ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር ጨምሯል

አዲስ አበባ፦ በአዲስ አበባ ከተማ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል አስታወቀ። በአሁኑ ጊዜም ከ310ሺ በላይ ሕጻናት በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል።

የማእከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተዘረጋው ቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም በተሠሩ ሥራዎች፤ የሕጻናት የትምህርት ተደራሽነት እያደገ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥትም ሆነ በግል ትምህርት ቤቶች እድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት ዓመት የሆነ ከ310ሺህ በላይ ሕጻናት በቅድመ አንደኛ የትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።

ቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ምን መልክ ሊኖረው ይገባል? በሚል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2013ዓ.ም መነሻ ጥናት ዳሰሳ መደረጉንና በአዲስ አበባ ከተማ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ የነበሩት ሕጻናት 49 በመቶ ብቻ እንደነበሩ ዶክተር ከበደ አመልክተዋል።

የሕጻናትን የእደገት ሁኔታ ጥናቱን መሠረት አድርጎ በተደረገ ምዘናም በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ሕጻናት 89 በመቶ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዝግጁ እንደሆኑ መረጋገጡንና በተመሳሳይ በሐምሌ ወር በሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት ቁጥሩ እንደሚጨምር ይገመታል ብለዋል። ቀደም ሲል ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዝግጁ የሆኑ ሕጻናት 39 በመቶ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሕጻናቱ የመቀበል ችሎታቸውን መሠረት ያደረገ በጨዋታ የማስተማር ሥነ ዘዴ እየተከተለ መሆኑንም አስረድተዋል። ሕጻናት በወቅቱ ቅድመ አንደኛ ከገቡ ለቀጣይ ትምህርት ዝግጁ የሚያደርጋቸውን መሠረታዊ ነገር ለማወቅ እንደሚያስችላቸው፣ በእዚህ መልኩ የሚሠራው ሥራ የትምህርት ብክነትን እንደሚቀንስ ገልጸዋል ። ለልጆች ምላሽ ሰጪ እንክብካቤና የቀዳማይ የመማር ዕድል ማግኘት እንዲሁም የመጫወቻ ቦታዎችና በሥራ ምክንያት ከወላጆቻቸው ጋር መዋል ለማይችሉ ልጆች ማቆያዎችን ምቹ ማድረግ ወሳኝ እንደሆነም አስረድተዋል።

አያይዘውም እድሜያቸው ከሦስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ከሚጠበቀው የእድገት በታች እንዳይሆኑ በተሠራው ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ ከሦስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት የእድገት ሁኔታ ከ12 ከመቶ ወደ 12 ነጥብ 05 በመቶ ጥቂት መሻሻል ቢኖርም አሁንም መሥራት ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል። በኦሮሚያና ድሬዳዋ በተደረገው መነሻ ጥናት በኦሮሚያ በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩት 19 ነጥብ 9 በመቶ በድሬዳዋ 19 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን አመልክተዋል።

ቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም የትውልድ መሠረት የሚጣልበት መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ከበደ፤ አነቃቂና ምላሽ ሰጪ እንክብካቤ፣ ሥርዓተ ምግብ፣ መልካም ጤንነት፣ የቀዳማይ የመማር ዕድል ለአእምሮ ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በቀዳማይ የልጅነት ጊዜ ልጆች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የአንድ ዶላር ኢንቨስትመንት ከ13 እና 16 ዶላር በእድሜ ዘመን ምላሽ የሚያደርግ መሆኑን የዓለም አቀፍ ጥናቶች ያመለክታሉ ብለዋል።

ከእዚህ አንጻር በአዲስ አበባ ከተማ ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ መሆኑንና በአዲስ አበባ ከተማ የሚሠራው ሥራም ሞዴል መሆኑን አመልክተዋል።

ድሬዳዋ፣ አማራ፣ ሲዳማ ፣ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ኦሮሚያ ክልሎች ልምድ ወስደው መነሻ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዳቸውንና ድሬዳዋና ኦሮሚያ ጥናቱን ማጠናቀቃቸውን አማራ፣ ሲዳማና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ መረጃ ትንተና ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል።

ዶክተር ከበደ እንደገለጹልን፤ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም እንክብካቤ፣ በቂ ሥርዓተ ምግብ፣ ምላሽ ሰጪ አነቃቂ ክብካቤ የቀዳማይ ልጅነት መማር ፣ ለሕጻናት የሚደረግ ጥበቃና ከለላ ማሕቀፎች አሉት። በፖሊሲም የተደገፈ ነው። ለእዚሁ ሥራ 5ሺህ የወላጆች አቅም ግንባታና ሥልጠና ባለሙያዎች ሠልጥነው በሥራ ላይ ይገኛሉ። ባለሙያዎቹ ቤት ለቤት በመሄድ ለወላጆችና አሳዳጊዎች ስለ መልካም ልጅ አስተዳደግ ምክርና ሥልጠና ይሰጣሉ።

ከሦስት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ አጠራጣሪ የእድገት ውስንነት ካጋጠማቸውም ወደ ጤና ጣቢያ ይልካሉ። ጤና ጣቢዎችም የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ይሰጣሉ። በ2015ዓ.ም ይፋ በሆነው ፖሊሲ ማሕቀፍ የተሟላ የሕጻናት ዕድገት እንዲኖር፤ እንዲሁም ሕጻናት በከተማ ደረጃ በእድሜያቸው የሚመጥን የሚጠበቅ የእድገት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማስቻል ነው። አስፈጻሚ ተቋማትም መልካም የልጆች አስተዳደግና አያያዝ ሥርዓት እንዲሰፍን የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You