ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለ16ኛ ጊዜ ቻምፒዮን መሆኑን ከወዲሁ አረጋግጧል። በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚሰለጥኑት ፈረሰኞቹ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው ነው የዘንድሮውን ዋንጫ የግላቸው ማድረግ የቻሉት።
ክለቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በሊግ ደረጃ ከተመሠረተ ጀምሮ ለ30 ጊዜያት ዋንጫውን ከፍ አድርጎ በመሳም ቀዳሚው ክለብ ነው። የዘንድሮን ዓመት ጨምሮ ፕሪሚየር ሊጉ በ1990 ዓ.ም በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ውድድር ማካሄድ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ለ16 የውድድር ዓመታት ማሸነፍ ችሏል። ሃዋሳ ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ከጊዮርጊስ ቀጥሎ ሊጠቀሱ የሚችሉ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ናቸው። ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ደግሞ የበኩር የሆናቸውን ዋንጫ ካነሱ ታሪካዊ ክለቦች ተርታ ተሰልፈዋል።
ፈረሰኞቹ የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለሁለት ተከታታይ የውድድር ዓመታት ከፍ በማድረግ ወደር ሊገኝላቸው አልቻለም። የ2014 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ በሊጉ መጠናቀቂያ ቀን ድሉን የግላቸው እንዳደረጉ አይዘነጋም። በዕለቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ከተማን በማሸነፉ እና ተፎካካሪው ፋሲል ከነማ በበኩሉ በድሬዳዋ ከነማ በመሸነፉ አጓጊ ሆኖ የነበረውን የዋንጫ ፉክክር ልማደኛው ክለብ ለ15ኛ የውድድር ዓመት የበላይ ሆኖበታል።
የዓምና ድሉን ለመድገም ይበልጥ ግምት እንዲሰጠው ያደረገው በዘንድሮ የውድድር ዓመት የመክፈቻ ጨዋታ አዲስ አዳጊውን ኢትዮጵያ መድንን 7 ለ 0 በሆነ ፍጹም የበላይነት በማሸነፉ ነበር። በመክፈቻው ጨዋታ ባስመዘገበው ድል የዋንጫው ቅድመ ግምት መሰጠቱ ስህተት እንዳልሆነ ማስመስከርም ችሏል። በዚህም በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው የቅርብ ርቀት ተፎካከሪውን ባህርዳር ከተማን በስድስት ነጥቦች በልጦ የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለዘውድ ሆኗል።
ጊዮርጊስ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው በ29ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መርሃ ግብር ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በመርታት ነው። ፈረሰኞቹ ቻምፒዮን ሲሆኑ በ29 ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻሉት 63 ነጥቦች ይዘው ነው። ይህም አምና ፕሪሚየር ሊጉን ሲያሸንፉ በ30 ጨዋታዎች ከሰበሰቧቸው አጠቃላይ ነጥቦች በሁለት ያነሰ ነው። በዚህም መሠረት አምና ቻምፒዮን ለመሆን በ30 ጨዋታዎች 65 ነጥቦችን ሲሰበስቡ ዘንድሮ በ29 ጨዋታዎች 63 ነጥቦችን መሰብሰብ ችለዋል። በዘንድሮው የውድድር ዓመት በ29 ጨዋታዎች 53 ግቦችን አስቆጥሮ የተቆጠረበት ጎል ብዛት ደግሞ 20 ነው። ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በተቃራኒ መረብ ያስቆጠረ ግብና የተቆጠረበት ከፍ ብሎ ይታያል። በ2014 ዓ.ም የውድድር ዓመት በ30 ጨዋታዎች በተቃራኒ መረብ ላይ 50 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ተቆጥረውበታል። ዘንድሮው በ29 የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች 53 ግቦችን አስቆጥሮ 20 ግቦች ተቆጥረውበታል። ይህም የሚያሳየው ከአምናው ጋራ ሲነጻጸር የተቆጠሩበት ግቦች በዘጠኝ ጨምሯል። የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬም በጥቂቱ እንደተዳከመም ያመላክታል።
ፕሪሚየር ሊጉ ዘንድሮ ከተለመዱት ተፎካካሪ ክለቦች ውጪ አዳዲስ ክለቦችን በማስመልከት የተለየ ነገርን ማሳየት ችሏል። ኢትዮጵያ መድንና ባህርዳር ከተማ በመጨረሻ ዋንጫውን ቢነጠቁም ባላቸው ሀብትና የተጫዋች ጥራት ተፎካካሪ መሆናቸውን አስመልክቷል። ኢትዮጵያ መድን ምንም እንኳን በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ በቻምፒዮኑ ክለብ በሰፊ ውጤት ቢሸነፍም በፍጥነት እራሱን አርሞ እስከ ውድድር አመቱ አጋማሽ ድረስ የሊጉ ክስተትና የጊዮርጊስ ዋንኛ ተፎካካሪ በመሆን የስፖርት ቤተሰብን አስደምሟል። መድን በሁለተኛው የውድድር ዓመት አጋማሽ ቢዳከምም እሱን ተክቶ ባህርዳር ከነማ ከፈረሰኛው ጋር እሽቅድድሙን አስቀጥሎታል። የጣና ሞገዶቹ ዋንጫውን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ማራኪ የሆነ እንቅስቃሴን ማድረግ ቢችሉም ሞገዱ በፈረሰኛው ተቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን መሆኑን አዋጅ ነጋሪ ሳያስፈልገው እራሱ ሊያውጅ ግድ ሆኗል።
ፈረሰኞቹ የ30ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ የመርሃ ግብር ማሟያ ጨዋታቸውን ካደረጉ በኋላ ቻምፒዮን የሆኑበትን ዋንጫና ሌሎች ሽልማቶችን በይፋ የሚረከቡ ይሆናል። ሊጉን በበላይነት በማጠናቀቃቸው ኢትዮጵያን በመወከል በታላቁ ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል። በዚህ መድረክ በተሳትፎ ደረጃ ትልቅ ልምድ ማካበት ችሏል። 13 ጊዜ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ በመሳተፍ ከኢትዮጵያ ክለቦች ቀዳሚው ሲሆን አንድ ጊዜ 16 ውስጥ በመግባት ትልቅ ታሪክ መጻፍ ችሏል። በተጨማሪም በ10 የአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና፣ በ 2 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫና በ3 የካፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በመሳተፍ ግንባር ቀደሙ ኢትዮጵያዊ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2015