ከቀናት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀ ዜና የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ቆይቷል:: ‹‹ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 738 ሚሊዮን ዶላር ለደቡብ ሱዳን ብድር ሰጠች›› የሚለው ዜና እንደተሰማ እንዴት ኢትዮጵያ ይህንን ማድረግ ቻለች? የዶላር እጥረት ያለባት ሀገር ይህንን ማድረጓ አግባብ ነው ወይ? የሚሉት ነጥቦች መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተዋል::
ሆኖም የአስተሳሰብ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ለሌላው ለመትረፍ እና ለማበደር የሚያንሳት ምንም ነገር የለም:: ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጨበጥ፣ የሚታይ፣ ለውጥና እድገት አለ። በዚህ በያዝነው ዓመት 8.4 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ ጠበቅ ያለ እቅድ ተይዟል። ባለፉት ሦስት ወራት የታዩትም አፈጻጸሞች የሚያመላክቱት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜያት ከራሷ አልፋ ለሌለችም መብቃት እንደምትችል ነው::
ግብርናን ብንወስድ፤ ግብርና ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ውጤት የታየበት ዘርፍ ነው:: ቀደም ሲል ክረምት እና ዝናብ ተጠብቆ ሲሠራበት የነበረው የግብርና እንቅስቃሴ አሁን ወቅት የማይገድበው ሆኗል:: በዚህም ምክንያት ሰብል፣ ጥጥ፣ ሆርቲካልቸር ተደምሮ ክረምት ከበጋ ሠላሳ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 1.4 ቢሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል::
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የሌማት ትሩፋት በርካታ ውጤቶች እየታዩበት ነው:: ሌማት (በአርቴፊሻል አስምሌሽን) በጣም በርካታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች የማዳቀል ሥራ ተሠርቷል። ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ 26 ሚሊዮን ጫጩቶች በዚህ ዓመት 150 ሚሊዮን ጫጩት የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው::
በሌላም በኩል በዚህ ዓመት 12 ቢሊዮን ሊትር ወተት፤ 218 ሺህ ቶን የዶሮ ሥጋ እንደምናገኝ ታቅዷል፣ 8 ቢሊዮን እንቁላል፤ 297ሺህ ቶን ማር እንደሚገኝ ይታሰባል:: ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ከማገዙም በሻገር ወደ ውጭ በመላክም የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይጫወታል::
በቡና የተገኘውም ውጤት የኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ ብሩህ መሆኑን የሚያመላክት ነው:: ኢትዮጵያ ከብራዚልና ከቬትናም ቀጥሎ ሦስተኛዋ ትልቅ ቡና አምራች ሀገር ለመሆን በቅታለች። ባለፈው ዓመት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ከቡና ኤክስፖርት አግኝተናል። በዚህ ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠበቃል።
ዘንድሮ ከአራት መቶ ሀምሳ እስከ አምስት መቶ ሺህ ቶን ድረስ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዟል። አራት መቶ ሀምሳ ሺ ቶን ማለት የዛሬ አምስት ዓመት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርት አራት መቶ ሀምሳ ሺህ ቶን አይሞላም ነበር። ይህ እድገት በቡና ብቻ ሳይሆን በሻይም ምልክት መታየት ተጀምሯል። ሻይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በስፋት ተተክሏል በጣም አስደናቂም ውጤት እየተገኘበት ነው።
ስንዴን በሚመለከት ሦስት መቶ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በዚህ ዓመት እንደሚመረት ይጠበቃል:: ጤፍ ከ600ሚሊዮን ኩንታል በላይ እንደሚመረት መሬት ላይ ያለው የማሳ አያያዝ ያስታውቃል::
በርካታ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ምርት መግባታቸው እና አንዳንዶቹም በአፍሪካ ገበያ የማፈላለግ ሥራ ውስጥ መግባታቸው የኢትዮጵያ ምርቶች በቀጣይ የአፍሪካን ገበያ እንደሚያጨናንቁት ይጠበቃል::
ማዕድን በሚመለከት በወርቅ፣ በብረታ ብረት፣ የድንጋይ ከሰል አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ይጀምራሉ:: በርካታ የወርቅ ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ ይገባሉ:: ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ ባለፉት ሦስት ወራት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱ ብዙዎችን ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ እንደሚያበረታታቸው ይጠበቃል::
ሲሚንቶ ብንወስድ የለሚ ሲሚንቶ ብቻ በዓመት 450 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ያመርታል:: አሁን ያለውን የሲሚንቶ ምርት 16 በመቶ እድገት ሀገር ውስጥ ያመጣል:: እነዚህ ፋብሪካዎች በተሟላ አቅም እየሠሩ ሲሄዱ የኢንዱስትሪው እና የማዕድን ዘርፉ ተደምሮ ከፍተኛ እመርታ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል::
የአገልግሎት ዘርፉም ቢሆን እድገቱ በጣም አመርቂ ነው:: የኢትዮጵያ አየር መንገድን ብቻ ብንወስድ አሁን ያለውን አቅም በብዙ እጥፎች የሚያሳድጉለትን ሥራዎች እያከናወነ ነው:: በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ በአፍሪካ ሁለተኛ የሆነውን አየር መንገድ በእጥፍ የሚበልጥ አቅም እየፈጠረ ነው:: 124 አውሮፕላን ማዘዝ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለን ኤርፖርት ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ተሳፋሪዎች በዓመት ማስተናገድ የሚችል ቢሆንም፤ በቂ ስላልሆነ ከ100 እስከ 130 ሚሊዮን ተሳፋሪዎች ማስተናገድ የሚችል ኤርፖርት ለመገንባት ጥናት ተጠናቋል:: ይህም በአፍሪካ ግዙፉ ኤርፖርት ያደርገዋል::
ከውጭ ንግድ ገቢም በሦስት ወር ውስጥ የተገኘው 1ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው:: ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ከመሆኑም በሻገር ሀገሪቱ የምትልካቸው ምርቶች በአይነትም ሆነ በመጠን መጨመራቸውን ያሳያል:: የምርቶቹ ተቀባይነት እያደገ መምጣቱም ያመላክታል::
በአጠቃላይ ለመስጠት እንጂ ለመቀበል የተፈጠረች ሀገር አይደለችም:: ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም የሰጠች፤ ሉሲን ለዓለም ሕዝብ ያበረከተች፤ በዓለም ላይ አንዲትም ቅንጣት ታክል ውሃ ሳትወስድ ለጎረቤቶቿ 12 ወንዞችን የምታበረክት፤ ሥልጣኔን ያስተማረች፤ ሕይወታቸውን በየጊዜው በሚሰዉ ጀግኖች አማካኝነት ለጥቁር ሕዝቦች ፋና ወጊ የሆነች ሀገር ነች:: ስለዚህም ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ ሰጪ እንጂ ተቀባይ ልትሆን አትችልም::
እነዚህ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተረጂነት ተላቃ እራሷን በምግብ እንደምትችል አመላካቾች ናቸው:: መንግሥት ‹‹ተረጂነት ይብቃ›› በሚል መርሕ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ከተመፅዋችነት ለማላቀቅ አዲስ ዕቅድ ይዞ መጥቷል::
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 250 ሺ ሄክታር በማረስ ኢትዮጵያ በቂ እህል ለማምረትና ከእርዳታ ተቀባይነት ለመላቀቅ አቅዳለች:: ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከእርዳታ እሳቤ እራሱን ማውጣትና እራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል:: ሁሉም እርዳታ መቀበልን ከተጸየፈ ኢትዮጵያ ከተረጂነት ወደ ሰጪነት የምትሸጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም