አዲስ አበባ፡- በዩኒቨርሲቲው የሚሰጡ ትምህርቶች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲኖራቸው እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በዋናነት ከሚሠራው የመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ ተማሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲው ሲወጡ ያላቸው ተፈላጊነት እንዲጨምር የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል።
በመሆኑም በዚህ ዓመት ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸው ትምህርቶችን ዓለም ዓቀፍ እውቅና እንዲያገኙ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
እውቅናውን ለማግኘት በአሜሪካ ሀገር የሚገኝ የትምህርት እውቅና የሚሰጥ ተቋም ምዘና ለማካሄድ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ የሚሰጠው እውቅናም ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው ትምህርት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም ላይ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የሚገመግም መሆኑን አብራርተዋል።
የኢንጂነሪንግና ሳይንስ ፕሮግራሞች የሚሰጠው ይህ እውቅና እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ባለፉት አራት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው የትምህርት ካሪኩለም ማሻሻያ ተደርጎበታል ብለዋል።
ምዘና ሰጪ አካላት በታኅሣሥ ወር እንደሚመጡ የገለጹት ደረጀ (ዶ/ር)፤ ከዛም በኋላ በአዲሱ ካሪኩለም የሚያልፉ ማለትም አሁን በዩኒቨርሲቲው ትምህርት ላይ ያሉ እና በዚህ ዓመት ዩኒቨርሲቲውን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች የሚያገኙት ዲግሪ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው እንደሚሆን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲው ተመርቀው ለሚወጡ ተማሪዎች በየትኛው የዓለም ሀገራት ቢወዳደሩ ሥራ ማግኘት የሚችሉበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት አቅዶ ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ ተማሪዎች ሲመረቁ አንድ ፈጠራ ይዘው መውጣት አለባቸው የሚል መሆኑን አብራርተዋል።
ይህም ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመው፤ ለዚህም የሚሆን ተማሪዎች ምርቶቻቸውን የሚሠሩበት እንዲሁም ለገበያ የሚያቀርቡበት ቦታ እየተመቻቸ ይገኛል ብለዋል።
የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችና ምርምሮች በስፋት እንዲሠሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም