ገና ልጅ እያለ ጀምሮ ከሽቦና ከብረት ጋር ቁርኝት ጥብቅ እንደነበረው ያስታውሳል፡፡ ትኩረት ሰጥቶና ሥራዬ ብሎ ባይከታተለውም ከዕድሜ አቻዎቹ ይልቅ ለፈጠራ ሥራ ነፍሱ ታደላ እንደነበር ቤተሰቡን ጨምሮ ጓደኞቹ ይነግሩት እንደነበርም ያስታውሳል፡፡ ህጻናት አፈር ፈጭተው በሚጫወቱበት እሱም እንደ ዕድሜ አኩዮቹ የሽቦ መኪና ይሠራ ነበር፡፡ በወቅቱ የዕድሜ አቻዎቹ ከሚሠሩት መኪና ይልቅ እርሱ የሚሠራው የሽቦ መኪና አስር እጥፍ የተሻለና አስገራሚ በወቅቱ ጓደኞቹ ይገልጹለት እንደነበርም ያስታውሳል፡፡ ይህ ችሎታው በሰፈሩም ሆነ ከሰፈሩ ውጭ ባሉ ጓደኞቹ ተመራጭ አድርጎት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
በወቅቱ ታዲያ በውስጡ ያለውን እምቅ ተሰጥኦ በቅጡ መረዳት ባይችልም፣ ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ ውስጣዊ ፍላጎትና ተሰጥኦውን እየተረዳ በመምጣቱ ለትምህርት ትኩረት በመስጠት አሳድጎታል፡፡
በትምህርት የዳበረውን ውስጣዊ ፍላጎትና ተነሳሽነቱን አጣምሮ የአምራች ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው እንግዳችን አቶ አይሸሽም ጥላሁን ይባላል፡፡ አቶ አይሸሽም የ‹‹ኤቲደብሊው›› ማሽነሪ አምራች ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው ደብረማርቆስ ከተማ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ንጉስ ተክለኃይማኖት ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ደብረማርቆስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው፡፡
አቶ አይሸሽም፤ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጥ ቤተሰብ የተገኘ መሆኑ ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እንዲማር እንዳደረገው ይናገራል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ያገኘ ሲሆን፤ ባገኘው የውጭ አገር የትምህርት ዕድልም እንዲሁ ሁለተኛ ዲግሪውን ከባርሴሎና፣ ስፔን በ‹‹ፐርሰናል ፋብሪኬሽን (ዲጅታል ፋብሪኬሽን)‹‹ አግኝቷል፡፡ ይህን ትምህርቱን ከውስጥ በመነጨ ጥልቅ ፍላጎት ደስ እያለው እንደተማረም አጫውቶናል፡፡ ፐርሰናል ፋብሪኬሽን ወይም ዲጂታል ፋብሪኬሽን የሚባለው ትምህርት በዋናነት በብዛት ማምረት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሳይሆን፤ ሰዎች ደስ ያላቸውን ማንኛውንም ነገር ማምረት እንዲችሉ የሚፈቅድ እንደሆነ አቶ አይሸሽም ይገልጻል፡፡
ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ አገር ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት ደስ እያለው የተከታተለው ትምህርት ዛሬ የተለያዩ የግብርና፣ የጽዳት፣ የጨርቃጨርቅ፣ የኮንስትራክሽንና ሌሎች የተለያዩ የማምረቻ መሳሪያዎችን ማምረትና ማባዛት አስችሎታል፡፡ በውስጡ የሚንቀለቀለውን የፈጠራ ሥራ ፍላጎት በተለያየ መንገድ አውጥቶ ለመጠቀም ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ከውጭ አገር የትምህርት ዕድል በተጨማሪ በአገር ውስጥም የተለያዩ ዕድሎች አጋጥመውታል፡፡ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም በመቻሉም ለስኬት እንደበቃ የሚናገረው አቶ አይሸሽም፤ ከትምህርት ቤት እንደወጣ በዳን ቴክኖክራፍት ሊፍት አምራች ድርጅት ውስጥ ለሁለት ዓመት ተቀጥሮ ሠርቷል፡፡ ከሁለት ዓመት የቅጥር ሥራ በኋላ ግን ከጓደኞቹ ጋር የተለያዩ ጥናቶች በማድረጉ በርካታ ክፍተቶችን ማስተዋል ችሏል፡፡ ክፍተቶችን ለመድፈንም ችግር ፈቺ የሆኑ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እያመረተ ይገኛል፡፡
በፈጠራ ሥራዎቹ በተደጋጋሚ ተወዳድሮ ማሸነፍ የቻለው አቶ አይሸሽም፤ በፈጠራ ሥራዎቹ ህንድ አገርም የመሄድ ዕድል ገጥሞታል፡፡ የሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ትምህርቱን በተለይም በባርሴሎና በብዙ ልፋትና ጥረት በተግባር መማር የቻለ ሲሆን፤ ትምህርቱም በመላው ዓለም ከሚገኙ ተማሪዎች ጋር በመሆኑ ብርቱ ፉክክር የነበረው እንደሆነ ያስታውሳል፡፡ ያም ቢሆን ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ወደ አገር ቤት በተመለሰ ጊዜም ትልቅ ራዕይ ሰንቆ በከፍተኛ ተነሳሽነት ለውጥ ለማምጣት አቅዶ የነበረ ቢሆንም ብዙ ደንቃራዎች ታግለውታል፡፡
ሁለተኛ ዲግሪውን በስፔን መንግሥት ወጪ የተከታተለው አቶ አይሸሽም፣ ይህን እድል ላመቻቸላት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ዓመት የማስተማር ግዴታ ነበረበት፡፡ ይህን ግዴታውን ለመወጣት በዩኒቨርሲቲው እሱ ተምሮት የመጣው ሙያ የትምህርት ክፍል ፕሮግራም ባለመከፈቱና የተለያዩ ግብዓቶች ባለመሟላታቸው ሳቢያ በዩኒቨርሲቲው ማስተማር አልቻለም፡፡ እርሱ ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የፈጠራ ሥራዎቹን በመሥራት የራሱን ድርሻ ለመወጣት ያደረጋቸው ከፍተኛ ጥረቶች ሁሉ ፍሬያማ ሆነው ውጤታማ እንዳደረጉት አጫውቶናል፡፡
መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያድግበትን የተለያየ መንገድ እያመቻቸ እንደሆነ የሚናገረው አቶ አይሸሽም፣ ለእዚህም የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከማምረቻ መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ በግሉ ፈቃድ ሳያወጣ ጀምሮ ከጓደኞቹ ጋር የሽመና ማሽን እና የተለያዩ መሳሪያዎችን ሲያመርት ጥቂት የማይባሉ ድጋፎችን ከመንግሥት ማግኘቱን ይገልጻል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ያልተሠሩ በርካታ ሥራዎች ስለመኖራቸው ይጠቁማል፡፡
አቶ አይሸሽም በ2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ ይተላለፍ በነበረው የፈጠራ ሥራ ውድድር ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ በወቅቱ ለውድድር ይዞ የቀረበው ማሽን የሽመና ሥራን በቀላሉና በፈጠነ መንገድ መሥራት የሚያስችል፤ የሸማኔዎችን ጊዜና ጉልበት የሚቀንስ፤ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር ነው፡፡ በወቅቱ ውድድሩን በማሸነፉ ከተበረከተለት 150 ሺ ብር ተሸራርፎ የቀረውን 80 ሺ ብር እንዲሁም ከመንግሥት ያገኘውን መጠነኛ የማምረቻ ቦታ ተጠቅሞ ኤቲ ደብሊው ማኑፋክቸሪንግን መመስረት ችሏል፡፡
በጥረቱ ያገኘውን ዕድል ተጠቅሞ ከሽመና ማሽን በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖችን ማምረት የጀመረው አቶ አይሸሽም፤ ወደ ገበያው ለመግባትም ቢሆን ብዙ ጥረት ማድረግን አልጠየቀውም፡፡ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለሥራው ጥራት አቅሙን በሙሉ አሟጦ መጠቀም በመቻሉ ነው፡፡ ‹‹ሰው ከሠራ ለሥራው ጥራት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት›› የሚል ጠንካራ እምነትም አለው፡፡ ይህ አመለካከቱ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት እንዲችልና ውጤታማ እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራል፡፡
መነሻውን በሽመና ማሽን ያድርግ እንጂ ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችን የሚሠራው አቶ አይሸሽም፤ የሰራው የሽመና ማሽን ለሸማኔው በስፋት ተደራሽ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ በሚፈለገው ልክ ሊሄድለት ስላልቻለ የሽመና ማሽን ማምረቱን ገታ በማድረግ በሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ማምረት ስራ በመሰማራት የደረቅ ሳሙናና ዲተርጀንት ፈሳሽ ሳሙና ማምረቻ፣ የቆዳ ውጤቶችን ማምረት የሚያስችሉ፣ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚሆኑ ክሬሸርና እንዲሁም ለግብርና ጠቃሚ የሆኑ ማሽኖችን በማምረት ብዙዎች ዘንድ ተደራሽ መሆን ችሏል፡፡
‹‹ኤቲ ደብሊው ማኑፋክቸሪንግ የተለያዩ ማሽኖችን በማምረቱ በአንድ አይነት የማሽን ምርት አይታወቅም›› የሚለው አቶ አይሸሽም፤ በሁሉም የማሽነሪ ምርቶች በየእለቱ እድገትና ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉንም ይናገራል፡፡ ውጤት እያስመዘገበና እያደገ የመጣው ኤቲ ደብሊው ማኑፋክቸሪንግ ቀድሞ ካገኘው የማምረቻ ቦታ የተሻለ ስፋት ያለው ቦታ ተወዳድሮ ማግኘቱንም ይጠቅሳል፡፡
መንግሥት በማኑፋክቸሪን ዘርፍ ለተሰማሩና ቢታገዙ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላሉ፤ ተኪ ምርቶችን ያመርታሉ በሚል ባዘጋጀው አገር አቀፍ ውድድር የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላት የቻለው ኤቲ ደብሊው ማኑፋክቸሪንግ፣ አገር አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ ውድድሩ አሸናፊ በመሆን ሰሚት አካባቢ 500 ካሬ ሜትር የተገነባ እንዲሁም ማስፋፋያ መሥራት የሚያስችል ተጨማሪ ቦታ ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ ከመንግሥት ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ትልቅ ድጋፍና ማበረታቻ በማግኘቱ መንግሥትን የሚያመሰግነው አቶ አይሸሽም፤ ሌሎችም ብዙ ጥረት የሚያደርጉና ጥቂት እገዛ ቢያገኙ ብዙ መሥራት የሚችሉ ስለመኖራቸው ተናግሯል፡፡
ኤቲ ደብሊው ማኑፋክቸሪንግ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የሚያመርታቸውን ማሽኖች እያሳደገ ከመሄዱ በተጨማሪ ለሠራተኞቹ የተለያዩና በመደበኛው ትምህርት የማያገኙዋቸውን አይነት ስልጠናዎች እንደሚሰጥም ይገልጻል፡፡ በተለይም በውጭው ዓለም ያገኘውን ዕውቀት ስልጠና በመስጠት ለሠራተኞቹ እያጋራ መሆኑን ይናገራል፡፡ አብዛኞቹ ሠራተኞች ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ የወጡ እንደመሆናቸው ያላቸውን መሰረታዊ እውቀት ተጠቅመው ተጨማሪ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት እንዲችሉ ትልቅ እገዛም ያደርጋል፡፡ ለአብነትም ብዙ እንጀራ በአንድ ጊዜ መጋገር በሚያስችለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንጀራ ፕሮጀክት ላይ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው አብሲት ማውጣት የሚያስችል ማሽን ዲዛይን ሠርተው አስረክቧል፡፡
‹‹ሁሉም ነገር ከቻይና መምጣት የለበትም›› የሚለው አቶ አይሸሽም፤ መሰል የፈጠራ ሥራዎችን መንግሥት እንዲያበረታታም ጠይቋል፡፡ ወሳኝ ከሆኑ ምርቶች ውጭ ያሉት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀድ እንደሌለበት ሲያስረዳም አብዛኛዎቹ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እዚሁ በአገር ውስጥ መሠራት የሚችሉ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ የሆኑ ምርቶች በአገር ውስጥ መመረት እንዲችሉ ሲደረግ ጠቀሜታው ድርብ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት ባለፈ ምርቶቹን በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው አበርክቶ እጅግ የላቀ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ሃብትን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ሃብቶች ስለመኖራቸው የጠቀሰው አቶ አይሸሽም፤ በአንድ ወቅት ተግባራዊ የሆነውን 70/30 የትምህርት ፖሊሲ ለዘርፉ የሰው ኃይል ልማት አስተዋፅኦ አድርጓል ብለው የሚያምኑት አቶ አይሸሽም፣ ፖሊሲው ምን ደረጃ ላይ ነው ብሎ መፈተሽ ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ መንገድ የሰው ኃይሉን ወደ ሥራ ለማስገባትም አምራች ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በተለይም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከማምረት ባለፈ እንዴት ማምረት እንደሚቻል ዕውቀት በማሸጋገር አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲበራከቱ ማድረግ እንደሚጠበቅም ይጠቁማል፡፡ በዚህ እሳቤ መሥራት ሲቻል ኢንደስትሪው ያድጋል፤ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይላል፡፡
ኤቲ ደብሊው ማኑፋክቸሪንግ ማሽኖችን ሲያመርት በዘርፉ የሰለጠኑ 20 የሚደርሱ ባለሙያዎችን በቋሚነት ቀጥሮ ሲሆን፣ እንደአስፈላጊነቱ በጊዜያዊነት የሚያሰራቸው ሠራተኞችም አሉት፡፡ ባለሙያዎቹ ከተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ሙያቸውን ማሻሻልና ማሳደግ እንዲችሉ ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ድርጅቱ የማሽነሪ ምርቶቹን በሁለት መንገድ ለገበያ ተደራሽ ያደርጋል፤ አንደኛው 85 በመቶ ያህሉን ትዕዛዝ ተቀብሎ ያመርታል፤ 15 በመቶ ያህሉን ደግሞ ጥናትን መሰረት በማድረግ አዳዲስ ማሽነሪዎችን ለማሳያነት እያመረተ ያቀርባል፡፡
ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የማሽነሪ ዲዛይኖችን በመመልከት አብዝቶ ማምረት እንደሚችልም አቶ አይሸሽም ጠቁሟል፡፡ ለአብነትም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በጋራ ያለሙትን የስንዴ መውቂያ ማሽን አምራች ኢንዱስትሪዎች አባዝተው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲያደርጉ ካደረጋቸው መካከል የአቶ አይሸሽም ድርጅት ነው፤ ይህ የመንግስት እርምጃ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና የሚበረታታ መሆኑንም ገልጧል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ስንዴ በስፋት በማምረት ትልቅ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን ጠቅሶ፣ የስንዴ መውቂያ ማሽን ዲዛይኑን ለማባዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አጫውቶናል፡፡
ሁለቱ ተቋማት አንድ ብለው የጀመሩትን ሥራ ማስቀጠል ይቻላል የሚለው አቶ አይሸሽም፤ በተለይም ግብርና ሚኒስቴር እንዲህ አይነት ሥራዎችን መቀበልና ማበረታታት ከቻለ ግብርናውን ማዘመን እንደሚቻል ነው ያመላከተው፡፡ ለዚህም እርሱ በግሉ በዘመናዊ መንገድ ማረስ የሚያስችሉ አነስተኛና ከበሬ ይልቅ ውጤታማ የሆኑ በግፊ የሚያርሱ ስድስት የሚደርሱ ግብርናውን የሚያግዙ የማሽን ዲዛይኖች እንዳሉትም ጠቁሟል፡፡ ቴክኖሎጂውን ከማልማት ባለፈ መጠቀምና ማለማመድ ላይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከቻለ በተለይም ግብርና ሚኒስቴር በዚህ ላይ ፍላጎቱ ካለው ዲዛይኖቹን ወደ ተግባር በማምጣት የተሻለ ሥራ መስራት እንደሚቻል አመላክቷል፡፡
ኤቲ ደብሊው ማኑፋክቸሪንግ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፤ በመደበኛነት በዓላትን ጠብቆ ሰዎች ምግብ እንዲመገቡ ከማድረግ በተጨማሪ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የመሥራት ዕድል ያላገኙ የአካባቢው ልጆች እንዲሰለጥኑና እንዲቀጠሩ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አቶ አይሸሽም ገልጿል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015