በኮቪድ-19 ምክንያት ከሦስት አመታት በኋላ በበጋ ወራት ውድድር ባለፈው ጥር 07/2015 ተመልሶ በአስር የስፖርት ዓይነቶች በአጠቃላይ 1106 ያሳተፈው የሠራተኞች ውድድር ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፍፃሜ አግኝቷል።
ቀደም ባሉት ሳምንታት በበርካታ የስፖርት ዓይነቶች አሸናፊዎች የተለዩ ሲሆን፣ በፍፃሜው ዕለትም በተወሰኑ ውድድሮች የፍፃሜ ግጥሚያዎች ተከናውነዋል።
በውድድሩ መዝጊያ ዕለት ትኩረት በተሰጠው የወንዶች 1ኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ፍፃሜ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስና ኢትዮ ቴሌኮም ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል። አምስት ግቦች ከመረብ ባረፉበት በዚህ ጨዋታ አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ 3ለ2 በሆነ ውጤት የ2015 የበጋ ወራት ውድድሮች ቻምፒዮን መሆን ችሏል። ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ በተካሄደው የ2ኛ ዲቪዚዮን የወንዶች እግር ኳስ የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ መከላከያ ኮንስትራክሽንን 1ለ0 በመርታት ዋንጫውን ወስዷል።
በ4 መቶ ሜትር የሩጫ አዝናኝ ፉክክር ያደረጉት የኢሰማኮ ሥራ አስፈፃሚና የዘጠኙ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን አመራሮች ውድድር አቶ ተክሉ ሸዋረጋ ቀዳሚ ሆነው ሲያጠናቅቁ፣ የኢሰማኮ ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ 2ኛ፣ አቶ አያሌው አህመድ 3ኛ ሆነው አጠናቀዋል። በስምንት መቶ ሜትር የሴቶች ውድድር ደግሞ መቅደስ ፀጋዬ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን፣ እመቤት ንጉሴ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ፣ ይርጋለም ተክሉ ከንፋስ ስልክ ፔፕሲ ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው ገብተዋል። ጠንካራ ፉክክር በታየበት የወንዶች 5ሺ ሜትር ውድድር መኩሪያ ዳምጠው ከመከላከያ ኮንስትራክሽን በበላይነት ሲያጠናቅቅ፣ አብረሃም አቡና መስፍን አዳነ ከንፋስ ስልክ ፔፕሲ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ጨርሰዋል። በዚህም ንፋስ ስልክ ፔፕሲ አጠቃላይ የአትሌቲክስ አሸናፊ መሆን ችሏል።
አዝናኝ በሆነው የገመድ ጉተታ ውድድር በወንዶች አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የዋንጫ አሸናፊ ሲሆን በሴቶች ብራና ማተሚያ ድርጅት የዋንጫ ባለቤት መሆኑን የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ያደረሱን መረጃ ያመለክታል።
በሠራተኛው የስፖርት መድረኮች የሴቶች ገመድ ጉተታ አሸናፊ የሆነው ብራና ማተሚያ ልዑካን ቡድኑን በሀገር ባህል አልባሳት አስጊጦ የውድድሩ ድምቀት በመሆን በተለየ ይታወቃል። ለበርካታ ዓመታት በሠራተኛው ስፖርት መድረክ ላይ ከብራና ማተሚያ ጋር በሀገር ባህል አልባሳት አጊጣ የምትገኘው ትዕግስት መንበረ፣ ብራና ማተሚያ በዚህ መድረክ ሁሌም የሽብርቅ ዋንጫ ተሸላሚ ከመሆኑ ባሻገር በውድድሮች ብዙ ዋንጫዎችን እንዳሸነፈ ትናገራለች። ዘንድሮም ከሴቶች ገመድ ጉተታ ውድድር በተጨማሪ በወንዶች የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር አሸናፊ መሆኑን በማስታወስ ብራና ማተሚያ በሠራተኛው ውድድር በመሳተፉ ሠራተኛውን ከመጥቀም አልፎ ራሱን ማስተዋወቅ እንደቻለ አስተያየት ሰጥታለች። ድርጅቱ ሠራተኛውን ወደ ስፖርቱ መድረክ ለመላክ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ያለችው ትእግስት፣ የሠራተኛው ስፖርት በኮቪድ ምክንያት ለሦስት አመት ተቋርጦ ቢቆይም ሠራተኛው ተነሳሽነቱ ሳይቀንስ እንደተመለሰና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ተናግራለች።
የዘንድሮው የበጋ ወራት የሠራተኞች ውድድር በኮቪድ ምክንያት ከሦስት አመት በኋላ መካሄዱን ያስታወሱት የኢሰማኮ ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍሰሃፂዮን ቢያድግልኝ፣ ጥሩ መነቃቃት የታየበት እንደነበር ተናግረዋል። እንደ አቶ ፍሰሃፂዮን ገለፃ፣ በኮቪድ ወቅት የሠራተኛው ስፖርት ተቋርጦ በመቆየቱ ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ ከመፍጠር አኳያ ክፍተት እንዳይፈጠር ተቋማት አስቸጋሪውን ጊዜ በማስ ስፖርት እንዲያሳልፉ የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ጭምር ብዙ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ያንን አስቸጋሪ ጊዜ አልፎ ሠራተኛው ወደ በጋ ወራት ውድድር ቢመጣም ጥሩ ውድድር ማድረግ ተችሏል። ለስፖርት ፍቅር ያላቸው ሠራተኞችን ወደ መድረኩ በማምጣት ረገድም በርካታ አበረታች ነገሮች ታይተዋል።
ኢሰማኮ ከሰላሳ ዓመታት በፊት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበረው ያስታወሱት ኃላፊው፣ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ አንዳንድ ውድድሮችን ያደርግ እንደነበር ያስረዳሉ። አሁንም ያንን ነገር ለመመለስ ኢሰማኮ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በቅድሚያ ግን የሀገር ውስጥ ሠራተኞችን ማጠናከር ተገቢ በመሆኑ አሠሪዎች ሠራተኛውን ለሚያሰባስቡ እንደዚህ ዓይነት የስፖርት መድረኮች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። «ከበጀት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ አለባቸው፣ በዚህም የሠራተኞችን ማህበርና ግንኙነት ማጠናከር ይገባል፣ ጤንነቱ የተጠበቀ ሠራተኛ አምራች ነው፣ ይህ ደግሞ የሚጠቅመው ለራሱ ለአሰሪው ጭምር በመሆኑ አሰሪዎች ይህን ተረድተው ድጋፍ ሊያደርጉልን ይገባል፡፡ የሠራተኛ ማህበራትም ይህን ነገር መሥራት ይጠበቅባቸዋል» በማለትም አብራርተዋል።
በክረምት ወራት የሚካሄደው ሀገር አቀፍ የሠራተኞች ስፖርት ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ሠራተኞች ከሁሉም አቅጣጫ የሚገናኙበት ነው። ለዚህ ውድድር ብዙዎች ናፍቆት እንዳላቸው የጠቆሙት ኃላፊው፣ በዚህ መድረክ ሠራተኞች የመነጋገር፣ ልምድ የመለዋወጥ፣ማህበራዊ ግንኙነት ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ፍላጎት አላቸው ይላሉ። ይህን ለማጠናከርም ኢሰማኮ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ለዚህ ደግሞ አሰሪዎች ሠራተኛው በስፖርት መሳተፍ መብቱ መሆኑን ጭምር አውቀው ትልቅ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2015