የሱዳንን መደበኛ ጦር በሚመሩት ጄነራል አብዱልፋታህ አል-ቡርሃንና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉን በሚመሩት ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) መካከል በተነሳ አለመግባባት የተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት በማስከተል ላይ ይገኛል:: ሦስት ወራት ሊሞሉት ጥቂት ቀናት በቀሩት በዚሁ ግጭት ምክንያት በርካቶች ከመሞታቸውም ባሻገር ፤ወደ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ እንደተፈናቀለና ከእነዚህ ውስጥ 700 ሺ የሚሆኑትን ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ::
በጦርነቱ ሳቢያ የመኖሪያ አካባቢዎች ዒላማ በመሆናቸው በርካታ ንጹሃን ዜጎች በእጅጉ የተጎዱ ሲሆን ሆስፒታሎችን ጨምሮ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል። የተለያዩ ሰብዓዊ ርዳታዎችም ለተጎጂ ወገኖች ማድረስ በእጅጉ ፈታኝ ሆኗል::
ይህ ግጭት እንዲያበቃ በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም አንዳችም ተጨባጭ ውጤት ሳያመጣ ጦርነቱ ዛሬ ድረስ ዘልቋል:: በአሜሪካና በሳኡዲአረቢያ ሸምጋይነት የተካሄዱት ድርድሮችም ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ቢሆንም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተጥሶ ውጊያው እስከአሁን ድረስ ቀጥሏል::
የሱዳን ግጭት በውይይት እንዲፈታና ሱዳን ወደቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት በምህጻረ ቃሉ ኢጋድ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል:: ኢጋድ የሱዳንን ግጭት በውይይት ለመፍታት ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ውይይት አካሂዶ የነበረ ሲሆን በዚሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐመድ አሊ እና የኢጋድ ሊቀ መንበር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተሳታፊ ሆነዋል።
በውይይቱ ላይ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ባይገኙም የውይይቱ ተሳታፊዎች የሱዳን ኃይሎች ግጭት በወታደራዊ አማራጭ መፍትሔ እንደማያገኝ በመገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እና ስምምነቱን የሚቆጣጠር ሥርዓት እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል::
ከዚህ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተደርሰው መጣሳቸውን ያነሳው የኢጋድ መግለጫ፤ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የሚደረሰው ተኩስ አቁም የመተግበሪያ ዘዴ ሊበጅለትና ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል::
ኢጋድ በመግለጫው አሁን በሱዳን ያለው ሁኔታ በውጭ ጣልቃ ገብነት ምክንያት እየተራዘመና እየተባባሰ መምጣቱም አንስቷል። ስለዚህም ወታደራዊ አማራጭ ለሱዳን መፍትሄ ስለማይሆን ተፋላሚ ኃይሎችን ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል:: የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችም ፊታቸውን ወደ ሰላም እንዲያዞሩ ጥሪ አቅርቧል::
የኢጋድ የሰላም ጥሪ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል የሚያመላክት ነው:: በተደጋጋሚ እንደታየውም አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ አቅም የመፍታት አቅም ያላት አህጉር ነች:: ከዚህ ቀደምም እንደታየው በአፍሪካ ህብረት የተመራው የሰላም ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ችግር ፈትቶ ኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ማድረግ ችሏል:: ስለዚህም አሁን ኢጋድ የጀመረውም ጥረት ፍሬ እንዲያፈራና ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ ተፋላሚ ወገኖች ችግራቸው በአፍሪካዊ መፍትሄ ሊፈታ እንደሚችል በቅድሚያ ማመን እና ለጥሪውም አዎንታዊ መልስ ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል::
በአጠቃላይ ሦስት ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀሩት የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ከመቀጠፉም ባሻገር በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ትተው እንዲሰደዱ አድርጓል:: ከዚሁ ባሻገርም ሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈግላቸው ወገኖች እንኳን በቂ አቅርቦት ለማዳረስ ጦርነቱ ፋታ እንዳልሰጣቸው ግብረሰናይ ድርጅቶች እየተናገሩ ነው:: በዋና ከተማዋ ካርቱምም ነዋሪዎች በምግብ እጥረት እና እየተስፋፋ በመጣው ዝርፊያ ምክንያት ከባድ ጊዜ እያሳለፉ መሆናቸው እየተነገረ ነው።
ስለሆነም የሱዳናውያን ስቃይ እንዲያበቃና ሱዳንም ወደነበረችበት መረጋጋት እንድትመለስ ተፋላሚ ኃይሎች በኢጋድ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ውይይት ሊመጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም