አዲስ አበባ፡- አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ሂደት ላይ የተሳተፉ ቢሆንም የቀሩ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የተከሰቱ አለመግባባቶች እና ግጭቶች በውይይትና በምክክር ለመፍታት የሚካሄደውን ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ ለማድረግ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ መሆን አለባቸው።
ለዚህም በምክክር ሂደቱ ላይ ተሳታፊ ያልሆኑ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክክር ሂደቱ የማስገባት ሥራን ኮሚሽኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በሂደቱ ውስጥ በመሳተፍ በተደረገ የድምፅ ምርጫም በጋራ ምክር ቤቱ ከተገኙ 53 ፓርቲዎች 40 መሳተፍ አለብን ብለው ድምፅ ሲሰጡ 13 የሚሆኑት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳልነበራቸው አንስተው፤ በኮሚሽኑ እና በጋራ ምክር ቤቱ በተደረገ ጥረት አንሳተፍም ካሉ 13 ፓርቲዎች ስድስት የሚሆኑትን ተሳታፊ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በመሆኑም በጋራ ምክር ቤቱ በአጠቃላይ ከሚገኙ 70 ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 65 የሚሆኑት እየተሳተፉ የሚገኙ መሆኑን አስታውቀዋል።
ምንም እንኳን በሂደቱ ላይ ተሳታፊ ያልሆኑ ፓርቲዎች በቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆኑም በምክክር ሂደቱ መሳተፍ ይገባቸዋል ያሉት ሰብሳቢው፤ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ መድረክ፣ ወቢን እና አረና ትግራይ ፓርቲዎች ከመጀመሪያው ራሳቸውን በማግለል እየተሳተፉ አይደለም ብለዋል።
በምክክሩ ሁሉንም አካል በማሳተፍ ሃሳብን ማድመጥ የሚገባው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
የምክክሩ ተሳታፊ ያልሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ለምክከሩ ውጤታማነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ አይነት ግጭቶችና የፖለቲካ ውስብስብነቶች ባሉበት ሀገር ለፖለቲካው ፓርቲዎች ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አቶ ደስታ አንስተው፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ላይ መሳተፋቸው ከሌሎች ሀገራት ላይ ከታየ ተሞክሮ አንጻርም አወንታዊ ጎን ያለው መሆኑን አብራርተዋል። በመሆኑም ኮሚሽኑ በቀሩት አጭር የሥራ ጊዜያት ውስጥ ቀሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የአንድ ሀገር ሀገራዊ ምክክር ሂደት መሳካት የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፍ ብቻውን ወሳኝ አይደለም የሚሉት አቶ ደስታ፤ ከመንግሥት ጀምሮ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም የታጠቁ ኃይሎች ወደ ምክክር በመምጣት ሁሉንም ማሳተፍ እንደሚኖርባቸው ነው የተናገሩት።
ማሕሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም