የስቴም ማዕከላት – ችግር ፈቺ ትውልድ ለማፍራት

ተማሪው “ተማር ልጄ” የሚለውን የወላጅ ምክር ተግባራዊ አድርጎ ላለፉት በርካታ ዓመታት ተማሪ ሆኗል:: በሂደቱም ፊደል ቆጥሯል፤ ሆኖም የትምህርት ሥርዓታችን አስተማሪ መናገር ተማሪ ማድመጥ ላይ ተወስኖ ቆይቷል:: በዚህም አብዛኛው ተማሪ ችግሮችን ከመለየትና ከመዘርዘር ወደ ችግር ፈቺነት ሳይሸጋገር ኖሯል :: ይህ አካሄድ ተቀይሮ ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባሻገር የሚሰጡ ትምህርቶች ችግር ፈቺ እና ተግባር ተኮር እንዲሆኑ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ተደርጓል:: ለዚህም በሀገሪቷ የሚገኙ አብዛኛው ተማሪዎች 70 በመቶ ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ የተቀሩት 30 በመቶ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ መሆን እንዳለባቸው ታምኖ ወደ ተግባር ቢገባም የታሰበውን ያህል ውጤታማ መሆን ሳይቻል ቆይቷል::

ተማሪዎችን በአስገዳጅ ሁኔታ “አንፈልገውም፣ ይከብደናል” ወደሚሉትና ዝንባሌያቸው ወዳልሆነ የትምህርት አይነት ማሠማራት ብዙም ውጤታማ አላደረግም:: ለዚህም በየአካባቢው የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአካባቢው የሚገኙ የሳይንስ ዝንባሌ ያላቸውን ታዳጊዎች የሚደግፉበት አሠራር ተዘርግቶ ቆይቷል:: በሀገራችን በሚገኙ አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሳንይንስ፣ ቴክኖሎጂ ምህንድስናና ሒሳብ (ስቴም) ማእከላት (Science Technology En­gineering & Maths (STEM) ተቋቁመዋል:: በዚህም በርካታ ተማሪዎች ሃሳቦችን ከማሰላሰል ባሻገር በተግባር የተፈተሸ መፍትሄዎችን ወደማመንጨት ተሸጋግረዋል::

በትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የኮሚኒቲ ኢንጌጅመንትና ሀገር በቀል እውቀት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ሰላም አለሙ የስቴም ማእከላቱን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ማቋቋም ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በአካባቢያቸው የሚገኙ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን እንዲደግፉና ተማሪዎቹ 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ለሳይንስ ያላቸው ፍላጎት እንዲጨምርና ወደ ዘርፉ ለመግባት እንዲያግዛቸው ነው:: ተማሪዎቹ ውሏቸው ከሳይንቲስቶች ጋር በመሆኑ የእነሱን እውቀት፣ ክህሎት እንዲሁም ላብራቶሪዎቹን ይጠቀማሉ፤ ይህም ወደ ዘርፉ እንዲሳቡ ያደርጋል:: በማእከሉ ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍላጎትና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ታቅፈው አስፈላጊው እገዛ ይደረግላቸዋል::

በዋናነት የስቴም ማእከሎቹ ዓላማ ተማሪዎች ለሳይንስ ያላቸው ፍላጎት እንዲጨምርና በትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ ነው ። በዚህም በማእከሎቹ የሚሰለጥኑ የታቀፉ ተማሪዎች በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ላይም ሁሉንም ተማሪዎች የማሳለፍ ሁኔታ ስላለ ጥሩ እየደገፉ ይገኛሉ:: ከዚህ በተጨማሪ ሥራ ፈጠራ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተማሪዎች አሉ::

በስቴም ፓወር ኢትዮጵያ ኃላፊ ዶክተር ስሜነው ቀስቅስ እንደሚሉት፤ ድርጅታቸው በዋናነት የሚሠራው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪንግና ሒሳብ የተግባር መማሪያ ማእከላትን በማቋቋም ተማሪዎች የተግባር ትምህርት እድል እንዲያገኙ ማድረግ ነው:: ተማሪዎቹ ተግባር ተኮር የሆነውን ትምህርት ካገኙ በኋላ የተማሩትን ሥልጠና መነሻ አድርገው የአካባቢ ችግር በመለየት ችግሩን በቴክኖሎጂ ከማቃለል ባሻገር ድርጅቶችን በመክፈት ሀብት እንዲፈጠሩ ያስችላቸዋል::

በሀገራችን የስቴም ማእከል ከተጀመረ 15 ዓመታት የተቆጠረ ሲሆን በዚህም 65 ማእከላት ማቋቋም ተችሏል:: አብዛኞቹ ማእከላት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አገልግሎት ይሰጣሉ:: በማእከላቱ እስካሁን ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተጠቅመዋል:: በየዓመቱ ማእከላቱ ተጠቃሚ ሆነዋል:: በማዕከሉ ሥልጠና ካገኙ በኋላ የአካባቢን ችግር የፈቱበትን ፕሮጀክት ለሀገር አቀፍ መድረክ ይዘው ይቀርባሉ:: ባሳለፍነው ሳምንት ዓለምአቀፉን የሳይንስ ቀን ምክንያት በማድረግ የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ሥራዎች ውድድርና አውደርዕይ ለዘጠነኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል::

ተማሪ ዘላለም ዘማች በጋዱላ ዞን ሜታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ያለፈውን ክረምት ያሳለፈው ከመኖሪያ ቤቱ በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው:: የክረምት ቆይታው ሲጠናቀቅ አብረውት ከሚማሩ 157 ተማሪዎች መሃል በማሸነፉ ለሀገራዊ የሳይንስ ቀን የፈጠራ ሥራውን እንዲያቀርብ ተመርጧል::

“ከዚህ ቀደም ስለኮዲንግ ምንም አናውቅም ነበር::” የሚለው ተማሪ ዘላለም በሚማርበት ትምህርት ቤት ኮምፒዩተር እንደሌለ ይናገራል:: በሁለት ወር ቆይታው ግን ስለኮምፒዩተርና ኮዲንግ ተረድቷል:: ተማሪ ዘላለም ለሀገር አቀፍ ውድድር ያስመረጠው ፈጠራው ሰውን ተክቶ እህል የሚያበጥር ማሽን በመሥራቱ ነው:: በንግድ ሥራ ቤተሰቡን የምታስተዳድረው እናቱ ተሯሩጣ ለቤተሰቡ ገቢ የምታመጣበትን ሰዓት እህል በማበጠር እየወሰደባት ስትቸገር በማየቱ ፈጠራውን ለመሥራት መነሳሳቱን ይናገራል::

የስቴም ማእከላቱ ከሚገኝባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው:: በዩኒቨርሲቲው የስቴም ማእከል ዳይሬክተር አለሙ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት ፤ በማእከሉ ወደ ዘጠነኛ ክፍል የሚያልፉ ተማሪዎች ተወዳድረው እንዲገቡ ይደረጋል:: እስከ 12ኛ ክፍል የሳይንስ ትምህርቶች (ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባይሎጂ፣ ሒሳብ) በተጨማሪም የእንግሊዝኛና የአይቲ ትምህርቶችን ይማራሉ:: በየዓመቱ ከስምንት ወደ ዘጠነኝ ካለፉት ውስጥ 50 ተማሪዎችን በመቀበል አገልግሎት ይሰጣል :: በዚህም በየአመቱ ከ190 እስከ 200 ተማሪዎችን ያስተናግዳል ::

ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ ካምፕ ውስጥ ካሉ ተማሪዎች በተጨማሪ በሌሎች ትምህርት ቤት ያሉና ፕሮጀክት የመሥራት ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ግብዓት በማቅረብና ለሚሠሯቸው ፕሮጀክቶች አማካሪ በመመደብ እንዲሠሩ ይደረጋል:: በተጨማሪም ከአምስተኛ ክፍል እስከ 11ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በሰመር ካምፕ (በክረምት ትምህርት መርሃ ግብር) ተቀብለን እናስተምራለን ያሉት ዶክተር አለሙ፤ በመደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር ሁሉም በንድፈ ሃሳብ የሚሰጥ በመሆኑ አብዛኞቹ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት እድልን አያገኙም:: ወደ ማእከሉ መምጣታቸው የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል:: ይህም ከሳይንስ ጋር የበለጠ ቁርኝት እንዲኖራቸው አግዟቸዋል ይላሉ:: በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚገኙ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ የተግባር ትምህርትን ለመሥራት እጥረት ሲገጥማቸው በተመረጡ የቤተ ሙከራ ሥራዎች ላይ ወደ ማእከሉ እየመጡ እንዲሠሩ ይደረጋል:: በአቅራቢያው ለሚገኙ መምህራንም ሳይንስን በቀላል መንገድ ማስተማር እንዲችሉ ሥልጠና ይሰጣል::

በስቴም ማእከላት ባሉ ተማሪዎች በግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝምና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተለያዩ ችግሮችን ይለያሉ የሚሉት ዶክተር ሥሜነው፤ ተማሪዎቹ ለለዩት ችግር በቴክኖሎጂ መፍትሄ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል:: በየማእከላቱ የተሠሩት ፈጠራዎች በየአካባቢው ተወዳድረው አሸናፊዎች ለሀገር አቀፍ ውድድር ይቀርባሉ:: በሀገር አቀፉ መድረክ ከመወዳደር ባለፈ እርስ በእርስ ልምድ ይለዋወጣሉ፤ በጋራ በመሆን ሌላ ፕሮጀክት እንዲሠሩም እድል ይፈጠራል:: በሀገር ደረጃ አሸናፊ የሚሆኑት በቀጣይ በአህጉር አቀፍ መድረክ ሀገራቸውን ወክለው የሚወዳደሩበት እድል እየተመቻቸ መሆኑን ጠቅሰዋል::

ተማሪ ሊድያ ጋሻው በሐረር ከተማ የጀግኖች መታሰቢያ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪ ናት:: በሐረር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለሚገኘው ስቴም ማእከል ከጓደኛዋ ሰምታ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ መጠቀም እንደጀመረች ትናገራለች:: በማእከሉም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን አይታለች:: ማየት ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንደሚቻልም ተምራበታለች:: እሷም በሌሎች ያየችውን ችግር የመፍታት ጅማሮ ወደ ራሷ በማምጣት “ዲጂታል አግሪካልቸር ሞኒተሪንግ ሲስተም” ስትል የሰየመችውን ችግር ፈቺ ፈጠራ ሠርታለች:: ፈጠራዋ ለተተከሉ እጽዋት በራሱ ውሃ ያጠጣል:: የሙቀትና የቅዝቃዜ ሁኔታንና ሌሎችም አስፈላጊ መረጃዎችን በስልክ ይልካል:: “የሚተከሉ እጽዋት ስንቶቹ ጤንነታቸው የተጠበቀ ይሆናል?” ብላ የምትጠይቀው ተማሪ ሊድያ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ውሃ ስለማያገኙ አብዛኞቹ እንደሚደርቁ ትናገራለች:: ለዚህ ችግር እሷ የሠራችው ፈጠራ መፍትሄ መሆኑን ታምናለች:: የሷ ፈጠራ የሚያስፈልገውን ያህል ውሃ የሚያጠጣ ሲሆን የሙቀት፣ የውሃ መጠንን ጨምሮ ማንኛውም ለእጽዋት የሚያስፈልገውን ግብዓት መስተካከል ያረጋግጣል፤ እንዲሁም መረጃውን እጽዋቱን ለሚከታተለው ሰው በእጅ ስልክ አማካኝነት ይልካል::

እንደ ዶክተር ስሜነው ገለጻ በስቴም ማእከላቱ በተማሪዎች የሚሠሩት የፈጠራ ሥራ በናሙና ብቻ እንዳይቀር መነሻ ገንዘብ በመስጠት ምርቱ ወደ ገበያ እንዲገባ የሚደረግበት ማእቀፍ አለ:: ከዚህ ባለፈም የ21ኛው ክፍለዘመን ክህሎት የሚባሉት የዲጅታል ሥልጠናዎች፣ የሥራ ፈጠራ (ኢንተርፕርነርሽፕ) ፣ የሂሳብ አስተዳደር (ፋይናንስ አድሚንስትሬሽን) እና መሰል ሥልጠና ለፈጣሪዎቹ ይሰጣሉ:: የተቋቋሙት ላብራቶሪዎች በሰባቱም ቀናት ለሃያ አራት ሰዓት ክፍት ሆነው ተማሪዎቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ቢፈለግም የአንዳንድ ተቋማት ላቦራቶሪዎች ለተማሪዎቹ ምቹ አይደሉም ይላሉ::

ማእከላቱ በአንዳንድ ቦታዎች ቅዳሜና እሁድ መምህራን እረፍት ነው በማለት የማይገቡበት ሁኔታ መኖሩን የሚያነሱት ዶክተር ስሜነው፤ የስቴም ማእከላቱን ሙሉ በሙሉ ያለመጠቀም ሁኔታ መኖሩን ያነሳሉ:: የተቋቋሙት የስቴም ማእከላት የታሰበላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋመበት ትምህርት ቤት፣ የትምህርት ቢሮ ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስደው እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል:: ላቦራቶሪዎቹ በፈረቃ አገልግሎት እንዲሰጡና በርካታ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢታሰብም፤ ለክትትል ሥራ ወደማእከላቱ ሲሄዱ በአንዳንድ አካባቢዎች ላቦራቶሪዎቹን ተማሪዎች የማይጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል። ተማሪዎች በላቦቹ በተገቢው መንገድ ቢገለገሉ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል::

በዩኒቨርሲቲው ስቴም ማእከል ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ዘጠነኛ ክፍል ሲገቡ ጀምሮ የነበራቸው የመቀበል አቅም፣ ነገሮችን የሚያዩበት የዕይታ አድማስ እናውቀዋለን የሚሉት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስቴም ማእከል ዳይሬክተር ዶክተር አለሙ፤ በሂደት የክፍል ደረጃዎችን ሲሻገሩ የሚታዩት ዕይታዎች በሙሉ ይቀየራሉ ይላሉ:: እንዲሁም አመለካከታቸው፣ ለትምህርት ፣ ለፈጠራ ሥራ ያላቸው መረዳት እና ሳይንስን የሚረዱበት ብሎም የሚያውቁበት አቅም እንደሚያድግ ይናገራሉ::

እንደ ዶክተር አለሙ ማብራሪያ ፤ የዩኒቨርሲቲው ስቴም ማእከል ለሰባት ዙር የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎችን አስፈትኗል። በዚህም ሁሉንም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ማሳለፍ ችሏል:: ይህም ማእከሉ የተማሪዎችን አረዳድ የተሻለ እንዲሆን ማገዙን ያሳያል:: ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የገቡ ተማሪዎች ስቴም ማእከሉን እንደሚያመሰግኑ ይገልጻሉ:: የዚህ ምክንያትም በማእከሉ ችግሮችን እንዴት መወጣት እንዳለባቸው መማራቸውና ነገሮችን በቀላሉ እንዴት መሥራት እንደሚችሉ በመማራቸው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ስኬታማ እንዲሆኑ አግዟቸዋል:: ከሀገር ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በተጨማሪ በርካቶች በውጭ ሀገራት ነጻ የትምህርት እድሎችን አግኝተዋል::

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You