ክሬምሊን፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስሜታዊነት እየታየባቸው ነው አለ። ሩሲያ ይህን ያለችው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰሞኑን የሩሲያውን አቻቸውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በኃይለ ቃል መናገራቸውን ተከትሎ ነው። ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ክፉኛ እንደተበሳጩ ተናግረው ነበር፡፡ ትራምፕ በሩሲያ ድርጊት ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸው፤ ጠንከር ባለ እና ባልተለመደ ተግሳጽ ፑቲንን ‹‹ምን ነካው? ብዙ ሰዎችን እየገደለ ነው›› ብለዋል። ኃይለ ቃላትን ተጠቅመው ወርፈዋቸዋል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በአንድ ሌሊት ከተፈጸሙት ጥቃቶች ሁሉ ከፍተኛው ነው በተባለውና ሩሲያ 367 ያህል ድሮኖችና ሚሳኤሎችን ተጠቅማ በፈጸመችው ጥቃት፣ በጥቂቱ 13 ሰዎች ሲገደሉ፤ በርካቶች እንደቆሰሉ ተዘግቧል። የዩክሬን አየር ኃይል ሩሲያ 298 ድሮኖችንና 69 ሚሳኢሎችን መተኮሷንና ከእነዚህም ውስጥ 266 ድሮኖችንና 45 ሚሳኢሎችን ማክሸፉን አስታውቆ ነበር፡፡
ትራምፕ በኒውጀርሲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ፑቲንን ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ፤ እንግባባለን፤ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሮኬቶችን ወደ ከተሞች እያስወነጨፈ ሰዎችን እየገደለ ነው። በጭራሽ የምወደው ነገር አይደለም” ብለዋል። አክለውም “የተወሰኑ ግዛቶችን ብቻ ሳይሆን መላዋን ዩክሬንን መጠቅለል እንደሚፈልግ ሁልጊዜም እናገር ነበር። ምናልባትም ይህ ትክክል ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። ነገር ግን ይህንን ካደረገ ሩሲያን ወደ ውድቀት ይመራታል” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ የሆኑት ድሚትሪ ፔስኮቭ ትራምፕ ያሰሙት ንግግር “በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች የሚያንፀባርቁት ስሜታዊ ጫና ነው” ብለዋል። ፔስኮቭ ሩሲያ በዩክሬን ያደረሰችው የአየር ድብደባ ዩክሬን የሩሲያ ማህበራዊ መሠረተ-ልማት ላይ ላደረሰችው ጥቃት የተሰጠ ምላሽ እንደሆነም ገልጸዋል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ የአየር መቋቋሚያው በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች 20 የዩክሬን ድሮኖችን መመከት ችሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ “ሩሲያ የወሰደችው የአየር ድብደባ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ትንታኔ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ፑቲን እና ሩሲያ ጦርነቱን ለመቀጠል እና ነፍስ ለማጥፋት የሚያደርጉት ነው” በማለት ጥቃቱን ኮንነዋል።
ዘለንስኪ አክለውም፤ ሩሲያ ከድርጊቷ እንድትቆጠብ የአሜሪካ ጫና አስፈላጊ እንደሆነ በአፅንዖት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ “ያለ አሜሪካ ጠንካራ ግፊት ይህ የሩሲያ አሰቃቂ ጥፋት ሊቆም አይችልም፡፡ የአሜሪካና የሌላው ዓለም ዝምታ ፑቲንን እያበረታታ ነው፡፡ ማዕቀቦች በትክክል ያስፈልጋሉ” ብለዋል፡፡
አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማክበድ እያሰቡ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ “በርግጠኝነት!” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የዩክሬን አውሮፓውያን አጋሮች በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ቢያዘጋጁም፤ አሜሪካ በበኩሏ የሰላም ድርድሮችን ለማሳለጥ እንደምትሞክር እና ይህ ፍሬያማ ካልሆነ ራሷን ከአሸማጋይነት ሚናዋ እንደምታስወጣ ስትናገር ቆይታለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም