
ሩሲያና ዩክሬን አንድ ሺህ የጦር እስረኞችን ለመለዋወጥ ተስማሙ። የዩክሬን መከላከያ ሚንስትር ረስተም ኡሜሮቭ እንዳስታወቁት፤ ሩሲያና ዩክሬን በሁለቱ ሀገራት መካከል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ትልቁን የጦር እስረኞች ልውውጥ ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ፤ይህ ስምምነት የስብሰባው ቁልፍ ውጤት መሆኑን በመጥቀስ፤ የልውውጡ ቀን መወሰኑን ነገር ግን በዚህ ደረጃ ሊገለጽ እንደማይችል ጠቅሰዋል።
ውይይቱ በተኩስ አቁምና በእስረኞች ልውውጥ ላይ አትኩሮት መደረጉን አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት አንድ ሺህ እስረኞችን በአንድ ሺህ እስረኞች ለመለዋወጥ ተስማምተናል ብለዋል። የሩሲያ ልዑካን ቡድን መሪ ቭላድሚር ሜዲንስኪ በበኩላቸው፤ ከዩክሬን ጋር በተደረገው ውይይት ሞስኮ ደስተኛ መሆኗን ገልጸው፤ ውይይቶቹ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ የሩሲያና የዩክሬን ልዑካን ባደረጉት ስብሰባ መሠረታዊ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኙ ሲሆን ባለሥልጣናቱ ውይይት ለማድረግ በቱርክ ኢስታምቡል ሲገናኙ ሳይጨባበጡ ነው ወደ ታቀደው ንግግር የገቡት። በጦርነት ላይ የሚገኙት ሀገራት የሚያደርጉት ውይይት ጉልህ የሆነ ውጤት ያመጣል ተብሎ ባይጠበቅም ትልቅ ርምጃ መሆኑን ተንታኞች ተናግረዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ውይይቱን እያስተባበሩ ያሉት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀካን ፊደን እና ሌሎችም ባለሥልጣናት ናቸው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር “በተቻለው ፍጥነት” መገናኘት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ፑቲን ከቱርክ እና ከዩክሬን አመራሮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው ትራምፕ ፑቲንን ማናገር የሚፈልጉት።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀካን ፊደን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአፋጣኝ መድረስ የሚኖረውን ጠቀሜታ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል። ዩክሬን ቅድሚያ የምትሰጠው የውይይቱ ግብ ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠለት የተኩስ አቁም መሆኑን አስታውቃለች። ሩሲያ በበኩሏ ግቧ ዘላቂ ሰላም ማምጣት እና “ችግሩን ከሥሩ መንቀል” መሆኑን ይፋ አድርጋለች።
ተንታኞች እንደሚሉት ሩሲያ ያላት የተኩስ አቁም ፍላጎት ሳይሆን የጦርነቱ መነሻ የሆነውን ምክንያት መቅረፍ ይሆናል። ይህም ከዩክሬን ሉዓላዊ ሀገር ሆና መቀጠል ጋር የሚጻረር ይሆናል። የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ማኅበርን (ኔቶ) መቀላቀልም አትችልም። እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሊቀበሉ አይችሉም።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ማርኮ ሩቢዮ በቱርክ በሚካሄደው የዩክሬን እና የሩሲያ የሰላም ድርድር ብዙ ተስፋ እንደሌላቸው መግለጻቸው ይታወሳል። ለውጥ እንዲመጣ ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን መገናኘታቸው አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል። ሩቢዮ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን አመራሮች ጋር በኢስታንቡል ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የዩክሬን አጋር የሆኑ ምዕራባውያን ሀገራት ሩሲያ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንድትመጣ ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ መስጠት እንደሚቀጥሉ እና በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉም አስታውቀዋል። ዩክሬን እና ሩሲያ ወደ ውይይት ጠረጴዛው ከመምጣታቸው አስቀድሞ የሚደርሱበት ስምምነት ቅድመ ሁኔታ ያለው ይሁን ወይንስ ቅድመ ሁኔታን ከግምት የማያስገባ በሚለው ላይ የተለያየ አቋም አንፀባርቀዋል።
ትራምፕ በውይይቱ ላይ አለመኖራቸው የሚጠበቀውን ያህል ድርድሩን ፍሬያማ እንዳይሆን ያደርጋል የሚልም ግምት አለ። ዜሌንስኪ “ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተኩስ አቁም” ለማድረግ ሩሲያ የማትስማማ ከሆነ “ፑቲን ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት የለውም” ብለው እንደሚወስዱት ተናግረዋል።
ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር ዜሌንስኪ ቢገናኙም ፑቲን በዚህ መድረክ አለመኖራቸው ውይይቱ የሚኖው ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተንታኞች ገልጸዋል። ቱርክ ውይይቱን “በ360 ዲግሪ” የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመመራት ውይይቱን እንደምታሳልጥ አስታውቃለች ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም