አብዛኛው ሕዝቧ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኑሮው በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመሰረተባት ኢትዮጵያ ከቀደመው ጊዜ አንስቶ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች፡፡ በመንግሥትና በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች የተደገፉ ተከታታይነት ያላቸው የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በቀደሙት የመንግሥት ስርዓቶች የተተገበሩት የባለ ብዙ ዘርፍ የግብርና ልማት ማዕቀፍ ፕሮግራም (Comprehensive Agricultural Package Program) እና የግብርና ልማት ኤክስቴንሽን ትግበራ (Extension Program Implementation Department (EPID) እንዲሁም የቅርብ ጊዜዎቹ የኢትዮጵያ የልማት ፕላን መመሪያ ማዕቀፍ፣ የግብርና መር ኢንዱስትሪ ፖሊሲ (Agricultural Development Led Industrialization (ADLI)፣ የዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ ፕሮግራም፣ የመጀመሪያው እና ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች (GTP I እና GTP 2) ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በእነዚህ የግብርና ዘርፍ ማሻሻያ መርሃ ግብሮችም የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን፣ ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሬ ዐሳይቷል፤ቁጥሩ ቀላል የማይባል ማህበረሰብም ከድህነት መላቀቁን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የግብርናና ገጠር ልማትን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ብዙ ባለሀብት አርሶ አደሮችን መፍጠር የቻሉበት ሁኔታ ስለመኖሩም ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት እምቅ አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የስራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ የሰጡ አይደሉም፡፡ አሁንም ግብርናው በዘላቂነት ከኋላ ቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም፤የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎች በርካቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥን እውን የማድረግ ተግባር ብዙ እርምጃዎች ይቀሩታል፡፡
ከሃገራዊ ለውጡ ወዲህ ትኩረት ከተሰጣቸውና ተስፋ ሰጭ ውጤት ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በየአመቱ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል፡፡ ለእዚህም ምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከልም ለስንዴ ልማት የተሰጠው ትኩረትና እየተገኘ ያለው ምርት ነው፡፡
ይህም ስኬት ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን የስንዴ ምርት እንድታሟላ ማድረግ ያስቻለ ከመሆኑም በተጨማሪ ስንዴ ምርት ስኬት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል እንድትመደብ አስችሏታል፡፡ ሀገሪቱ ስንዴን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሏም ሌላው የስንዴ ልማቱ ስኬት ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ይህ ስኬት የዓለም አቀፍ ተቋማት አድናቆትና ምስክርነትም ተችሮታል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ዓመት ከዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ያገኙት ‹‹የአግሪኮላ›› ሜዳሊያ ሽልማት (Agricola Medal) የዚህ ስኬት ምስክር ነው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክም ለኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ስኬት ተደጋጋሚ ምስክርነቶችንና አድናቆትን ሰጥቷል፡፡
በግብርናው ዘርፍ፣ በተለይም በስንዴ ልማት፣ የተገኘው ውጤት በሀገር አቀፍ ደረጃም ለከፍተኛ ሽልማት የበቃ አኩሪ ተግባር መሆን ችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት አምስት የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማትን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መቀበላቸው ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የግብርና ሚኒስቴር ሲሆን፣ ሚኒስቴሩን ለሽልማት ካበቁት ስራዎቹ መካከል ዋናው የስንዴ ልማት ነው፡፡
የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በስንዴ ልማት ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት እውን መሆን የቻለው በመንግሥት ቁርጠኛነት ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት የስንዴ ልማቱ የተጀመረው በመንግሥት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፎለት ነው። የፌዴራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ሀገራዊ ጉዳይ የጋራ ዕቅድ አውጥተው መክረዋል፡፡
መንግሥት ዘርፉን ለማዘመንና ለማስፋት እንደ ማዳበሪያ ላሉት ግብቶች በየዓመቱ በቢሊዮኖች ብር ድጎማ የማድረግ፣ ለሜካናይዜሽን ትኩረት የመስጠት፣ ለሜካናይዜሽን እርሻ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረውን የኩታ ገጠም እርሻ የማስፋፋት ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ይህ ጥረት በየዓመቱ እየጎለበተ መጥቶ ስንዴን በዓመት እስከሦስት ጊዜ ድረስ ማምረትና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በየካቲት 2015 ዓ.ም የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ የመላክ መርሃ ግብርን በኦሮሚያ ክልል፣ ባሌ ዞን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ‹‹ባሌ ላይ ያየነው ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ሂደት ለኢትዮጵያ ማድረግ ከሚገባን ትንሹ ስኬት ነው። ምክንያቱም የምናደርገውንና የምናቅደውን በተግባር በአረንጓዴ ዐሻራና በሕዳሴ ግድብ እያሳየን መጥተናል። አሁን ደግሞ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆም ባለፈ ስንዴን ወደ ውጭ በመላክ ያሰብነውን በተግባር ፈፅመን ለኢትዮጵያዊያንና ለዓለም አሳይተናል። ኢትዮጵያ ከስንዴ እርዳታ መላቀቅና ወደ ውጭ መላክ አትችልም ያሉንን ችለን በማሳየታችን ኩራት ተሰምቶናል። በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እርዳታ ፈላጊ ነው፡፡ ይህ ችግር ይበልጥ በቁጭት ለልማት የሚያነሳሳና ‹ኢትዮጵያን ኤይድ/Ethiopian Aid› በሚል ስንዴ ለመለገስ ተግተን እንድንሠራ የሚያደርግ ነው፡፡ በዓለም ላይ የተፈጠረውን የስንዴ ገበያ ችግር ለማቃለልም ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ትወጣለች›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ወርቃለማሁ ጣሰው በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው የስንዴ ልማት ስራ፣ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ይገልፃሉ፡፡ እሳቸው እንደሚያስረዱት፣ የስንዴ ልማቱ ኢትዮጵያ ያለባትን የስንዴ ምርት እጥረት ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ስንዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ በገበያ ላይ ተፈላጊ ምርት በመሆኑ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትም ትልቅ ሚና አለው፡፡
ስንዴን ለማምረት የሚያስችሉ ብዙ የቴክኖሎጂ አማራጮችም አሉ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ስንዴን በበጋ ወቅት በመስኖ የማልማቱ ተግባር ቀደም ሲል ብዙም ያልተለመደ ስራ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ስንዴን በመስኖ የማልማት ተግባር የሚደነቅና ከዚህም የበለጠ መጠናከር ያለበት ስራ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹ስንዴን በበጋ ወቅት፣ በመስኖ የማምረት ስራ ምርቱ ከእጥፍ በላይ እንዲያድግ አስችሏል፡፡ ይህም ስንዴ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትርጉም ያለው አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በስንዴ አምራችነቷ ተጠቃሽ እየሆነች ትገኛለች›› ይላሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ወርቃለማሁ የስንዴ ልማቱ ጥሩ ውጤት እያስገኘ መሆኑ ባይካድም፣ ‹‹ልማቱን በመንግሥት ትልቅና ቀጥተኛ ድጋፍ የማከናወን አካሄድ የስንዴ ልማቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርገዋል?›› የሚለው ጉዳይ በቂ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ‹‹የስንዴ ልማቱ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረትና ተሳትፎ እየተከናወነ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዚህ ሁኔታ የስንዴ ልማቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሆኖ የመቀጠሉ ጉዳይ ግን ጥያቄን ያስነሳል፡፡
