎላ ነው:: ለአብነት በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የሚወለደውን የህፃናት ቁጥር ማወቅ ከተቻለ ከአራት ዓመት በኋላ ስንት ህጻናት መዕዋለ ህፃናት ይገባሉ የሚለውን ለማወቅ ይረዳል::

ስለዚህ ለዚህ ስንት መምህራን፣ ትምህርት ቤቶች፣ ምዝገባ ማዕከል፣ መማሪያ ክፍሎችና ቁሳቁስ ብሎም ሌሎች ግብዓቶች ያስፈልጋሉ የሚለውንም ለማወቅ ይጠቅማል:: ስለዚህ ወሳኝ መረጃዎችን ለመወሰንና ለቀጣይ ሥራም መሠረት የሚጥል ነው::

በከተማ ውስጥ ያለውን ፍቺ አሃዝ ማወቅም ትርጉሙ ሰፋ ያለ ነው:: ለምሳሌ በፍቺ ውስጥ በየትኛው የዕድሜ ክልል ያሉት እየተፋቱ ነው የሚለው ለጥናትና ትንተናም ይጠቅማል:: እየተጋቡ ያሉትስ በምን የዕድሜ ደረጃ ያሉት ናቸው፤ የኢኮኖሚ ወይንም የገቢ ሁኔታቸው ምን ይመስላል? ትዳር ከመሠረቱ በኋላ አብሮ የመቆየት ዝንባሌ ምን ይመስላል? የሚሉትንና ሌሎችን ለማወቅ ያገዛል:: በየቦታው የምንመለከታቸው ወይንም ጎዳና ላይ ያሉት ህፃናት ከየት መጡ? የሚለውን ለማወቅም በእጅጉ ይጠቅማል::

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ለአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ያግዛል:: ይህ ምዝገባ በሀገሪቱ ውስጥ መቶ በመቶ ሽፋን ቢኖረው ችግሩንም ወይንም ማህበራዊ ቀውሱን በደንብ ለማወቅም ያግዛል:: ለሴቶችም በጣም ይጠቅማል:: በርካቶች ተጋብተው

 አብረው ይኖራሉ እንጂ በወሳኝ ኩነት አያስመዝግቡም:: በመሆኑም መሰል መረጃዎችን ለማወቅና ለመለየት ፋይዳው የጎላ ነው::

 አዲስ ዘመን፡አዲስ አበባ ውስጥ ጋብቻ ፈጽመው በወሳኝ ኩነት የማይመዘገቡት ስንት ናቸው?

አቶ ዮናስ፡ በዚህ ላይ ዳሰሳ ጥናት አልሰራንም:: አብዛኛው ሰው ጋብቻን መፈፀምን ወይንም ጋብቻ ተከናወነ ብሎ የሚቆጥረው የቤተሰብ መተዋወቅ፣ ፎቶ መነሳትና የመሳሰሉትን እንጂ ማስመዝገቡ ላይ ገና ብዙ መሥራት ይገባል:: ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ሰፋ ባለ ደረጃ እየተመዘገቡ ያለውና ጥናትም ያለው የልደት ነው::

አዲስ ዘመን፡በልደት ላይ ያለው መረጃስ ምን ይጠቁማል?

አቶ ዮናስ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዩኒሴፍ እኤአ በ2017 ባወጣው መረጃ መሠረት ከሚወለዱት አምስት ህጻናት ውስጥ አራቱ አይታወቁም፤ ወይንም ልደታቸው አይመዘገብም:: በዘመናዊ አነጋገር ደግሞ ተወልዶ ልደቱ ያልተመዘገበ ህፃን ልጅ በመንግሥት አይታወቅም ማለት ነው:: ሳይታወቅ ወደዚህች ምድር መጥቶ በመንግሥት ሳይታወቅ ይሄዳል ማለት ነው::

ይህ በአንፃራዊነት የራሱ ትርጉም አለው:: በተለይም ከህፃናት መብት አኳያ ሲታይ ማግኘት ያለባቸውን አያገኙም ማለት ነው:: ይህ ሥርዓት በወቅቱና በአግባቡ ቢዘረጋ ኖሮ ብዙ ችግሮች ይቃለላሉ:: ሰዎች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ቢመዘገቡና የወሳኝ ኩነት ሥርዓት ቢጠናከር አንድ ሰው በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ መታወቂያ ካርዶችን አያወጣም ነበር:: ወይንም ደግሞ መታወቂያ ለማውጣትና ለመሳሰሉት አገልግሎቶችም እንግልቶች አይኖሩም ማለት ነው:: የሃሰተኛ ሰነድ መስፋፋትና የሁሉ መሠረቱ ይህን ሥርዓት በአግባቡ ባለመተግበሩ ነው::

 አዲስ ዘመን፡በአዲስ አበባ ሁለትና ከዚያ በላይ መታወቂያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን ተቋሙ ያውቃል?

አቶ ዮናስ፡ በትክክል! እኛ ዘንድ የሥነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና ክፍል አለ:: በየጊዜው ሰነድና መረጃዎችን ይይዛል፤ ኦፕሬሽን ይሰራል:: በበጀት ዓመቱ በማጭበርበር እና በሃሰተኛ መረጃና በመሳሰሉት ላይ ሲሳተፉ የተገኙት 169 ሰዎች ተገኝተዋል::

ይህ ካለን ሥርዓትና ከመጣንበት አኳያ ሊገርመን አይገባም:: ከችግሩ ስፋት አኳያ ኢትዮጵያ ተጋላጭ አልሆነችም:: ይህን ሥርዓት ባለመዘርጋታችን ሊደርስ የነበረው ችግር በራሱ አልደረሰም ብለን እንገምታለን::

ለአብነት አንድ ሰው ከሌላ ቦታ መሸኛ ይዞ መጥቶ የአዲስ አበባ መኖሪያ መታወቂያ ሲጠይቅ ይህን ለማጣራት እንኳን የዘረጋነው ሥርዓት አልነበረም፤ የምንመለከተው ማህተም መኖሩን ብቻ ነው:: ስለዚህ በዚህ ላይ መሥራት ከነበረበት አኳያ ብዙ አልሰራንም ማለት ነው::

ከጎረቤት አገር ከሚመጡ ስደተኞች ጋር የሚመሳሰል ኢትዮጵያዊ ፊት ወይንም ገፅታ አለ:: ይህ ሰው የአዲስ አበባ መታወቂያ ይዞ ሊገኝ ይችላል:: ለዚህ ደግሞ ሀገር አቀፍ ሥርዓት ባለመዝርጋታችን የመጣ ነው:: በእንጭጭ ላይ ያለ ሥርዓት ነው:: በመሆኑም ይህን ሥርዓት ባለመዘርታችን ለአደጋ አልተጋለጥንም:: አዲስ አበባ ለማህበራዊም ፖለቲካዊም ክስተቶች ማዕከል ናት:: አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ አዲስ አበባ ተጋላጭ የመሆን ዕድል አላት:: በመሆኑም ለመፍትሄ እየተጋን ነው::

አዲስ ዘመን፡በስደተኞች ሥም አዲስ አበባ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና የከተማዋ ነዋሪነት መታወቂያ ያላቸው መኖራቸውንስ መረጃው አላችሁ?

አቶ ዮናስ፡ እኛ ማወቅ ብቻ ሳይሆን እንደ ሌላ ተቋም ችግር እስኪከሰት አንጠብቅም:: በአሁኑ ወቅት ይህን ችግር ለማቃለል ትልቅ የሪፎርም ሥራ ሰርተናል:: የአሰራር ሥርዓታችንን ቀይረናል:: ከዚህ ቀደም የነበረው አካሄድና አሰራር አግባብ ባለመሆኑ ብዙዎችን ለማሻሻል ተገደናል:: ከዚህ ቀደም የምንጠቀምባቸውን ካርዶች ሙሉ ለሙሉ ቀይረናል ወይንም እንደገንዘብ ‹ኖት› በአዲስ ተክተናል:: ከዚህም በተጨማሪ አገልግሎት ስንሰጥባቸው የነበሩ ፕሪንተሮችንም ቀይረናል::

አዲስ ዘመን፡- ፕሪንተሮችንና ካርዶችን ለመቀየር አስገዳጅ ሁኔታ ነበር?

አቶ ዮናስ፡- አዎ በትክክል! ሪፎርም ስናደርግ አንዱ ችግር አለበት ከተባሉት መካከል አገልግሎት ሲጥበት የነበሩ ካርዶች ጭምር የስርጭት ሥርዓታቸው ትክክል አልነበረም:: ሁለተኛው ከሀገር አቀፍ ካርድ ሥርጭት ጋር ምንም የሚለይ ነገር አልነበረውም:: ይህ ደግሞ አዲስ አበባ ወይንም ባህርዳር የተሰራጨ ካርድ ድሬዳዋ ሊገባ ይችላል፤ ሀሰተኛ ሰነድም ሊሰራበት ይችላል::

በተጨማሪም በእኛው መዋቅር ሥር ሆኖ ካርዶቹ ከእኛ እጅ ወጥተው ደላላ ወይንም ‹‹ፎርጂድ›› ሰሪ እጅ ይገባ ነበር:: ስለዚህ እንደ ገንዘብ ኖት መቀየር ነበረብን:: አደጋ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ስለታሰብም መቀየሩ አስገዳጅ ሆኗል::

አዲስ ዘመን፡ለዚህ ወጪው ስንት ነበር?

አቶ ዮናስ፡ ካርዶቹ ደረጃቸው የጠበቁ ናቸው:: ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ልክ እንደ ገንዘብ ህትመት ደረጃውና ምስጢራዊነቱ ተጠብቆ የታተመ ነው:: ልክ እንደ ቼክ ለእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ በስማቸው እየታተመ የሚወጣ ነው::

አሁን ያስገባነው ፕሪንተር ደግሞ ‹‹ሲኩሪቲ ፕሪንተር›› ይባላል:: በምስራቅ አፍሪካም በኢትዮጵያም የመጀመሪያው ፕሪንተር ነው:: ግዥውንም የፈጸምነው ከአሜሪካ ነው:: በዋጋ ውድ ብቻ ሳይሆን የአንድን ሰው ማንነት በሰርተፍኬቶቹ ውስጥም አትሞ የሚያወጣ ነው:: በዓይን ከሚታዩት ውጭ በዓይን የማይታይ ሚስጥራዊ ህትመት በውስጡ ያለው ነው::

የተመዝጋቢውን ፎቶ ግራፍ ጭምር በሰርተፍኬት ውስጥ አብሮ የሚያትም ነው:: ሀሰተኛ ሰነድ የሆነ እና ያልሆነ ሰነድ የሚለይበት ሥርዓት ዘርግተናል:: ይህንንም በከፍተኛ ወጪ ልንገዛውና ልንተገብረው የተገደድነው ሃሰተኛ ሰነድ የሚያደርሰውን ኪሳራ ለማስቀረት ነው::

ሃሰተኛ ሰነድ እጅግ አደገኛ የሆነና አደጋ እየፈጠረ  ነው:: ሥርዓታቸውን እያሻሻሉ የመጡት ካልሆኑ በስተቀር የትኞቹም ሀገራት ለሃሰተኛ ሰነድ ተጋላጭ ናቸው:: ኢኮኖሚ ባደገ ቁጥር ሃሰተኛ ሰነድ የማዘጋጀት፤ ሰዎች ማንነታቸውን የማጭበርበርና ከአንድ በላይ ማንነት የመያዝ ዝንባሌያቸው ከፍተኛ ይሆናል:: ሰው በተለየ መንገድ ማንነቱን ለመቀየር፣ ለመሰወርና ሀብት ለማግኘት ብሎም ለማጭበርበር ጥረት ያደርጋል::

 አዲስ ዘመን፡ይህ ለሽብር ተግባር የማጋለጥ እድልስ የለውም?

አቶ ዮናስ፡ ሰነድ ማጭበርበር ሽብር ለመፈጸም ጭምር ይጠቀሙበታል:: የአሜሪካው 9/11 የሽብር ተግባር ማንነትን በማጭርበርና በመግባት የተፈፀመ ነው:: አብዛኞቹ የሽብር ጥቃቶች ማንነትን የሚገልፁ ሰነዶችን በማጭበርበር የሚፈፀሙ ናቸው:: ዘርፉ በተፈጥሮም የዓለም ልምድም የሚያሳየው ተጋላጭ ነው:: ግለሰብ እና ድርጅት ላይ ለማድረስም እነዚህ ሰነዶች ተጋላጭ ናቸው:: ስለዚህ እንደ አዲስ አበባ ይህን ለማስተካከል ነው የሚሰራው::

አዲስ ዘመን፡ተቋሙ መሰል ስጋቶችን ለመቀነስ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ዮናስ፡እንደ አዲስ አበባ ካርዶችን መቀየር የመጀመሪያው ነው:: ቀደም ሲል የአሰራር ሥርዓት አልነበረውም:: ካርድ እንደማንኛውም ንብረት ክፍል ይገባና ይወጣ ነበር:: አሁን ኦዲት የሚደረግበት ሥርዓትና ስርጭት ዘርግተናል:: አንዳንድ ቦታ ካርድ ጨርሰናል የሚሉ አሉ::

ይህ ማለት ካርዱ ማለቁንና ኦዲት መደረጉ በትክክል ሳይረጋገጥ ካርድ አይላክም:: ቀደም ሲል መዋቅር አልነበረውም:: አሁን ሥርዓት አለው፤ መዋቅር አለው:: በየዕለቱ የሚሰጠው ካርድ ልክ ባንክ ላይ እንደሚሰራ ገንዘብ ጠዋት ርክክብ ተደርጎ ማታ ቆጠራ ተደርጎ ነው ርክክብ የሚፈፀመው:: ባለሙያ እጅ የሚያድር ካርድ አይኖርም::

አዲስ ዘመን፡ይህን አሰራር ለማዘመን የተወገዱና የታተሙት ስንት ናቸው?

አቶ ዮናስ፡ አገልግሎት ላይ ያልዋሉትን ጨምሮ 25 ሚሊዮን ብር በላይ በላይ የሚገመቱትን አስወግደናል:: ይህን የሚተካ አትመን አሰራጭተናል:: አሁን ባለው ሁኔታ አንዱ ክፍለ ከተማ ያለው ከሌላው ክፍለ ከተማ እንኳን የሚያገለግል አይደለም:: ስለዚህ ከአንዱ ክፍለ ከተማ ሌላው ክፍለ ከተማ ሄዶ ማጭበርበር አይቻልም:: ከዚህ ቀደም ያለገደብ ይሰራጭ ነበር:: አሁን ግን ለአንድ ወረዳ ለ15 ቀናት የሚያገለግል ብቻ ነው የሚሰራጨው::

አዲስ ዘመን፡የተሰራጩት አዳዲስ ህትመቶች ምን ያክል ናቸው?

አቶ ዮናስ፡ በአሁኑ ወቅት 600ሺ በላይ ካርዶች ተሰራጭተዋል:: የልደት፤ የጋብቻ የመሳሰሉት አሉ:: በወር ክፍለ ከተማ ከማዕከል ይረከባል:: ወረዳ ደግሞ ከከፍለ ከተማ ይረከባል:: ይህ በዓመቱ መጨረሻ እንደማንኛወም ንብረት ይቆጠራል:: ጉድለት ከተገኘ እንደማንኛውም አካል ተጠያቂነት አለ::

ባለፈው ዓመት በነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ኦዲት ተደርጎ ጉድለት በተገኘበት ቦታ ተጠያቂነት ማስፈን ተችሏል:: 600ሺ ካርዶች በኋላም ሁለተኛ ዙር ታትሟል:: ይህም የሆነው በአንዳንድ የኩነት ምዝገባዎች ላይ ከፍ ያለ ፍላጎት ስለሚከሰት ነው::

አዲስ ዘመን፡ይህን አሠራር ሊተገብር የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ተችሏል?

አቶ ዮናስ፡ በአጠቃላይ ሪፎርማችን በዋናነት አስፈላጊ በሚባሉ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው:: የመጀመሪያው የቴክሎጂ መጠቀም አቅም ነው:: ይህን ከላይ በገለፅኩት መንገድ እየተተገበረ ነው:: መመሪያዎችን በማሻሻል ብቁ የሰው ኃይል በተገቢው ቦታ መመደብ ሥራ ሰርተናል:: ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበርም ለባለሙያዎች ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል::

የእኛ ሰነድ ከሀገር ደህንነት ጋር ካለው ቁርኝት አኳያ በትጋት እየሰራን ነው:: የሰኩሪቲ ኢንተለጀንስ ዲፓርትመንት ለመክፈትም ጥረት ጀምረናል:: አመራሮችም በዚሁ ልክ በትጋት እንዲሰሩ አድርገናል፤ እየተሰራም ነው:: በዚህ ዘርፍ በጤና ተቋማት ገብተን እንመዘግባለን:: ትምህርት ቤቶችም ላይ ምዝገባ አለ:: የሰው ኃይል አቅም መገንባትና መመደቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል:: መዋቅርና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲጣጣም እየሰራን ነው::

አዲስ ዘመን፡ይህን አሠራር በመዘረጋታችሁ ዘርፉ ላይ ያለው ሙስና ቆሟል ማለት ነው?

አቶ ዮናስ፡ አይደለም:: ከሙስና የፀዳ የመንግሥት ተቋም የለም:: ሙስና ድርጊት ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብ ጭምር ነው:: ሙስና ገንዘብ መስረቅ ብቻ አይደለም:: የመንግሥትን የሥራ ሠዓት አለማክበርና መሸራረፍ ሙስና ነው:: እኛ በሪፎርም ውስጥ ብዙ ነገር ነው ያሰብነው:: አገልግሎት ተቋርጦ የነበረው የካርድ ሥርጭታችን አግባብነት የጎደለው በመሆኑ ነው:: በአገሪቱ በተከሰተው ጦርነትንም ሳቢያ ሰርገው ለመግባትና ሀሰተኛ ሰነድ በመያዝ የሚንቀሳቀሱ በመኖራቸው ጭምር ተቋርጦ ቆይቷል::

ነገር ግን ሪፎርሙን ስንጀምር ብዙ ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ ነው:: ስለዚህ ይህን ችግር ለማቃለል ቴክኖሎጂ መጠቀም አለብን ብለን ነው የተነሳነው:: በአዲስ አበባ ከተማ ካሉን 118 ወረዳዎች ውስጥ 114 ወረዳዎች በቴክኖሎጂ አገልግሎት እየሰጡ ነው:: 14 ወረዳዎችን ወደዚህ ለማስገባት ሂደት ላይ ነን:: በዚህ በጀት ዓመት ብቻ 550ሺ የዲጅታል ምዝገባ ሰጥተናል:: የማንዋል አገልግሎት የሰጠነው በ10 ወር ውስጥ 61ሺ ነው:: ስለዚህ 91 በመቶ አገልግሎታችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው::

አዲስ ዘመን፡ለነበረን ቆይታ እያመሰገንሁ የሚጨምሩት ሃሳብ ካለ ዕድሉን ይጠቀሙ::

አቶ ዮናስ፡ አመሰግናለሁ፤ የእኛ አቋም 2016 ኢዲስ አበባ የወረቀት መታወቂያ አትሰጥም:: ቀደም ሲል ማንዋል የተሰጣቸው በእጃቸው ያለው ጊዜው እስከሚያበቃ መጠቀም ይችላሉ:: ቤት ለቤት የጤና እክል ላለባቸው አገልግሎት እየሰጠን ነው:: ከእነዚህ ውጭ ሁሉም ወደ ዲጂታል ሥርዓት ይገባል:: ከሙስና የጸዳ ተቋም እናደርጋለን ብለን ጥረት እናደርጋለን::

ይሁንና ችግሮች የሉም ማለት አይደለም:: ይህ ግን በሂደት የሚስተካከል ይሆናል:: እስካሁን በመረጃ ቋታችን 1 ነጥበ 9 ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎች ዲጂታል ምዝገባ አድርገዋል:: በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ይዘዋል:: ቀደም ሲል ዲጂታል መታወቂያ የሚታተመው በአንድ ማዕከል ነበር:: አሁን ወደ 11 ወረዳዎች ወረዳዎች ወርዷል::

ተቋማችንም 80ኛ ዓመቱን እያከበረ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ ብዙ ታሪካዊ ተግባራትን አከናውኖ ያለፈ ነው:: በቀጣይ ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጥ ተጠቃሽ ተቋም እናደርገዋለን:: አገልግሎታችንም የተቀላጠፈ ይሆናል::

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም

 

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *