ማኅበራዊ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች መረጃ የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ:- ማኅበራዊ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች መረጃ በአንድ ቋት የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር  ዴኤታ ሁሪያ አሊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ማኅበራዊ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች የተለያዩ አገልግሎትን ማግኘት እንዲችሉ ብሔራዊ የምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በዚህም ማኅበራዊ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲመዘገቡ እየተደረገ ይገኛል።

ማኅበራዊ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚባሉት የስደት ተመላሾች፣ የውጭ ሀገር ስደተኞች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሌሎች ርዳታ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ በመጥቀስ፤ የእነዚህን ዜጎች መረጃ በዘመናዊ ሥርዓት በአንድ ቋት መሰብሰብ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

ይህም የድግግሞሽ ሥራ እንዳይኖር፣ ትክክለኛ መረጃን ለማደራጀት፣ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ ለመወሰን እና ለፖሊስ ግብዓትነት እንደሚያገለግል አብራርተዋል።

አሁን ላይ በብሔራዊ የምዝገባ ሥርዓቱ የጎዳና ተዳዳሪዎችን መመዝገብ መቻሉን አንስተው፤ ይህም ውጤታማ በመሆኑ ሌሎች የማኅበራዊ ጥበቃ ተጠቃሚዎች በምዝገባ ሥርዓቱ እንዲካተቱ ይደረጋል ብለዋል።

ስደተኞች የንግድ ሥራ ለመጀመር እና የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማግኘት የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸው ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በብሔራዊ የምዝገባ ሥርዓቱ ከተካተቱ በኋላ ግን የፋይዳ መታወቂያን በመያዝ አገልግሎቱን በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን በመጠቆም፤ ይህም የዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት። ለዚህም ሚኒስቴሩ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

ቴክኖሎጂ ማዘመን ላይ በትኩረት እየሠራን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ይህም የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎችን እና የስደት ተመላሽ ዜጎቻችንን እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በሚገባቸው ልክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

ሚኒስቴሩ እንደ ሀገር ትክክለኛ መረጃ እንዲኖር እና ሰዎች የሚገባቸውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በዚህም ከኢትዮጵያ የሚወጡትን እና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር እና መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ገልፀዋል።

ሳሙኤል ወንደሠን

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You