የነገዋን ኢትዮጵያ መመልከቻ ዓውድ

ትምህርት ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የፈጠራ ውድድሮች ያካሂዳል፡፡ በዚህም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና መምህራን የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለውድድር ያቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ ውድድሮች መካከል ደግሞ ሀገር አቀፍ የሳይንስና ምሕንድስና የፈጠራ ሥራዎች ውድድርና ዓውደ ርዕይ አንዱ ነው፡፡

በውድድሩ ላይ አንደኛ የወጣውና ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል የመጣው ወጣት ዮናታን አፈወርቅ የእንስሳት መኖ እጥረትን በቀላሉ ሊቀርፍ የሚችል የፈጠራ ሥራ ይዞ ቀርቧል፡፡

የፈጠራ ውጤቱ አይ ኦቲ አሲስትድ ቨርቲካል ፊድ ፕሮዲውሲንግ ማሽን እንደሚባል የሚገልፀው ተማሪ ዮናታን፤ ማሽኑ መኖን በአጭር ጊዜ በማምረት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል መሆኑን ይናገራል፡፡

የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመቅረፍ መሥራቱን በመግለጽ፤ ለማሽኑ መሥሪያነት የተለያዩ ሴንሰሮችንና ግብዓቶች በመጠቀም መሥራት መቻሉን ይገልጻል፡፡

የመኖ ማሽኑ በማያቋርጥ መልኩ ምርት በማቅረብ የመኖ እጥረትን ችግር ሊቀርፍ የሚችል እንደሆነም ነው የሚያስረዳው።

ማሽኑ አንድ ኪሎ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎን በመጠቀም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከአምስት ኪሎ ግራም በላይ መኖ ምርት መስጠት የሚችል ማሽን ነው።

ማምረቻ ማሽኑ በአሁኑ ሰዓት ገበያ ላይ ከሚገኙት የመኖ ምርቶች ለየት የሚያደርገው የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ያሉት በመሆኑ ነው የሚለው ወጣቱ፤ በተለይም ፖታሺየም ናይትሬት፣ ፎስፈረስ የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘ መሆኑን ይናገራል።

በቀጣይ ማሽኑን ወደ ገበያ በማቅረብ ከፈጠራ ሥራው ተጠቃሚ ለመሆን ማቀዱንም ነው የሚያስረዳው።

የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች የማኅበረሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባም ያሳስባል።

የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ትግበራ መቀየር የሥራ ዕድልን፣ ሀብትን ለመፍጠር እና ከውጪ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ያስችላል የሚለው ደግሞ የፈጠራ ሥራ ባለሙያው ወጣት ኢዘዲን ካሚል ነው።

የመጀመሪያውን ሀገር አቀፍ የሳይንስና ምሕንድስና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር ካሸነፈ በኋላ በርካታ ዕድሎች እንደተከፈቱለት የሚናገረው ወጣት ካሚል፤ የፈጠራ ሥራዎቹ የተሻለ ሀብት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት እንዳስቻሉት ይናገራል።

ወጣቱ የፈጠራ ሥራዎቹን ተግባራዊ በማድረግ ወደ ገበያ ሥርዓቱ ገብቷል። በዚህም አሁን ላይ የቴክኖሎጂና ፕሮሞሽን ድርጅት ባለቤት መሆኑን እና 18 ሠራተኞችን በሥሩ ቀጥሮ እየሠራ እንደሚገኝ ያስረዳል።

ከ400 በላይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት የድርጅቱን የሶፍትዌር ውጤቶች እየተጠቀሙ እንደሚገኝ የሚገልጸው ወጣቱ፤ ከ37 በላይ ሀርድዌር ሥራዎች ላይ መሥራቱንና 14 ሽልማቶች ማግኘት መቻሉን ይናገራል።

የውድድር መርሐ ግብሮች ተወዳዳሪዎች ከተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር ዕድል እንደሚፈጥርላቸውም ነው የሚገልጸው ።

ታዳጊና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ከግል ሥራ ይልቅ በቡድን መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ወጣት ካሚል ይመክራል።

የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ትግበራ መቀየር የሥራ ዕድል፤ ሀብት መፍጠርና ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል መሆኑንም ወጣቱ ይናገራል።

ውድድሮች ግብ ሊሆኑ እንደማይገባ እና የፈጠራ ሥራዎች ወደ ገበያ መውጣት እንደሚገባቸው የሚመክረው ኢዘዲን፤ የፈጠራ ሥራዎች ግብ መሆን የሚገባው ለኅብረተሰቡ ቀርበው ችግር ፈቺነታቸው ላይ ሊሆን ይገባል ይላል።

የፈጠራ ባለሙያዎች ከቴክኒካል እውቀቶች ባሻገር የቢዝነስ እሳቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ በመግለጽ፤ የቢዝነስ አስተዳደር፣ የገበያ እና ፋይናንስ ዕውቀቶች እንደሚያስፈልጋቸው ይገልጻል።

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ የዘንድሮውን የዓለም የሳይንስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለ9ኛ ጊዜ ሀገር አቀፍ የሳይንስና ምሕንድስና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር መካሄዱ ብዙ ዕድሎችን ፈጥሯል።

ለአንድ ሀገር እድገት ሳይንስ፣ ሂሳብ እና ምሕንድስና ወሳኝ ናቸው የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በተለይም ተማሪዎች እና መምህራን ለሳይንስ ትኩረት እንዲሰጡ ለማነቃቃት ሀገራዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ያብራራሉ።

ተማሪዎች ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ የተዘጋጁላቸውን ማዕከላት ተጠቅመው የፈጠራ ሥራዎችን እንደሚሠሩ በመግለጽ፤ ዩኒቨርሲቲዎች እና መምህራን በማኅበረሰብ አገልግሎት ልጆች ወደ ፈጠራ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።

ውድድሩ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበው እውቅና የሚሰጥበት መሆኑን ገልጸው፤ የፈጠራ ውጤት ያላቸው ወደ ሥራ ፈጣሪነት፣ ሀብት ወደ ማፍራት ሂደት እንዲገቡ የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ።

9ኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስና ምሕንድስና የፈጠራ ሥራዎች ውድድርና ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You