በስልጤ ዞን ከሰባት ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን በ2015 ዓ.ም ከሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ለመትከል አቅዶ እየሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ:: በበልግ ወቅት ብቻ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን የቡና ችግኝ መተከል መቻሉም ተገልጿል::

በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ልማት ኃላፊ አቶ ሙርሰል አማን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በስልጤ ዞን የቡና ልማት ሥራ አበረታች እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል:: በዘንድሮ ዓመት ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ በበልግ ወቅት ብቻ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተተክሏል::

እንደ አቶ ሙርሰል ገለጻ፤ ዞኑ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው:: በዘንድሮ ዓመት 250 ሄክታር ያረጀ ቡና ለመጎንደል ታቅዶ 253 ሄክታር መፈጸም ተችሏል:: በተጨማሪም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትና አጠቃቀም እየተተገበረ በመሆኑ የቡና ምርታማነት እያደገ መጥቷል ሲሉ ገልጸዋል::

የቡና ማስፋት ስትራቴጂን መሰረት ያደረገ የቡና ክላስተር ተከላ ሥራ አበረታች ውጤት እየመጣ ይገኛል ያሉት አቶ ሙርሰል፤ በዞኑ ከቡና መሬት ሽፋን ውስጥ በዘንድሮ ዓመት ምርት ከሚሰጠው አምስት ሺህ 285 ሄክታር ማሳ ላይ 35 ሺህ 224 ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል:: ምርቱንም ለዓለም ገበያ በማስተዋወቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል::

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *