ከእያንዳንዱ ወሳኝና ታሪካዊ መታጠፊያ /critical juncture/ ማግስት መዋቅርና ተቋም ወይም ድርጅት ይመሠረታል፤ ይከለሳል፤ ይበረዛል፤ ይከስማል። ዝቅ ብዬ የዘረዘርኋቸው አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ከአንደኛው፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነቶችና ከቅኝ ግዛት መንኮታኮት በኋላ የተመሠረቱ ናቸው። የመንግስታቱ ማህበ/ሊግ ኦፍ ኔሽን/፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም፣ የዓለም የንግድ ድርጅት፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶ፣ የሶቭየት ሕብረትና የምሥራቅ አውሮፓ ሶሻሊስት ሀገራት ጎራ ትብብር/ዋርሶ/፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የቡድን 7 ሀገራት፣ የቡድን 20 ሀገራት፣ አስያን፣ የሻንጋይ ኮኦፕሬሽን፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት ወይም ኢጋድ፣ ኮሜሳ፣ ሳዳክ፣ ኤኩዋስ፣ ብሪክስ፣ ወዘተረፈ እንዲሉ። የዛሬ መጣጥፌ ትኩረት ብሪክስ /BRICS/ ላይ ስለሆነ በቅድሚያ ሰሞነኛና ተያያዥ ጉዳዮችን ወይም ግጥምጥሞችን ላነሳሳ።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ለብሪክስ አባልነት ኦፊሴላዊ ጥያቄ ማቅረቧን ነግሮን ብዙም ሳንቆይ፤ ላለፉት ሶስት አመታት ትከተለው የነበረውን የማለዘብ የውጭ ግንኙነት ጊዜያዊ መርህን እልባት ሰጥታ ወደ መደበኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ መመለሷን ሰሞኑን ገልጾልናል። ወዲህ የአሜሪካው ኢንቨስትመንት ባንክ ጎልድማን ሳክስ በሚቀጥሉት 50 አመታት የብሪክስ አባል ከሆኑ ሀገራት ቻይናና ሕንድ አሜሪካንን ቀድመው እንደ ቅደም ተከተላቸው በኢኮኖሚያቸው ዓለምን ይመራሉ ሲል ይተነብያል። ኢትዮጵያም በ6 ነጥብ 2 ትሪሊየን ዶላር ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት 17ኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ ባንኩ አክሎ ጠቁሟል።
ይህን ተስፋ የሰነቀች ሀገር አበክራ ብሪክስን ለመቀላቀል ማመልከቷ ተገቢ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን አርቆ አስተዋይነት ወይም ስትራቴጂካል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ደጅ ስትጠና ሶስት አስርት አማታትን ላሳለፈች ሀገር፤ አሜሪካ ኢፍትሐዊ በሆነ አግባብ ከአጎዋ ወይም AGOA /The African Growth and Opportunity Act/ ማለትም ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ሀገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ ከሚያስችል ዕድል ለታገደች ሀገር፤ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዋ ከዓለም ባንክና ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ልታገኘው የነበረ ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍና እርዳታ በአሜሪካና በምዕራባውያን በመታገዱ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ላለች ሀገር ቢሪክስን ለመቀላቀል መወሰን ይበል የሚያሰኝ ውሳኔ መሆኑ በልኩ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል። ለመሆኑ ይሄ ለብልጽግና ለእድገት ስትራቴጂካዊ መነሻም መውጫም የሆነው ብሪክስ ማን ነው።
“ብሪክስ” ወይም “BRICS” የሚለው ምህጻረ ቃል በማደግ ላይ ያሉ የአምስት ሀገራትን ስብስብ የሚወክል ነው። የየሀገራቱን የመጀመሪያ ሆሄ በመውሰድ የተፈጠረ መጠሪያ ነው። ‘B’ን ከBrazil ፣ ‘R’ን ከRussia ፣ ‘I’ን ከIndia ፣ ‘C’ን ከChaina በመጨረሻም ‘S’ን ከSouth Africa በመውሰድ “BRICS”የሚለው ስያሜ ተመሠረተ። መጠሪያው የተፈጠረው በ2001 ዓ.ም ጂም ኦኔል በተባለ የኢኮኖሚክስ ጠበብት ሲሆን እነዚህ ሀገራት በ21ኛው መክዘ በዓለም ኢኮኖሚ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሚሆኑ ተንብዮ ነበር። ከ22 አመታት በኋላ ዛሬ ያረጋገጥነው ትንበያው ጠብ ያላለና ትክክለኛ ሆኖ መሆኑን ነው።
የብሪክስ ሀገራት በተለያየ የጆኦግራፊ ክልል የሚገኙ ሲሆኑ፣ የሕዝብ ብዛታቸው ከ3 ቢሊየን በላይ ወይም ከዓለማችን ሕዝብ 40 በመቶውን የያዙ፤ ከዓለማችን መሬት ወይም የብስ 26 በመቶ የሚሸፍኑ፤ ከዓለማችን ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት 23 በመቶ ድርሻ ያላቸው ናቸው። የተመሠረተበት ዋና አላማ በሀገራቱ መካከል ትብብር ለመፍጠርና ለመመካከር ነው። እርስ በርስ ለመነገድ፣ ኢንቨስት ለማድረግና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማሳለጥ የተቋቋመ ስብስብ ነው። በየጊዜው በመደበኛነት በመሰባሰብ ስለ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ቀጣይነት ስላለው ልማት፣ ስለዓለማቀፍ አመራርና ጸጥታ ይመክራሉ። ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ።
ብሪክስ ከተቋቋመበት አላማ አንዱ ብሪክስ ባንክ የተሰኘ አዲስ ባንክ ማቋቋም ነው። ባንኩ ለአባል ሀገራቱ ሆነ ለሌሎች ለመሠረተ ልማት ግንባታ እና ቀጣይነት ላላቸው ልማቶች ብድር ያቀርባል። በአሜሪካና በምዕራባውያን ቅድመ ሁኔታዎችና እጅ ጥምዘዛዎች ስር ከወደቁት የዓለም ባንክና ዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ተጽዕኖ በመላቀቅና አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኢነርጂ፣ ጤናና ትምህርት ላይ በስፋት የመስራት ዕቅድ አለው። በሀገራቱ መካከል ትብብርንና የልምድ ልውውጥን ለማሳለጥ የጋራ ፎረም መመስረቱን ሰነዶች ያወሳሉ።
በአባላቱ መካከል መተባበርና መደጋገፍ እንዳለ ሁሉ ተግዳሮቶችና ልዩነቶችም አሉ። እያንዳንዱ ሀገር የየራሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ባህሪ ያለው መሆኑ የመጀመሪያው ተግዳሮት ሲሆን የጋራ ፍላጎት የሚንጸባረቅበት ወይም የየሀገራቱ ፍላጎት በእኔ እብስ በእኔ እብስ የሚሳሳቡበትና የሚራኩቱበት መድረክ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትም አለ። ጂኦፖለቲካው ውጥረት፣ የንግድ ግጭቶችና የሚከተሉት የኢኮኖሚ ሥርዓት ለስብስቡ አንድነት ስጋቶች ናቸው።
ያም አለ ይህ ብሪክስ በማደግ ላይ ላሉት አምስት ሀገራት ድምጽም መድረክም ነው። ስጋታቸውን የሚያሳስቡበት፣ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ በዓለማቀፍ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተገቢውን ስፍራና ትኩረት እንዲያገኙ የሚጠይቁበት የጋራ መድረክ ነው። ለዚህ ይሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 41 ሀገራት የአባልነት ማመልከቻቸውን ይዘው የተሰለፉለት። መልሱን ወደፊት የምናገኘው ይሆናል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ባለፈው ሳምንት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥል እና ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን አሳውቀዋል። አሁን እየተለወጠ ባለው የዓለማችን ሁኔታ እና ከዓለም የአሰላለፍ አንጻር ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ የሚረዱ ዓለም አቀፍ ተቋሞች አባል እንድንሆን እንሠራለን። ከእነዚህ አንደኛው ብሪክስ ነው። የአባልነት ጥያቄው ቀርቧል። ብሪክስ ከኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ በጎ ምላሽ እንደሚሰጠን እንጠብቃለን። ብሔራዊ ጥቅሞችን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋርም መሥራታችንን እንቀጥላለንም። ቻይና እና ሩሲያ ለጥያቄያችን ድጋፍ መስጠታቸውን አምባሳደር መለስ ዓለም አስታውቀዋል።
እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ቱርክ እና ግብፅ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። ጥያቄ ከማቅረብ ውጭ እስካሁን ቀዳሚዎቹን አምስት ሀገራት ለመቀላቀል የቻለ ሀገር ግን የለም ይለናል የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ቢቢሲ። ከአፍሪካ አልጄሪያን እና ግብፅን ተከትሎ የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረባቸውን በይፋ ካሳወቁ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ሦስተኛዋ ሆናለች። እስካሁንም ስብስቡ ለቀረቡለት የአባልነት ጥያቄ የሰጠው ምላሽም ሆነ፣ ሊሰጥ ስለሚችለው ውሳኔ ምንም ፍንጭ አላሳየም።
የብሪክስ አባል ሀገራትን ከፖለቲካ ይልቅ ምጣኔ ሃብት እንዳስተሳሰራቸው ተደጋግሞ ታይቷል። ከሰሞኑ የአባል ሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በደቡብ አፍሪካ ተገናኝተው ነበር። በዚህ ወቅትም ዓለም በምዕራባዊያን ከሚዘወረው ሥርዓት መውጣት እንዳለባት አንስተዋል። የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር፤ ቡድኑ በጂኦፖለቲካ ውጥረት፣ በእኩልነት አለመኖር እና በደኅንነት ስጋት ውስጥ ላለው ዓለም መሪ ሃሳብ ይዞ መቅረቡን ገልጸዋል። የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ሱብራህማንያም ጃይሻንካር ስብስቡ ዓለም ባለብዙ መልክ ስለሆነች ባረጀው መንገድ አዲሱን አጀንዳ መፈጸም አይቻልም። ከምንጋፈጣቸው ችግሮች አንዱ የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ሲሆን ብዙ ሀገራት በጥቂቶች በጎ ፈቃድ እንዲኖሩም ሆነዋል ብለዋል።
የብሪክስ ጥያቄ የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንድ ሰበዝ ነውና ስለ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ከተነሳ አይቀር አቶ መሐሪ ታደለ ማሩ (ፒኤችዲ)በአንድ ወቅት በአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ካስነበቡን የተወሰነውን ላጋራ ወደድሁ። ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላት ተሳትፎና የውጭ ፖሊሲዋ እ.ኤ.አ በ2002 ሥራ ላይ ባዋለችው የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራተጂ ላይ የተመሠረተ ነው። በቅርቡ ያጋጠሟት ውስጣዊ ግጭቶች ቢኖሩም አገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ቁልፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናት። በክፍለ አኅጉሩ ውስጥ መረጋጋት በመፍጠር በኩልም ወሳኝ ሚና አላት። የኢትዮጵያ መንግሥት በወሳኝ መልኩ ኢጋድና የአፍሪካ ኅብረት በመሳሰሉት ባለብዙ ዘርፍ ኤጀንሲዎች አማካይነት በክፍለ አኅጉሩና በአኅጉሩ ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ ያደርጋል።
በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድም እንደ አንድ የሚታመን አደራዳሪ ይታያል። ይህ ሚናውም ባለው ተነጻጻሪ ወታደራዊ አቅምና በአካባቢው የሰላም ደኅንነት እርምጃዎችና እንቅስቃሴዎች ውስጥ በሚያደርገው ቋሚ ተሳትፎ፤ ሽብርን በመቋቋም ረገድ ያለው አቅምና ተነሳሽነት፤ የአፍሪካዊነት ውርሱና ባለብዙ ዘርፍ መድረኮችን አሟጦ የመጠቀም አቅሙ የመሳሰሉት ባህርያት እንዲዳብሩ አድርጓል። በአንጻሩ አሳሳቢ የዴሞክራሲ አለመዳበር፣ በጎሳ የተመሠረተ ፖለቲካው፤ ሙስና፣ ሕገ መንግሥታዊ ተጠያቂነት የዳኝነት ቁጥጥርና የፓርላማ ክትትል ውስንነት ያለበት መሆን፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የጠና ድህነት የመሳሰሉት ለውስጣዊ ደኅንነት ትልቅ ሥጋት የሆኑ ውስጣዊ ችግሮችም አሉት።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በወሳኝ መልኩ የሚመሠረተውም ለእነዚህ ውስጣዊ ሥጋቶች በሚሰጠው ግብረ መልስ ላይ ነው። ሽብርና የጎረቤት አገሮች ያላቸው የተስፋፊነት ፖሊሲዎች፤ በዓባይ ዙሪያ ከግብፅ ጋር ያለው የተጠቃሚነት ክርክር የመሳሰሉት ኢትዮጵያ ባላት የሰላምና የማኅበራዊ ዕድገት ጉዞ ላይ ጥላ የሚያጠሉ የውጭና የውስጥ ሥጋቶች ናቸው። የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነትና ስትራቴጂ ፖሊሲው መሠረታዊ መርሆች ከሁለት አሠርታት በኋላም አግባብነታቸው እየታየ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ለውስጣዊ ተጋላጭነት ልዩ ትኩረት ከሚሰጠውና ከሚፈለገው በላይ ወደ ውስጣዊ ጉዳዮች ከሚያየው የውጭ ፖሊሲ ይልቅ ሚዛኑ በጠበቀ መልኩ የውጭ ሥጋቶችን ቀድማ ወደምታመክንበትና ሕጋዊ ተጠቃሚነቷንም ወደምታስከብርበት ፖሊሲ መሸጋገር ይጠበቅባታል። ማመጣጠን ለውጭ ሥጋቶችና ዕድሎች በቂ ትኩረት መስጠትን ይጠይቃል።
ባለፉት አሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ይበልጥ ምክንያታዊና ዓላማ ወዳለው ጠንካራ የአካባቢው የውጭ ፖሊሲ ተሸጋግራለች። በሒደቱም ወሳኝ የአካባቢው ኃይልና በአፍሪካዊ ጉዳዮችም ወሳኝ ሚና ያላት ሀገር ሆናለች። የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ (በተለይም የአካባቢ ዲፕሎማሲዋ) እንደ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ዑጋንዳ ከመሳሰሉት የቅርብ ጎረቤቶቾ ጋር ባላት ግንኙት ዙሪያ የሚያጠነጥንና ብሎም በአፍሪካ ኅብረት፣ በኢጋድና የምሥራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል፤ የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በመሳሰሉት ተቋማት ላይ ካላት የማጠናከር ሚና ላይ ተያያዥነት ያለው ነው።
ካላት የረዥም ጊዜ የነጻነት ታሪክ መነሻነት የተነሳ ኢትዮጵያ ሰፊ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ልምድ ባለቤት ነች። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ /እ.ኤ.አ 1916-1974/ እና የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም /እ.ኤ.አ 1974-1991/ መንግሥታት አሁን እየታዩ እንዳሉት የውጭ ሥጋቶች ዓይነት ያጋጠሙዋቸው ቢሆኑም ውስጣዊ ችግሮቻቸው ግን የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን መንግሥትን በማስወገድ እ.ኤ.አ በ1991 ሥልጣን በተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ሥር በተከታታይ ካሉት መስተዳደሮች ካጋጠሙት በዓይነታቸው ይለያሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ /እ.ኤ.አ 1991-2012/፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ /ከ2012 ጀምሮ/ አስተሳሰብ ላይ ልዩ ግንዛቤ የፈጠሩት እነኚህ ውስጣዊ ጥያቄዎችና ለእነሱ የሚሰጡት መልሶች ናቸው። ሁለቱም መስተዳደሮች ቀድሟቸው ከነበሩት መንግሥታት በተለየ መልኩ ለውስጣዊ የፖለቲካ ለውጦች ትኩረት የሚሰጡና ወደ ውስጥ የሚያዩ መስተዳድሮች ናቸው። እንደ አንድ ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋቱን የመፍቻ ዘዴ በማቀድ የኢሕአዴግ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2002 በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 86 በመመሥረት የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ የደኀንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጿል። የደኅንነት ፖሊሲውና ስትራተጂው ከውጫዊ ሥጋቶችና ተጋላጭነት ይልቅ ለውስጣዊ ደኅንነት፣ ከውጭ ፖሊሲ ይልቅ ለውስጣዊ ኩነቶች ቅድሚያ ይሰጣል። በውጤቱም ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ሊለያዩ በማይችሉበት ደረጃ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በመቅረፅ ረገድ እንዲጣመሩ ተደርገዋል።
ሻሎም ! አሜን
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም