አጓጊው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሊካሄድ ወደ አንድ ወር የተጠጋ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። በዓለም አትሌቲክስ የሚመሩ ውድድሮች እስከሚዘጉ ድረስም ሀገራቸውን በቻምፒዮናው የሚወክሉ አትሌቶች አቅማቸውን በመፈተሽ ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እጩ አትሌቶችም በተለያዩ ውድድሮች ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎ የግል ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ከሰሞኑ በስዊዘርላንድ ሉዛን በተካሄደው ዳይመንድ ሊግም በተለያዩ ርቀቶች በርካታ አትሌቶች አስደናቂ አቅማቸውን አስመስክረዋል።
የዳይመንድ ሊጉ ስድስተኛዋ መዳረሻ በሆነችው ሉዛን ከተካሄዱ ውድድሮች መካከል አንዱ 5ሺ ሜትር ሲሆን፤ በዚህም ወቅታዊ አቋማቸውን አሳይተዋል። በዚህ ርቀት በወንዶች በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ኡጋንዳዊውን አትሌት ጣልቃ በማስገባት ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ነበር ያጠናቀቁት። ከእነዚህ አትሌቶች መካከልም በዚህ ርቀት እንዲሁም በ10ሺ ሜትር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በእጩነት የተመረጡ ይገኙበታል። በዓለም ቻምፒዮናው ኢትዮጵያ በምትታወቅበት 10ሺ ሜትር የሰዓት ማሟያ በቀዳሚነት መቀመጥ የቻለው አትሌት በሪሁ አረጋዊ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ነው አሸናፊ የሆነው።
በዓመቱ በተካሄዱ ውድድሮች ምርጥ አቋሙን በማሳየት ላይ የሚገኘው ይህ አትሌት ዳይመንድ ሊጉን ጨምሮ በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና እንዲሁም በስፔን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ላይ አሸናፊ በመሆን ድንቅ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል። የ22 ዓመቱ ወጣት አትሌት በ5 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ሲሆን፤ በ10 ኪሎ ሜትርም በኢትዮጵያ ፈጣን ሰዓት አለው። ባለፈው ዓመት በአሜሪካዋ ዩጂን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዲፕሎማ ቢያገኝም፤ በዚህ ዓመት አቅሙን አጠናክሮ ወደ ውድድር በመመለስ በባትረስ ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና በግሉ እና በቡድን የብር ሜዳሊያን ለሀገሩ ማስመዝገብ ችሏል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስፔን በተደረገው የማጣሪያ ውድድርም በሪሁ 26:50.66 በሆነ ሰዓት በቀዳሚነት ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ይኸውም አትሌቱ በቀዳሚነት ለቡዳፔስቱ ቻምፒዮና በርቀቱ ተሳታፊነቱን ያረጋገጠበት ሆኗል። በሉዛን ዳይመንድ ሊግ ተሳትፎውም በምርጥ አቋም 12:40.45 የሆነ ሰዓት አስመዝግቦ አሸናፊ ሆኗል። የዓመቱን ምርጥ ሰዓት ያስመዘግበው አትሌቱ ዩጋንዳዊውን የወቅቱ የርቀቱ ምርጥ አትሌት ጆሹዋ ቺፕቴጊን በማስከተል ነው። አትሌቶቹ ከወዲሁ ትከሻ ለትከሻ መለካካታቸውም ምናልባትም በዓለም ቻምፒዮናው ሊኖራቸው የሚችለውን ፉክክር አስቀድሞ ተጠባቂ እንዲሆን ያደርገዋል።
ከሁለቱ አትሌቶች ባሻገር የኦሊምፒክ ቻምፒዮናው ሰለሞን ባረጋም በቡዳፔስት 10ሺ ሜትር ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ከሚጠበቁ አትሌቶች ቀዳሚው ነው። ሰለሞን በስፔኑ የማጣሪያ ውድድር ከበሪሁ በአንድ ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት ኢትዮጵያን ከሚወክሉ እጩ አትሌቶች መካከል አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በዳይመንድ ሊጉ በነበረው ተሳትፎም የሀገሩን ልጆች ተከትሎ በመግባት አምስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል። ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትላቸው አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ሰለሞን በዓመቱ በዳይመንድ ሊግ እንዲሁም በዓለም የሀገር አቋራጭ ውድድር ሀገሩን ወክሏል።
እጅግ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፉ ከሚገኙ አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ለሜቻ ግርማም በዚህ ውድድር በ 1ሺ500 ሜትር ተሳትፏል። በዚህ ዓመት ብቻ በ3ሺ ሜትር እና በ3ሺ ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረወሰኖችን የጨበጠው ብርቅዬው አትሌት በሶስት ዳይመንድ ሊጎች በእነዚህ ርቀት ተሳትፎዎቹ ሊረታው የሚችል አትሌት አልተገኘም። በሉዛን 1 ሺ500ሜትር ተሳትፎውም እጅግ ተቀራራቢ በሆነ ሰዓት ኖርዌያዊውን አትሌት ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ከዚህ አንጻር አትሌቱ በቡዳፔስቱ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያውን ከማጥለቅ የሚያቆመው ያለ አይመስልም።
ሌላው ውድድር በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል የተካሄደ ሲሆን ወጣቷ አትሌት ሲምቦ አለማየሁ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች። በቅርቡ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የታየችው ታዳጊዋ አትሌት በተያዘው ዓመት ዳይመንድ ሊጉን ጨምሮ በተለያዩ ውድድሮች ላይ በነበራት ተሳትፎ ወቅታዊውን አቋሟን ብቻም ሳይሆን በርቀቱ የወደፊት ተስፋዋን ጭምር ማስመስከር ችላለች። ከሌሎች ዕጩዎች አንጻር ባላት እጅግ የፈጠነ ሰዓት መሰረትም ለቻምፒዮናው በቀዳሚነት ልትታጭ ችላለች።
በቻምፒዮናው ኢትዮጵያን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሴቶች ለመወከል ከታጩ አትሌቶች መካከል አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ እና መቅደስ አበበም በሉዛን ተሳታፊ የነበሩ አትሌቶች ናቸው። በዚህም ብሄራዊ ቡድኑ ተሰባስቦ ሆቴል ከመግባቱ አስቀድሞ በእነዚህ ውድድሮች ላይ ወቅታዊ አቋማቸውን በመፈተሽ ላይ ይገኛሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም