ለከባዱ ራስን ማጥፋት – ቀላሎቹ መፍትሔዎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት 800 ሺህ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን ይህም ራስን ማጥፋትን ሦስተኛው እና ትልቁ የሞት መንስኤ አድርጎታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችንም ሰዎች ራሳቸውን አጠፉ የሚሉ ዜናዎች እየተበራከቱ ናቸው፡፡ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ቢሆንም ታዋቂ ሰዎች፣ ሃብታም፣ ደሃ፣ ወጣት፣ አዛውንት ሳይለይ ሁሉም የችግሩ ተጋላጭ መሆናቸው ይነገራል፡፡

በሀገራችን የማኅበረሰቡ ስለ ጉዳዩ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑና እንደ ችግር የሚወራ አለመሆኑም ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡

በዚህም የበርካቶች ሞት መንስኤ የሆነው ራስን ማጥፋት ተገቢው መፍትሔ ሳይበጅለት ተሸፋፍኖ እንዲዘልቅ ሆኗል፡፡ ችግሩ ተደብቆ አለያም ተሸፋፍኖ የሚያልፍ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ከማባባስ ባለፈ የተቀረው ኅብረተሰብ ስለ ጉዳዩ እውቀት እንዳይኖረውና እንዳይማርበት ያደርጋል፡፡

እንዲሁም በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናትና ምርምሮች አለመደረጋቸው ችግሩን ለመፍታት አዳጋች አድርጎታል፡፡ ታዲያ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚዳርጉ ምክንያቶች ምንድናቸው? ምንስ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል በሚለው ዙሪያ ኢፕድ የሥነልቦና ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡

የሰው ልጅ ራሱን ለማጥፋት የሚዳርጉት ብዙ ምክንያቶች አሉ የሚሉት የሥነልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ኪሮስ ናቸው፡፡

ዓለም ላይ በዓመት ከ800 ሺህ ሰዎች በላይ እራሳቸውን እንደሚያጠፉ ጥናቶች እንደሚያሣዩ ጠቅሰው፤ ራስን ከማጥፋት ጀርባ የተለያዩ አይነት የሥነልቦና እና የአዕምሮ እክሎች የሚገኙ መሆኑን ይናገራሉ።

ራስን ለማጥፋት በዋናነት ከሚዳርጉ የሥነልቦና ሕመሞች መካከል ድባቴ የሚባለው አንዱ ሲሆን ይህም ራሳቸው ከሚያጠፉት ሰዎች አብዛኛዎቹ በድባቴ ሕመም የተጠቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ሰዎች በሕይወት ዘመን በተለይም በልጅነት ያጋጠመ አሰቃቂ አጋጣሚ፣ ከወላጅ ጋር ያላደጉና የሚገባውን ፍቅር ያላገኙ እንዲሁም ሥነልቦናዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር የመቋቋም አቅም ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች እንደሚያሣዩ ይገልጻሉ።

ይህም በሚያጋጥማቸው ራስን የመጥላት እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት፣ የብቸኝነት ስሜት ራስን ማጥፋትን እንደ ማምለጫ መንገድ አድርገው የሚወስዱ መሆኑን ያስረዳሉ።

አንዳንድ የሥነልቦና ሕመሞች በዘር እንደሚተላለፉ ጥናቶች ያሳያሉ የሚሉት ባለሙያው፤ በቤተሰብ የመጣ የሥነልቦና ሕመም እንዲሁም በሱስ የሚጠቁ ሰዎች ለሕይወት ትርጉም አለመስጠትና በሕይወት የሚጠብቁት ነገር ሳይሳካ ሲቀር ከእውነታው ማስታረቅ ሲከብዳቸው   ራሳቸውን የሚያጠፉ መሆኑን ይናገራሉ።

በአንድም በሌላም መንገድ ሰዎች በሆነ የሕይወት አጋጣሚ እራስ የማጥፋት ስሜት ውስጥ ይገባሉ ያሉት አቶ ኤርሚያስ፤ በአካል ላይ ሕመም ሊያጋጥም እንደሚችለው ሁሉ የሥነልቦና ቀውስ ሊያጋጥም እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል ይላሉ።

በመሆኑም እያንዳንዱ ስሜት ጊዜያዊና የሚለወጥ ስሜት መሆኑን ማወቅ፣ ሕይወት ትርጉም ያለው እንጂ የአጋጣሚ ውጤት እንዳልሆነ መገንዘብ፣ በዓላማ የተፈጠሩ እንደሆኑ ማሰብ ብሎም የሥነልቦና አማካሪ ጋር በመሄድ እርዳታ ማግኘት እንደሚገባ ያስረዳሉ።

አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት ራስን ማጥፋት ሦስት ሂደቶች ያሉት ሲሆን ማሰብ፣ ራሳቸውን የሚያጠፉበትን መንገድ ማቀድ እና ራስን ለማጥፋት መሞከር ናቸው። እንደማኅበረሰብ ስለአዕምሮ ሕመም ያለንን አመለካከት በመቀየር ከመፍረድ ይልቅ በቅርብ በመረዳት፣ ጆሮ መስጠትና ችግሮቻቸውን ማዳመጥ ይገባል ባይ ናቸው።

ራስን ለማጥፋት በስፋት ተጋላጭ የሆነው ወጣቱ ትውልድ በመሆኑም መንግሥት ለአዕምሮ ጤንነት ትኩረት በመስጠት በስፋት በሥነልቦና እና አዕምሮ ግንባታ ላይ በትኩረት መሥራት አለበት ይላሉ።

ሌላኛዋ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ ጫላ በበኩላቸው፤ ተስፋ መቁረጥ ሰዎች እራሳቸውን እንዲያጠፉ የሚገፋፋቸው ዋነኛው ምክንያት ነው ይላሉ።

በሀገራችን ጥሩ የማኅበራዊ ግንኙነቶች ቢኖርም አንዳንድ ሰዎች የውስጣቸውን ለሰዎች አውጥቶ ማውራት ቀላል አይሆንላቸውም የሚሉት ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ፤ በሚያጋጥማቸው የብቸኝነትና የድብርት ስሜትም እራስን የማጥፋት ሃሳቦች እየዳበሩ እንዲመጡ ያደርጋሉ ብለዋል።

በመሆኑም ሃሳብን ለሌሎች ከማካፈል ጀምሮ ለራስ ዋጋ መስጠት፤ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር፤ ሱሶችን መተው እና እራስን ማዳመጥ የመሳሰሉ ተግባራትን በማከናወን መፍትሔ መስጠት የሚቻል መሆኑን ያስረዳሉ።

በመሆኑም አንድ ሰው ከቀድሞ በተለየ ፀባይና ዝምታን ወይም ራስን የማግለል ባሕሪ ሲያዘወትር ምንድነው ብሎ መጠየቅ እና የሃሳቡ ተካፋይ መሆን ከዚህ ችግር ለማስወጣት ወሳኝ መፍትሔ ነው ይላሉ።

በተለይም በማኅበረሰቡ በኩል ያለን ግንዛቤ ለማሳደግ በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሥራት የግድ የሚል መሆኑን ይገልጻሉ።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You