የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በመጪው ነሃሴ ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዳል፡፡ ሃንጋሪ በመዲናዋ ቡዳፔስት በታሪኳ ትልቁን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የምታስተናግድ ሲሆን፤ ከመላው ዓለም 200 የሚሆኑ የሀገራት አትሌቶችን ለመቀበል ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ትገኛለች፡፡ በሩጫ እና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች አሉ የተባሉ ስኬታማና አዳዲስ ኮከብ አትሌቶች የሚደምቁበት የውድድር መድረክ እንደመሆኑ በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ከፍተኛ ግምት ይሰጠዋል፡፡
የዓለም ሀገራት ለዚህ ታላቅ የውድድር መድረክ አትሌቶቻቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት ጀምረዋል። በቻምፒዮናው ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት የማራቶን ቡድኗን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል። ከትናንት በስቲያ ደግሞ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች የሚሳተፉ አትሌቶቿን አሳውቃለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ800 ሜትር እስከ 10ሺ ሜትር ባሉ ርቀቶች እጩ የብሄራዊ ቡድን አባላት ከነተጠባባቂዎቹ ይፋ አድርጓል። በዚህም በ800 ሜትር ሴቶች የመግቢያ መስፈርቱን ያሟሉት አትሌት ሀብታም ዓለሙ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ወርቅነሽ መለሰ ኢትዮጵያን ወክለው በቡዳፔስቱ ቻምፒዮና የሚሳተፉ አትሌቶች ይሆናሉ።
ከሁለት ወራት በፊት በፈረንሳይ በተካሄደ ውድድር በዚህ ርቀት ተሳትፎ የነበረው አትሌት ኤፍሬም መኮንን በኮታ የቻምፒዮናው ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠ ብቸኛው አትሌት ሆኗል። ኢትዮጵያ ውጤት በምትጠብቅበት የሴቶች 1 ሺ500 ሜትር ውድድር በዩጂን በተደረገው የዓለም ቻምፒዮና የዲፕሎማ ባለቤት የነበረችው አትሌት ፍሬወይኒ ሃይሉ ቀዳሚ ተመራጭ ሆናለች። ከዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችውና በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ባሳየችው ብቃት ትልቅ ተስፋ የተጣለባት ወጣቷ አትሌት ብርቄ ሃየሎም ሌላኛዋ ተመራጭ ሆናለች። በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት ታደሰ ለሚ፣ አብዱከሪም ተኬ እና ኤርሚያስ ግርማ እጩ መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ የሆኑበት የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር በዓለም ስመጥር የሆኑ አትሌቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ይሆናል። በወንዶች በኩል በዶሃ እና ዩጂን የዓለም ቻምፒዮናዎች የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በቅርቡ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ለሜቻ ግርማ የተካተተበት ቡድን ይፋ ተደርጓል። ጌትነት ዋለ እና አብረሃም ስሜም በዚህ ርቀት የተመረጡ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ሆነዋል።
በተመሳሳይ ርቀት በዩጂን የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው የርቀቱ ስፔሻሊስት አትሌት የወርቅውሃ ጌታቸው ዘንድሮም ድንቅ ብቃቷን ለማሳየት እድል አግኝታለች። ወጣቷ አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ፣ ዘርፌ ወንድምአገኝ እና መቅደስ አበበም በርቀቱ ዕጩ በመሆን ተካተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት ስሟ ከተጠራባቸው እንዲሁም በርካታ ክብሮችን ከተቀዳጀችባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ የ5 ሺ ሜትር ውድድር ነው፡፡ በዚህ ርቀት በወንዶች በኩል አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ጥላሁን ኃይሌ እጩ ሆነው ሲቀርቡ፣ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የ 1 ሺ500 ሜትር አሸናፊው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ተጠባባቂ ሆኖ ተመርጧል። በቀዳሚነት የተመረጡት ሁለቱ አትሌቶች በቅርቡ ኦስሎ ላይ በተካሄደው ዳይመንድ ሊግ አንደኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ በሴቶች በኩል የዓለም ቻምፒዮናዋ ጉዳፍ ጸጋዬ በቀጥታ በርቀቱ ተሳታፊነቷን ያረጋገጠች አትሌት ሆናለች፡፡ አትሌት ያለምጌጥ ያረጋል ደግሞ በተጠባቂነት ተይዛለች፡፡
በቅርቡ ስፔን በተካሄደው የ10ሺ ሜትር የሰዓት ማሟያም በሁለቱም ጾታ 6 አትሌቶች ተመርጠዋል። በዚህ ርቀት ኢትዮጵያ የዓለም ቻምፒዮናን ጨምሮ በኦሊምፒክና ሌሎች ውድድሮች ውጤታማ መሆኗ ይታወቃል፤ በዚህ ውድድርም ለሜዳሊያ ከሚጠበቁ ቡድኖች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ በወንዶች በኩል 26፡50፡66 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነው አትሌት በሪሁ አረጋዊ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ እና ይስማው ድሉ ደግሞ በተከታይነት በቡድኑ የተካተቱ አትሌቶች ናቸው፡፡ የዓለም ቻምፒዮናዋ ለተሰንበት ግደይ ያለችበት የሴቶቹ ቡድንም በተመሳሳይ ለአሸናፊነት በቅድሚያ ተጠባቂ ነው፡፡ እጅጋየሁ ታዬ እና ለምለም ኃይሉ በማጣሪያው ባስመዘገቡት ሰዓት በውድድሩ ላይ የሚካፈሉ አትሌቶች ናቸው፡፡
እጩዎቹን ያሳወቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከምርጫው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን እስከ ዛሬ ድረስ እንዲያቀርቡ አስታውቋል፡፡ ከማራቶን እና ከ10 ሺ ሜትር በቀር ባሉት ርቀቶችም ዓለም አቀፍ ውድድሮች እስከሚዘጉ ድረስ በሚመዘገብ ውጤት የዕጩ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችልም ፌዴሬሽኑ አስገንዝቧል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2015