የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች እግር ኳስ ቻምፒዮና በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ በወንዶች አንደኛ ሊግን የሚቀላቀሉ አራት ቡድኖችን እንዲሁም በሴቶች ከፍተኛ ሊግን የሚቀላቀሉ ሁለት ክለቦችን የሚለይበት መድረክ ነው፡፡
ውድድሩ በሁለቱም ፆታ በድምቀት የቀጠለ ሲሆን፤ ዛሬ አስራ አንደኛ ቀኑን አስቆጥሯል። በከፍተኛ ፉክክር ታጅቦ የቀጠለው የወንዶች ውድድር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ እየተካሄደ ሲሆን፣ ለ25 ቀናት የሚቆይ ይሆናል። በቻምፒዮናው ከአስር ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ክለቦች የሚፎካከሩበትም ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሪነት ከሚካሄዱ ውድድሮች አራተኛ እርከን ላይ የሚቀመጠው የክልል ክለቦች ቻምፒዮና ወደ የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር የሚቀላቀሉትን ክለቦች ለመለየት አጋጊ ፉክክር የሚታይበት ሆኗል፡፡
በቻምፒዮናው ከሰኔ 14/2015 ዓ.ም ጀምሮ 31 ክለቦች በስምንት ምድቦች ተከፍለው ውድድራቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እስከ ሐምሌ 8/2015 ዓ.ም በሚቆየው ውድድር በእያንዳንዱ ምድብ አራት ክለቦች ተደልድለው የምድብ ማጣሪያቸውን ወደ ማገባደዱ ተቃርበዋል።
ከምድብ 1-15ኛ ካምፕ ሀዋሳ፣ ሚቶ፣ ኩርሙ ጉሌ፣ ቤሮ ወርቅ፤ በምድብ 2 ቃላድ አምባ፣ ጎንደር አራዳ፣ ወንዶ ገነት፣ መንጌ ቤኒሻንጉል፤ ምድብ 3 ናቲ ዩኒቲ፣ ቡልቡላ አሜን፣ ዋልያ ድሬዳዋ፣ ሱሉልታ ቢ ምድብ 4 አማያ፣ ቦሌ ገርጂ፣ ገንደ አብዲ ቦሩ፣ ዱል አዛሀቢ፤ ምድብ 5 መታፈሪያ ክፍሌ፣ ደምበጫ ከተማ፣ ቢኢ ከተማ፣ ማያ ሲቲ፤ ምድብ 6 ምቦቦ ዳዲበን፣ ኛንግላንድ፣ መልካ ኖኖ፣ ፍቅር በአንድነት፤ ምድብ 7 ቦረና መካነ ሰላም፣ ጊምቢ ከተማ፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ሠመራ ሎጊያ፤ ምድብ 8 ቲሊሊ ከተማ፣ ደንቢ ዶሎ፣ የኛ ፣ የኛ አዲስ ከቴ በስምንቱ ምድቦች የተደለደሉ ክለቦች ናቸው።
የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ቻምፒዮና የክልል ክለቦች ተሰጧቸውን የሚያሳዩበት እና የወደፊት ኮከቦች የሚወጡበት ወሳኝ መድረክ ነው። በብሔራዊ ቡድን ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ለሚፈልጉ እና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ፕሮፌሽናል ክለቦችን ቀልብ ለመሳብ ለሚፈልጉ ተጫዋቾች እንደ መወጣጫ ሆኖም ያገለግላል። በመላ አገሪቱ የሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በዘንድሮው ቻምፒዮና የሚደረጉትን አስደሳች ጨዋታዎችና ፉክክሮች በጉጉት እየተከታተሉም ነው።
ቡድኖቹ ጠንካራ የምድብ ጨዋታዎችን በማካሄድ ላይ ሲሆኑ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመቀላቀል ጥረት በማድረግ ላይም ናቸው። ወሳኝ ድሎችን ለማስመዝገብ እና በውድድሩ የበለጠ ግስጋሴ ለማድረግ የሚያሳዩት እንቅስቃሴም በተጠባቂነቱ ቀጥሏል። በቀጣይ ከእያንዳንዱ ምድብ የሚያልፉ ቡድኖች የጥሎ ማለፍ ውድድራቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።
በዚህም በ2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የሚሳተፉ አራት ክለቦች ይለዩበታል። እስከ አሁን በሁሉም ምድቦች በተደረጉ ጨዋታዎች የተሻሉ እንቅስቃሴዎችና ተመጣጣኝ ፉክክሮች ተደርገዋል። በጎሎች የታጀቡና ለተመልካች የማይሰለቹ ጨዋታዎች ተመልካቹን ይበልጥ ጉጉት እንዲያድርበት አድርገዋል፡፡ ቡድኖቹ አብዛኞቹን የምድብ ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን ጥሎ ማለፉን የሚቀላቀሉትም ከወዲሁ እየተለዩ ይገኛሉ።
ሌላኛው የኢትዮጵያ ሴቶች የክልል ክለቦች ቻምፒዮና በተመሳሳይ በሀዋሳ ከተማ አርቴፊሻል ሜዳ እየተካሄደ ነው። ዘጠኝ ክለቦች በሁለት ምድብ ተደልድለው ውድድራቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የሴቶቹ ውድድር ከተጀመረ አንድ ሳምንት የሞላው ሲሆን የተለያዩ ቡድኖች በሚያደርጉት ፉክክር ያልተጠበቁ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ቢሾፍቱ ከተማ፣ ኤግልስ ዲላ፣ አምቦ ጎል ፕሮጀክት፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና ደብረማርቆስ በምድብ አንድ ሲደለደሉ ሰሌክት ኮሌጅ፣ ሲዳማ ፓይለት ፕሮጀክት፣ ገበዝ ማርያም ከተማና ጉለሌ ክፍለ ከተማ በምድብ ሁለት ተደልድለው ውድድራቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው። በውድድሩ ላይ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ ክለቦች በቀጣይ በ2016 ዓም የሚካሄደውን የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ የሚቀላቀሉ ይሆናል። እንደ ወንዶቹ ሁሉ የሚደረገው ፉክክር ቀላል የሚይባል ሲሆን ቡድኖቹ እርስበርስ በሚያደርጉት ግንኙነት ጠባብ በሆኑ ውጤቶች እየተሸናነፉ ቀጥለዋል።
ውድድሮቹ ዛሬም በወንዶችና በሴቶች በተለያዩ ሜዳዎች ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን ቀሪ ከምድቡ የሚያልፉ ክለቦች ተለይተው ይታወቃሉ። በወንዶች 16ቱን የሚቀላቀሉና በሴቶች ደግሞ ወደሚቀጥለው ዙር አላፊ ክለቦችን ለመለየት የሚደረገው ፍልሚያም ተጠባቂ ይሆናል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015