ዜጎች ስለማኅበራዊ ሚዲያዎች ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፦ ዜጎች ስለሚጠቀሟቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አይነቶች ግንዛቤያቸው ሊያድግ እንደሚገባ የጋዜጠኝነትና ሥነተግባቦት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ሰለሞን ሙሉ ገለጹ።

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሰለሞን ሙሉ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ ዜጎች የማኅበራዊ ሚዲያዎችን አሠራር ካለመረዳት የተነሳ ለተለያዩ ጉዳቶች እየተዳረጉ በመሆኑ ስለሚጠቀሟቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አይነቶች በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል።

የማኅበራዊ ሚዲያዎችን አጠቃቀም የቻሉ ዜጎች ለበጎ ተግባር እያዋሉት እንደሆነ ገልጸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሠራሩን ያልተረዱ ተጠቃሚዎች አሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ ሲወድቁ ይስተዋላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ስማርት ሞባይል ያለው ሰው የመጀመሪያ ሥራው የፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቲዊተር፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራምና ሌሎችንም የማኅበራዊ ሚዲያ አይነቶች መጫን ነው የሚሉት መምህሩ፤ በዚህም የተለያዩ ይዘቶችን እንደሚከታተል ጠቁመዋል።

እንደ መምህር ሰለሞን ገለጻ፤ በተለይም ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚመለከቱት ብልጭልጭ ይዘት እየሳባቸው ስብዕናቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በዚህም የማኅበራዊ ሚዲያ በዜጎች ላይ እያደረሰባቸው ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማዘውተራቸው የትምህርት ወይም የሥራ ጊዜያቸውን ትርጉም በሌለው ጉዳይ ላይ ማሳለፋቸው በሁለንተናዊ የሕይወት እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና በማሳደር ለድብርትና ለማይጨበጥ ምኞት እንደሚዳርጋቸውም አንስተዋል።

በመሆኑም ለዜጎች የሚዲያና የመረጃ አጠቃቀም ሥልጠናዎችን ስለእያንዳንዱ የማኅበራዊ ሚዲያ አይነት፣ አሠራርና ስለቢዝነስ ሞዴላቸው እንዲረዱ በማድረግ ተፅዕኖውን መቀነስ ይቻላል ብለዋል።

በአደጉ ሀገራት የማኅበራዊ ሚዲያ ዕውቀት ለሕጻናትም ጭምር ከታችኛው ክፍል ጀምሮ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ እንዲማሩ እየተደረገ እንደሆነ መምህር ሰለሞን ተናግረዋል።

ይህ ተሞክሮ በኢትዮጵያ የሌለ በመሆኑ ቢያንስ ከመሰናዶ ጀምሮ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ ሊሰጥ እንደሚገባ የሚያነሱት መምህር ሰለሞን፤ በተለይም ከማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የመረጃ መዛባት፣ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን መዋጋት የሚቻለው ቀድሞ ዜጎችን በማስተማር ነው ብለዋል።

መምህር ሰለሞን፤ በመደበኛ የትምህርት ሥርዓቱ ላሉ ዜጎች በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካቶ ማስተማር ይቻላል፤ ነገር ግን ሌሎችን ባሉበት ቦታ ማለትም ወጣቶችን በወጣቶች ማኅበር፣ የመንግሥት ሠራተኞችን በየተቋማቸውና በሌሎችም ዜጎች ሊገኙ በሚችሉበት ስፍራ ሥልጠና መስጠት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጭ ማንኛውም መረጃ እንደሐሰት የሚወስድበት ሁኔታ መኖሩን ያነሱት መምህሩ፤ ይህ ተገቢ እንዳልሆነ በማስተማር በሁሉም የሚዲያ አይነት የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመመርመር ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ሀሳብ አመዛዝኖ መቀበል እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You