የግል አምራቾች ወደ ስንዴ ልማቱ ስራ መግባት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ ምርቶች ትርፍ ተኮር (Profit-Oriented) ከሆኑ፣ በህብረተሰቡ እና በአምራቹ ፍላጎትና ተነሳሽነት የሚከናወን ከሆነ ስራው ራሱን ችሎ ይቀጥላል ሲሉም አመልክተው፣ በማበረታቻና በመንግሥት ደጋፍ የሚከናወን ከሆነ ብዙ ርቀት ላይጓዝ ይችላል ይላሉ፡፡
ስለዚህ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ እየቀነሰ፣ የክላስተራይዜሽን፣ የቴክኖሎጂ፣ የብድር ተደራሽነትን በመፍጠርና በማመቻቸት ቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ቢቀጥል ባለሃብቶች ያለስጋት ወደ ዘርፉ ገብተው ሊሰማሩ ይችላሉ ፤ምርቱም እያደገ ዘላቂ ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ተሳትፎውን እየቀነሰ የግለሰቦች/የባለሀብቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣት አለበት፡፡ ይህም የስንዴ ምርቱ ከሚጠበቀው በላይ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል›› በማለት ይመክራሉ፡፡
የግል ባለሀብቶች ወደ ስንዴ ልማት እንዲገቡ ወሳኝ ሚና ካላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የመሬት አቅርቦት መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪው፣ መሬት መዘጋጀትና ባለሃብቶች በቀላሉ መሬት የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡ ቢሮክራሲውን ማቅለል እንዲሁም ለባለሃብቶች ማበረታቻዎችን (ብድር ማመቻቸት፣ የግብር እፎታ መስጠት፣ ቴክኒካዊ ድጋፎችን መስጠት…) ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ አምራቹ አማራጭ የገበያ እድሎችን ተመልክቶ እንዲሸጥ መፍቀድ ያስፈልጋል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ስለስንዴ ልማት ስኬቶች ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ‹‹ግብርና ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ መነቃቃት እንዳመጣ ይታወቃል፤ በዚህ ዓመት 6.1 በመቶ እድገት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የግብርና ሴክተር 6.1 በመቶ እድገት ያመጣል ስንል አምና በነበረው መሠረት ቢሆን ይህ ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል።
ስንዴን በሚመለከት የተከበረው ምክር ቤት በደንብ እንደሚያውቀው፣ በቅርቡም ወደ ምርጫ ክልላችሁ ስትሄዱ እንዳያችሁት፣ በዚህ አመት ክረምትና በጋ ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ይሸፈናል። በከፍተኛው ደረጃ በሄክታር አርባ ኩንታል ቢመረት ቁጥሩ ከፍ ይላል። ነገር ግን ቀንሰን ከአርባ በታች እንደሚገኝ አስበን ብንሄድ፣ በዚህ ዓመት ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር በትንሹ ሶስት መቶ ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ይመረታል። ሰላሳ ሺ ቶን ስንዴ ይመረታል ማለት ነው። ሰላሳ ሺ ቶን ስንዴ ማምረት ማለት በአፍሪካ ሁለተኛው አምራች ከሶስት እጥፍ በላይ ማምረት ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ስንዴ አምራች ሀገር ዘጠኝ ሺህ ቶን ገደማ ነው የሚያመርተው። ይህም ማለት ቢያንስ የዚህን ሶስት እጥፍ ምርት እንሰበስባለን ማለት ነው።
ስንዴ እንዴት እየተቀለደበት እንደተጀመረ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፡፡ አሁን ሁሉም የሚቀበለው እየሆነ መጥቷል። ሶስት መቶ ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በዚህ አመት ማሳካት ከቻልን ለዚያ በቂ ገበያና የእሴት መጨመር ስራ ከሰራን ለማሳደግ ያለን አቅም በዚያው ልክ እየሰፋ ይሄዳል። እነዚህ በግብርና ዘርፍ የመጡ ውጤቶች ያገኘናቸውን ድሎች ጠብቀን ስንሰራና የገጠሙንን ድካሞች አርመን፤ አርቀን እያስፋፋን መሄድ ብንችል አሁንም ሰፊ መሬት በጣም ሰፊ ውሃና የሰው አቅም ስላለን የማደግ እድሉ በጣም ሰፊ ነው። በመስኖና በበጋ የማምረት አቅማችንም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ማሸነሪና ፓምፕ መጠቀመም ጨምሯል። ማሽነሪም፣ ምርጥ ዘርም፣ ማዳበሪያም ተጨማሪ ስራ ይፈልጋሉ። እነዚህን በመስራት ሁለት ቁልፍ ተግባራት ከፊታችን እንደ ፈተና ይጠብቁናል። አንደኛ ጥራት፤ ሁለተኛ አምራችነትን ማሳደግ ይገባል›› በማለት ተናግረዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም