አዲስ አበባ ከተማ ለዘመናት የኢትዮጵያ ስፖርት ማዕከል በመሆን ዘልቃለች፡፡ የሀገሪቱን ስፖርተኞች በከተማዋ እንደ ማግኔት እየሳበ የዘለቀው ስፍራ ደግሞ አዲስ አበባ ስታዲየም ነው፡፡ በእርግጥ የስፖርት ቤተሰቡም ስለ ስፖርት ፍቅር ሲል ከዚህ ስፍራ ሳይርቅ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አንጋፋው ስታዲየም ስፖርትን ብቻም ሳይሆን በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁነቶችንም ሲያስተናግድ የቆየ ስፍራ ነው፡፡
የእግር ኳስ ስፖርትን ለረጅም ዓመታት ተሸክሟል፤ አፍሪካ ዋንጫንና ሌሎች አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ከማስተናገድ አንስቶ የፕሪሚየር ሊጉ እና የበርካታ ውድድሮች ጅማሬ ይኸው ስታዲየም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ ክለቦች ለአሸናፊነት የሚያደርጉትን ትንቅንቅ ያሳዩበት፣ አንጋፋ ተጫዋቾች ተሸኝተው አዳዲስ ትውልዶች የሚተኩበትም ነው፡፡ ድል የቀናቸው ፈንድቀው የተረቱ ያነቡበት፤ ደማቅና አስደማሚ የቡድን ድጋፍ የለመደ ስታዲየምም ነበር፡፡ እርግጥ ነው አስጊ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮችም በየጊዜው መስተዋላቸው አይዘነጋም፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርትም ቢሆን ከጀማሪ አንስቶ ኢትዮጵያን እስካስጠሩ አትሌቶች ድረስ አቅማቸውን የፈተሹበት ስታዲየም ነው፡፡ ከታዳጊ እስከ አዋቂ በስፖርት ፍቅር የተነደፉ የከተማዋ ነዋሪዎች የተመላለሱበት ስታዲየምም ነው፡፡ አሁን ግን ይህ ሁሉ ለአዲስ አበባ የስፖርት ቤተሰብ ትዝታ ነው፡፡ ምክንያቱም በከተማዋ ብሔራዊ ቡድኑን ከተመለከተ፣ ክለቡን ከደገፈ እንዲሁም ሀገር በበጎ ያስጠራውን የአትሌቲክስ ውድድር ካጣጣመ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተለመደው ድምቀትና ለዛ ያለው ድጋፍም ደብዘዝ ማለቱ፤ ደጋፊውም አብዛኛውን ጨዋታ በቴሌቪዥን መስኮት መመልከቱ አልቀረም፡፡ የእግር ኳስም ሆነ የአትሌቲክስ እንዲሁም በሌሎች ስፖርቶች የሚከናወኑ ውድድሮችም አማራጮችን ለማማተር ተገደዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት መናኸሪያ የሆነው ይህ ታሪካዊ ስታዲየም ከስፖርት ወዳዱ ሕዝብ ሊለያይ የቻለው በጥገና ምክንያት ነው፡፡ በተጫጫነው እርጅና እንዲሁም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርትን ባለማሟላቱ ወደ ጥገና የተገባ ቢሆንም፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋም ተጥሎበት ነበር፡፡ ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ጊዜው ተራዝሞ የተነፋፈቁት ውድድሮችና የስፖርቱ ቤተሰቡ ዳግም የመዋሃድ ተስፋን ያገኙት ከሰሞኑ ነው፡፡ ስፖርቱን በመምራት ላይ የሚገኘውና የስታዲየሙ ባለቤት የሆነው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በመጪው ዓመት 2016 ዓ.ም መጀመሪያ የስታዲየሙ ጥገና ተጠናቆ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግን ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
ለመገናኛ ብዙኃን በተዘጋጀው የጉብኝት መርሃ ግብር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸው የተስተዋለ ሲሆን፤ እድሳቱን አስመልክቶም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት የሜዳ ፈሳሽ ማስወገጃና የሳር ተከላ ሥራ፣ የተጫዋቾች መልበሻ ክፍሎችን ጨምሮ የተለያዩ ግልጋሎት የሚሰጡ ክፍሎች፣ የካፍ ቢሮ፣ የሚዲያ ክፍልና የVIP ላውንጅ ሥራዎች፣ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የውስጥ አጥርና የተመልካች መተላለፊያ መንገድ፣ … ሥራዎች በመገባደድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ወቅትም 22ሺ የሚሆኑ የስታዲየሙ ወንበሮች በመገጠም ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህንን ተከትሎም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፤ ግንባታው የተጀመረው ጥገና ለማድረግ ቢሆንም ስታዲየሙ በእርጅና ምክንያት በመጎዳቱ እድሳት እየተደረገለት በመሆኑ ረጅም ጊዜ እንደወሰደ ይጠቁማሉ፡፡ የእድሳቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ሥራም 65 ከመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ደረጃውን በጠበቀ መልክ እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ቀሪዎቹ ሥራዎችም በመጪዎቹ ወራት ተጠናቀው በአዲሱ ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን ለማካሄድ ዝግጁ ይሆናሉ ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
ቀሪው ሥራ የመም እድሳት ሲሆን፤ ለዚህም የሚሆነውን በጀት በእቅድ ተይዞ ለአትሌቶች ዝግጁ ይሆናል፡፡ የቪአይፒ ወንበሮች ገጠማ፣ በማታ ጨዋታዎችን ለማከናወን የሚረዳ መብራት፣ የስክሪን እና የጄኔሬተር ገጠማ፣… በቀጣይም የመኪና ማቆሚያን ጨምሮ በስታዲየሙ ዙሪያ ያሉ ሥራዎች የሚከናወኑ እንዲሁም ጥራቱን በሚመለከት የካፍ ባለሙያዎች የሚታይ እንደሚሆንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015