ጥር 07/2015 በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተጀመረው የሰራተኛው የበጋ ወራት ውድድሮች የፊታችን እሁድ በዚያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፍፃሜ እንደሚያገኙ ታውቋል። በኮቪድ-19 ምክንያት ለሶስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የሰራተኛው ስፖርት ለረጅም የውድድር ጊዜ በሚቆየው የበጋ ወራት ውድድሮች ዘንድሮ ተመልሶ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ጠንካራ ፉክክሮችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። በዚህም በመጪው እሁድ የፍፃሜ ፉክክር በሚያስተናግዱ ጥቂት ውድድሮች በይፋ የሚጠናቀቅ ሲሆን ባለፉት ሳምንታትም በበርካታ ውድድሮች አጠቃላይ አሸናፊዎች ተለይተው መታወቃቸውን ከኢሰማኮ የስፖርት ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
እሁድ ውድድሩ በይፋ ሲጠናቀቅ የፍፃሜ ፉክክር ከሚያስተናግዱ ጨዋታዎች መካከል በሁለቱም ዲቪዚዮን በወንዶች የእግር ኳስ ውድድር የዋንጫ አሸናፊ የሚለይበት በጉጉት ይጠበቃል። በሁለተኛ ዲቪዚዮን ፍፃሜ ተጋጣሚዎችም መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ይሆናሉ። አንደኛ ዲቪዚዮን የፍፃሜ ጨዋታም ኢትዮ ቴሌኮምን ከአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ጋር ያገናኘ ሆኗል።
ከእግር ኳስ በተጨማሪ በሴቶች ስምንት መቶ ሜትር እንዲሁም በወንዶች አምስት ሺ ሜትር የሚካሄዱ የአትሌቲክስ የፍፃሜ ውድድሮች ይጠበቃሉ።
አዝናኝ በሆነው የገመድ ጉተታ ውድድርም በሁለቱም ፆታ የፍፃሜ ግጥሚያ እንደሚኖር ታውቋል። የኢሰማኮ ስራ አስፈፃሚና የዘጠኙ ኢንደስትሪ ፌዴሬሽን አመራሮች የ4 መቶ ሜትር ፍፃሜ ውድድር የሚያደርጉም ይሆናል።
ቀደም ብለው የፍፃሜ ውድድር ተካሂዶባቸው አጠቃላይ አሸናፊዎች የተለዩ ሲሆን፣ በ1ኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ቮሊቦል አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሃያ ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። በሴቶች ደግሞ 13 ነጥብ የሰበሰበው አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ቀዳሚውን ደረጃ ይዞ ጨርሷል። በጠረጴዛ ቴኒስ የወንዶች አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ16 ነጥብ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ በ2ኛው ዲቪዚዮን ብራና ማተሚያ ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ ቀዳሚ ሆኗል። የሴቶቹን ፉክክር በበላይነት የፈጸመው አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ደግሞ አስራ ሁለት ነጥብ ሰብስቧል። አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ በወንዶች ከረንቦላ ውድድርም አራት ነጥብ እና በወንዶች የዳማ ውድድር ስድስት ነጥብ በማስመዝገብ በበላይነት አጠናቋል።
የወንዶች የዳርት ውድድርን ጂኦ ሴንቴቲክ ኢንደስትሪያል አስራ ሁለት ነጥብ ይዞ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፣ በሴቶች አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ በአስር ነጥብ እየመራ አጠናቋል። የወንዶች የቼስ ውድድር ደግሞ አስራ ሁለት ነጥብ በሰበሰበው ኢትዮ ቴሌኮም የበላይነት ተጠናቋል።
በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ በቆየው የወንዶች 2ኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ውድድር መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአስራ ሁለት ነጥብ የመጀመሪያውን ምድብ በመሪነት አጠናቋል። የሁለተኛው ምድብ ደግሞ ዘጠኝ ነጥብ በሰበሰበው ሆራይዘን አዲስ ጎማ መሪነት ተጠናቋል። በ2ኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ቮሊቮል ውድድር የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ሃያ አምስት ነጥብ በመሰብሰብ ቀዳሚ ነው።
በዘንድሮው የበጋ ወራት ውድድር በአስር የስፖርት አይነቶች በአጠቃላይ 1106 ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ 910 ወንድና ቀሪዎቹ ሴቶች ናቸው። ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የእግር ኳስ ውድድር 500 ሰራተኞች የተሳተፉበት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2015