በአዳማ ከተማ በበጋ መስኖ ልማት 30 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ማልማት ተጀምሯል

አዲስ አበባ፡- በአዳማ ከተማ በበጋ መስኖ ልማት 30 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ማልማት መጀመሩን የከተማዋ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዓለሙ ቂልጡ እንደገለፁት፤ በከተማዋ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ለማሳካት ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል።

በተለይ በዘንድሮው በጋ ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በወንጂ፣ በአዋሽ መልካሣና በመልካ ሂዳ ወረዳዎች በበጋ መስኖ የታረሰውን መሬት በዘር የመሸፈን ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአጠቃላይ 30 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ከ75 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና 18 ሺህ  192 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

የስንዴ ልማት ሥራው በኩታ ገጠም እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው በእስከ አሁኑ ሂደት ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

አጠቃላይ ከሚለማው መሬት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤ ይከናወናል ብለዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ 12 ሺህ 392 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በከተማው የዶሮና ወተት ላሞች እርባታ፣ ሰንጋ ማድለብ፣ የአሣማ እርባታ፣ የበጎችና ፍየሎች እርባታ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የግብርና ልማት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ዳግም ሲዋቀር በከተማው ዙሪያ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ አስተዳደሩ መካለላቸው ይታወሳል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You