የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ ካስጀመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ አንዱ ነው። እአአ በ2021 ግብጽ ካይሮ ላይ የተጀመረው ይህ ውድድር፤ በሊጎቻቸው ሻምፒዮን የሆኑ ክለቦች በየዞኖቻቸው በሚያደርጉት የማጣሪያ ውድድር አሸናፊ በሆኑ ክለቦች መካከል የሚካሄድ ነው። በመጀመሪያው ሻምፒዮንስ ሊግ እንደ ወንዶቹ ሁሉ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውስ የሴቶች ክለብ ዋንጫውን በማንሳት ታሪካዊ ድሉን ማጣጣም ችሏል። የቀጣዩን ውድድር ዋንጫ ያስቀረው ደግሞ የአዘጋጇ ሞሮኮ ክለብ ነበር።
ሦስተኛው የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ኮትዲቯር አዘጋጅነት በተያዘው ዓመት የሚደረግ ይሆናል። የ2024 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ የሆነችው ኮትዲቯር ዝግጅቷን በዚሁ ሻምፒዮና ላይ ለማሳየት እንደሚረዳትም ይጠበቃል። በዚህ ሻምፒዮና ላይ ተካፋይ ለመሆንም በካፍ ስር ባሉት 5ቱ ዞኖች ውስጥ የማጣሪያ ውድድሮች ይደረጋሉ። ኢትዮጵያ የምትካተትበት የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር (ሴካፋ) የዞን የማጣሪያ ውድድሩን በዑጋንዳ አዘጋጅነት ያካሂዳል። በማጣሪያው የሚካፈሉ ክለቦች የምድብ ድልድልም ታውቋል።
በዚህም መሠረት 9 ቡድኖች በሁለት ምድብ ተደልድለው ውድድራቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። የኢት ዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ቡድንም 5 ክለቦች በሚገኙበት የመጀመሪያው ምድብ መደልደሉን አረጋግጧል። በዚህ ምድብም የዑጋንዳው ካምፓላ ክዊንስ፣ የጅቡቲው ኤፍኤዲ፣ የቡሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ እና የደቡብ ሱዳኑ ዬይ ጆይንት ስታርስ ጋር ተመድበዋል። በሁለተኛው ምድብ ደግሞ የታንዛኒያው ጄኬቲ ኩዊንስ፣ የኬንያው ቪጋ ኩዊንስ፣ የሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ እንዲሁም የዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽን የሴት እግር ኳስ ክለቦች ተደልድለዋል። በማጣሪያው አሸናፊ የሚሆነው ክለብም ዞኑን ወክሎ በኮትዲቯሩ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል።
የማጣሪያው ውድድሩም በካምፓላ ከመጪው ነሐሴ 6-18/2015 ዓም የሚካሄድ መሆኑንም በሞሮኮ በነበረው የዕጣ አወጣጥ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የሴካፋ ውድድር ዳይሬክተር ዩሱፍ ሙሲ አስታውቀዋል። በዕጣ አወጣጡ መሠረትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ ጋር እንደሚያደርግ ታውቋል። ቀጣይ የምድብ ጨዋታዎቹንም ከጅቡቲው ኤፍኤዲ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳኑ ዬይ ጆይንት ስታርስ ጋር የሚያከናውን ይሆናል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን ጅማሮውን በሃዋሳ በማድረግ ሁለተኛውን ዙር በባሕርዳር ባካሄደው የዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው። ክለቡ በሊጉ የፍጻሜ ጨዋታ መቻልን 2 ለምንም በመርታት በሰበሰባቸው 61 ነጥቦች ዋንጫውን በተከታታይ ለ3ኛ ጊዜ፤ በሊጉ ታሪክ ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ በማንሳት ደማቅ ታሪኩን መጻፍ ችሏል። የክለቡ አጥቂዎች ሎዛ አበራ እና አረጋሽ ካልሳ ደግሞ በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች መሆናቸው ይታወሳል። ይህም ክለቡ ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ለመሳተፍ በሚያስችለው ማጣሪያ ተካፋይ አድርጎታል።
በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ጠንካራ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ባለፉት ሁለት የሻምፒዮንስ ሊጉ የማጣሪያ ውድድሮች መሳተፉ የሚታወስ ሲሆን ለዋንጫ ተፎካካሪ እስከመሆን የደረሰበት ታሪክ አለው። ያም ሆኖ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። ከሁለት ዓመት በፊት በተሳተፈበት ውድድር እስከ ፍጻሜ የተጓዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኬንያው ቪጋ ኩዊንስ በነበረው ጨዋታ በመደበኛ ሰዓት አንድ እኩል ቢለያይም በተጨማሪ ሰዓት ግብ ተቆጥሮበት ነበር የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ እድሉ የተጨናገፈው። በዚህም አጥቂው ሎዛ አበራ በከፍተኛ ግብ አግቢነት እንዲሁም ሁለተኛ ለወጣበት 20ሺ ዶላር የሽልማት ገንዘቡን ወስዶ ወደ ሃገሩ መመለሱ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ምድቡን በመምራት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ቢችልም በዑጋንዳው ሺ ኮርፖሬት 2ለ1 በሆነ ጠባብ ውጤት በመረታቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ጉዞው ተገቷል። ለደረጃ ባደረገው ጨዋታም የሩዋንዳውን ኤኤስ ኪጋሊን 3ለ1 አሸንፎ ሦስተኛ ሊሆን ችሏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2015