
የአንድ ሀገር እና ሕዝብን የለውጥ መነሳሳት ትርጉም ወዳለው ለውጥ በማሻገር ሆነ ለውጡን ውጤታማ በማድረግ ሂደት ውስጥ ጋዜጠኝነት ትልቅ አቅም ነው። የለውጥ አስተሳሰቦችን በተደራጀ መንገድ በሕብረተሰቡ ውስጥ በማስረጽ፤ ከዛም ባለፈ የለውጡን ሂደት በተጨባጭ መረጃ በመግራት የማይተካ አበርክቶ እንዳለውም ይታመናል።
ብዙዎች እንደሚያስቡት እና እንደሚያምኑት የጋዜጠኝነት ሙያ ወቅታዊ መረጃዎችን ሰብስቦ፣ መርጦ እና አደራጅቶ ለማኅበረሰቡ ማቅረብ ነው። ይህ ሙያዊ ተልዕኮው የማኅበረሰቡን የእለት ተእለት የመረጃ ፍላጎት በማሟላት ላይ የተመሰረተ፤ ከውልደቱ ጀምሮ በዋነኛነት እያከናወነው ያለው ተቀዳሚ ተግባሩም ይሄው ነው።
ይህ ግን የሙያዊ ተልዕኮው አልፋ እና ኦሜጋ አይደለም፤ በተለይም አሁናዊ በሆነው ዓለም ካሉ የተለያዩ ፍላጎቶች አኳያ በአንድም ይሁን በሌላ ሙያው ለነዚህ ፍላጎቶች የተገዛ ነው። ዛሬ ላይ ያለ የትኛውም የመገናኛ ብዙሀን ተቋም የሚገራበት ተልዕኮ እና ከተልዕኮው የሚመነጭ ፍላጎት አለው። ለዚያ ፍላጎት ተገዥ በሆነ ፖሊሲ ስለመመራቱም የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በተለይም መረጃ ሁለንተናዊ አቅም እየሆነ በመጣበት በዚህ የዲጅታል ዘመን፤ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የመገናኛ ብዙሀኑን፤ መረጃ ከመሰብሰብ እና መርጦ አደራጅቶ ከማሰራጨት ባለፈ፤ የሀገራቱ ሕዝቦች እራሳቸውን ችለው ትናንትን ለመሻገር የሚያደርጉትን ጥረት ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማስቻል ሂደት ውስጥ ከፍያለ ኃላፊነት አለባቸው።
የሕዝባቸውን ተለውጦ የመገኘት መሻት ወደ ተጨባጭ የለውጥ አቅም በመለወጥ ሆነ፤ የለውጡን ሂደት በለውጡ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ቅኝት በመግራት ከተገማችም ሆነ ተገማች ካልሆኑ ፈተናዎች ለውጡን መታደግ የሚያስችል ሕዝባዊ ዝግጁነት መፍጠር፤ ለዚህም የለውጥ ኃይል ሆነው መንቀሳቀስ የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በብዙ ፍላጎቶች፤ በተቃርኖ ውስጥ በሚጓዘው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ ሀገር እና ሕዝብ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን፤ ብሔራዊ ጥቅሞች ተጠብቀው የሚሄዱበትን፤ የሕዝብ ፍላጎት ልዕልና አግኝቶ ገዥ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ አስተሳሰቦች መሰረት የሚሆንበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ለዚህ የሚሆን ሙያዊ ግርዘት ያስፈልጋቸዋል።
ከተለመደው የሙያ ትርክት ወጥተው፣ ተጨባጭ ዓለም አቀፍ አሁናዊ ሙያዊ እውነታዎችን መሰረት ያደረገ፤ የሕዝባቸውን እውነተኛ መሻት ተጨባጭ ወደሚያደርግ ሙያዊ አበርክቶ የሚወስድ መታደስ፤ ለዚህ የሚሆን የእውቀት ሽግግር ያስፈልጋቸዋል። ሙያዊ አበርክቷቸውም የሚመዘነው ከዚሁ እውነት በሚመነጭ ስኬት ነው።
እንደ ሀገር እኛ ካለንበት የለውጥ የታሪክ ምዕራፍ ሆነ ለውጡ እያጋጠመው ካለው ውስጣዊ እና ውጪያዊ ፈተና አኳያ ጋዜጠኝነትን እንደ አንድ የለውጥ መሳሪያ ልንጠቀምበት፤ ለዚህ የሚሆን ሙያዊ ዝግጁነት ልንፈጥር ይገባል። ይህንን ማድረግ ከጋዜጠኝነት ሥነምግባርም ሆነ መርኅ ጋር በተቃርኖ መቆም ሳይሆን ሙያውን ለሕዝብ ፍላጎት ስኬት አቅም አድርጎ መጠቀም ነው።
ለውጡ በሕዝባችን ሁለንተናዊ ፍላጎት የተመሰረተ ከመሆኑ አኳያ፤ የሕዝብ ፍላጎት ልዕልና አግኝቶ ገዥ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ አስተሳሰቦች መሰረት የሚሆኑበትን አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር፤ ብሄራዊ ጥቅሞች በማስጠበቅ፤ ለውጡን ከውስጥ እና ከውጪ ፈተናዎች ከመታደግ አኳያ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል የሜሄዱበትን ለዚህ የሚሆን ሙያዊ ማስተካከያ ያስፈልጋቸዋል።
በተለይም የመላው ሕዝባችን ሁለንተናዊ የልብ መሻት ሰላም ከዚህ የሚመነጭ ሀገራዊ ልማት እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ሀገራዊ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት በብዙ የሚጠበቅባቸው ሕዝባዊ ኃላፊነት ነው። ይህ መንግሥት እና የመንግሥትን ሥርዓትን ከመደገፍ እና ከመቃወም ያለፈ፤ የሀገርን ዛሬዎች ከትናት ስብራት የማከም እና ነገን ብሩህ የማድረግ ሀገራዊ ራዕይ አካል መሆን ነው!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም