የታሪካዊው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የማራቶን ውድድር ትናንት ለ39ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በ42 ኪሎ ሜትር ፉክክሩ መቻል በወንዶች አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን በሴቶች ኦሮሚያ ፖሊስ አሸናፊ ሆኗል። የወንዶቹን ፉክክር ፌደራል ፖሊስ 2ኛ፣ ፌደራል ማረሚያ 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። በሴቶች ደግሞ ፌደራል ፖሊስ 2ኛና መቻል 3ኛ ሆነው ፈፅመዋል።
መነሻውንና መድረሻውን ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ በማድረግ የተካሄደው ይህ የማራቶን ውድድር ዳገታማ ቦታ የሚበዛበት እንደመሆኑ ፉክክሩ ለአትሌቶች ቀላል አልነበረም። ያም ሆኖ ብርቱ ፉክክር ባስተናገደው የሴቶች ውድድር ጠጂቱ ሥዩም ከመቻል 2:41:33 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች። እሷን ተከትላም አስናቀች ግርማ ከኦሮሚያ ፖሊስ በ2:41:35 የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን፣ ብዙሀገር አደራው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2:41:38 ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችላለች።
በወንዶች መካከል በተደረገው ፉክክርም ብርሃኑ ደበበው ከፌደራል ፖሊስ በ2:14:85 ሰዓት 1ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ልመነህ ጌታቸው ከመቻል 2:15:12 በሆነ ሰዓት 2ኛ፣ ገልገሎ ጠና ከፌደራል ማረሚያ በ2:17:40 ሰዓት 3ኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
የወንዶቹን ውድድር በአሸናፊነት ያጠናቀቀው አትሌት ብርሃኑ ደበበው በታሪካዊው የማራቶን ውድድር ሲሳተፍ የመጀመሪያው መሆኑን በመጠቆም ፉክክሩ ፈታኝ መሆኑን ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል። የውድድሩን ስፍራ ፈታኝና አስቸጋሪ በማለት የገለፀው ባለድሉ አትሌት፣ ሙሉ በሙሉ በዳገትና ቁልቁለታማ ስፍራ መካሄዱ ፉክክሩን ይበልጥ ፈታኝ እንዳደረገው ተናግሯል። ያም ሆኖ ውድድሩ
በጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ የተሰየመና ታሪካዊ እንደመሆኑ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ በመቻሉ ትልቅ ክብር እንደተሰማው አስረድቷል። በቀጣይም በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ውጤት ለማምጣት እንደሚሠራም አክሏል። አትሌት ብርሃኑ እንደ ቡድን ዋንጫን ለማንሳት አቅደው ወደ ውድድር መግባታቸውን በማስታወስ ይህ ባይሳካም በአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ ለሆነው መቻል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል።
2ኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳለያ ተሸላሚ የሆነው አትሌት ልመንህ ጌታቸው ክለቡ መቻል በውድድሩ መሳተፍ ከጀመረ አስር ዓመታትን እንዳስቆጠረ በማስታወስ፤ በመድረኩ ውጤታማ መሆኑን ተናግሯል። ለዘንድሮው ውድድርም እንደክለብ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ፈታኝ በነበረው ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ መሆን እንደቻሉ አስተያየቱን ሰጥቷል። በሁለቱም ፆታ ከ1ኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ላጠናቀቁ አትሌቶች ከወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳሊያ በተጨማሪ እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። እስከ 8ኛ ደረጃ ያጠናቀቁ አትሌቶችም የሽልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አማካኝነት በየዓመቱ የሚካሄደው የአበበ ቢቂላ ማራቶን ለከተማ አስተዳደር፣ ለክለቦችና ለግል ተወዳዳሪ አትሌቶች የሀገር ውስጥ የውድድር ዕድል ለመፍጠርና ተተኪ የማራቶን አትሌቶችን ለማፍራት ታስቦ ነው የሚካሄደው። በዚህም በሁለቱም ፆታ 169 የክለብ አትሌቶች፣ 21 በክልል የተወከሉና ከ50 በላይ የግል ተወዳዳሪ አትሌቶች በዘንድሮው ውድድር ተሳትፈዋል። አንጋፋ(ቬተራን) አትሌቶችም በውድድሩ ተሳታፊ ናቸው ። አምና ባሕር ዳር ለ38 ጊዜ በተካሄደው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር በወንዶች አትሌት በላይ ኦልቀባ ከኦሮሚያ ፖሊስ 2:13:24 በሆነ ሰዓት አሸናፊ የነበረ ሲሆን፣ በሴቶች ዝናሽ ጋረደው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 2:32:15 በሆነ ሰዓት ባለ ድል መሆኗ ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ ለሽልማት 400ሺ ብር ያዘጋጀ ሲሆን 1ኛ 50ሺ፣ 2ኛ 25ሺና 3ኛ 20ሺ ብር የገንዘብ ሽልማቶችን አበርክቷል። ከ4ኛ-8ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የገንዘብ ሽልማቱ ለአንጋፋ አትሌቶችም የተበረከተ ሲሆን ከ1ኛ- 6ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን ላጠናቀቁ አትሌቶች ተበርክቷል። በዚህም 1ኛ ለወጡት 12ሺ ብር፣ 2ኛ ለወጡት 6ሺ ብርና 3ኛ ለወጡት 5ሺ ብር ተበርክቷል። በሁለቱም ጾታ በቡድን አሸናፊ የሆኑ ክለቦች ደግሞ የዋንጫ አግኝተዋል።
የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ውድድር በ1974 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረ ሲሆን፤ በየዓመቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተካሄደ አሁን 39ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። በመጀመሪያው ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት ሀገራት ማለትም ጅቡቲና ሶቪየት ተካፍለዋል። እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ የአበበ ቢቂላ ዓለም አቀፍ ማራቶን ውድድር የሚል ስያሜን በመያዝ የውጭ ሀገራት አትሌቶችን ተሳታፊ ሲያደርግ ቢቆይም ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን ውድድሩ ሀገራዊ መልክ እንዲይዝና ስያሜውም የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር በሚል ተሰይሞ እየተካሄደ ይገኛል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም