የኢትዮጵያን ፖለቲካ አሳምረው ያውቁታል። ከ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ «ቅንጅት» በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ተሳትፈዋል። ጀርመን ከገቡ ጀምሮ ለ17 ዓመት ያህል ፅዋ ያልጠጡበት የፖለቲካ ማህበር የለም። በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበርንና የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶችን ያውቋቸዋል። እነመኢሶን፣ ኢህአፓን፣ ሻዕቢያን፣ ኦነግን፣ ህወሃትንና ሌሎችን የተዋወቁት በስደት ላይ እያሉ ነው። ከአብዛኞቹም ጋር የፖለቲካ ጠበል ጻዲቅ ተቃምሰዋል።
አዳዲስ የፖለቲካ ማህበራትና የአርነት ድርጅቶችን አዋልደዋል። አያሌ የፖለቲካ ዕድሮች ሲመሰረቱም ሲፈርሱም ታዝበዋል። አንዳንዶቹ መሠረታቸው ሲጣል የፖለቲካ ሲሚንቶና አሸዋ አቀብለዋል። ሆኖም ከየትኛውም የፖለቲካ ስብስብ ጅምር እንጂ ውጤት አላዩም። ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ነጋሶ ለኦሮሞ ህዝብ መብትና ነጻነት የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ለመመስረት ታትረዋል። ሆኖም የፖለቲካው አበባ ሲጽደቅ እንጂ ሲደርቅ አሻፈረኝ አሉ። እናም አንጀት የሚያርስ የፖለቲካ ድርጅት ባህር ማዶም ሆነ አገር ቤት መጥፋቱ እያብሰከስካቸው ቁዘማ ያዙ።
ተስፋ ቆርጠው ግን ለፖለቲካው ጀርባቸውን አልሰጡም። ምክንያቱ ደግሞ ሌላ ሳይሆን ከተስፋ መቁረጥ ጋር ስለማይተዋወቁ ብቻ ነው። እናም ለአገራቸው አንድ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት ደጅ ደጁን ሲመለከቱ ኢህአዴግን እመንገዳቸው ላይ አገኙት። አጥንተውት እና አስጠንተውት ተጠጉት። ለዓመታት ከኖሩበት ባህር ማዶ ጓዛቸውን ጠቅልለው አገራቸው ገቡና ቃል ኪዳን አሰሩ።
ከኢህአዴግ ጋር 10 ዓመት የሚያህል የፖለቲካ መንገድ ተጉዘዋል። የለውጥን ተስፋ ሰንቀው በኦህዴድ አመራርነት፣ በሚኒስትርነትና በርዕሰ ብሔርነት በጽናት አገልግለዋል። ነጋሶ የዓላማ ሰው ናቸው፤ ላመኑበት በጽናት የሚቆሙ፡፡ ነገር ግን ለቃሉ የሚታመን የፖለቲካ ድርጅት በባትሪ ፈልገው አጡ፡፡ የሚገጥሟቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ሃሳባቸውንና አቋማቸውን እየቀያየሩ መከራቸውን አበሏቸው፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ በኩል ሶሻሊዝምን እንገነባለን ያላቸው ኢህአዴግ እንኳን የምመራው በነጭ ካፒታሊዝም ነው ብሎ እምነታቸውን አፈረሰባቸው ፤የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ስላልፈቀደ ለጊዜው ሶሻሊዝምን መሳቢያ ውስጥ ከተነዋል ሲባሉ «መታለላቸው» አሳዘናቸው፡፡ ሊጠይቁ እና ሊሞግቱ ሞከሩ፤ ውጤቱ ውግዘት ሆነባቸው::
እኚህ አንጋፋ ፖለቲከኛ የህይወት ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን ነጠላ የፖለቲካ መንገድ ብቻ አይደለም የምናየው፡፡ ከሞላ ጎደል የዘመኖቻቸውን የፖለቲካ ጎዳናም ተንሰላስሎ እናገኘዋለን፡፡
ለአገር የኖሩ የአገር አድባር የሆኑት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በስኳር ህመም እና በደም ግፊት ምክንያት በሳኡዲ አረቢያ በአሜሪካ እና በመጨረሻም በጀርመን ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በ75 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል። እኛም ዛሬ እኚህን ታላቅ የአገር ባለውለታ በ«ሕይወት እንዲህ ናት» አምዳችን ልንዘክራቸውና የሕይወት ጉዞአቸውን ልናወሳ ወደናል፤ መልካም ንባብ!
ልጅነት
በደምቢ ዶሎ መሀል ከተማ በቤተል ቤተክርስቲያን መንደር ልዩ ስሙ ከቾ በምትባል አካባቢ ነው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የፈለቁት። ከወላጅ እናታቸው ዲንሴ ሾሊ እና ከቄስ ጊዳዳ ሶለን ጳጉሜን 5 ቀን በ1935 ዓ.ም ተወለዱ:: ነጋሶ ልጅነታቸውን ያሳለፉት በምቾት አይደለም፤ለእግራቸው ሸራ ጫማ አያውቁም። ለትምህርት ሲሉም ከወላጆቻቸው ቤት ወጥተው በየዘመድ አዝማዱ ተንከራተዋል።
የነጋሶ የልጅነት ሕይወት በችግር የተሞላ ብቻ አልነበረም፡፡ እርሳቸውም «ልጅነቴ ማር እና ወተቴ»ን አሳምረው ያውቁታል:: ጣፋጭ የልጅነት ትዝታም ነበራቸው፤ «ጢሎ» የምትባለውን ጥቁሯን ላማቸውን አይረሷትም፡፡ ሌላው የልጅነት ሕይታቸውን «ዳንዲ የነጋሶ መንገድ» በሚለው መጽሐፍ ላይ ስለ ገጠመኛቸው ሲናገሩ «በኦሮሞ ባህል እናት ልጇን ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት የምታጠባ ቢሆንም እኔ ግን ቶሎ ጡት አልተውኩም ነበር፡፡ እናቴ ሲጨንቃቸው ጡታቸውን የሚመር የግራዋ ቅጠል ጨምቀው ቀቡት፤ አሁንም አልተው አልኩኝ፡፡ ብዙ ቆይቼ ነው ያቆምኩት፡፡»ጡት መጥባት እንዳቆሙ አጎታቸው በማረፋቸው እና አጎታቸው ወንድ ልጅ ስለሌላቸው በባህሉ መሰረት ቤተሰብ ደግሞ የሚወከለው በወንድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዶክተር ነጋሶ ለአጎታቸው ቤተሰብ ተሰጡ፡፡
የትምህርት ሕይወት
ትምህርት ቤት ሳይገቡ ሀሙስ ሀሙስ ሚሲዮናውያን የአካባቢውን ልጆች ይጋብዞቸው ነበር፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፣ ፀሎት እና መዝሙርም ያስጠኗቸዋል፡፡ ስለ ትምህርት አጀማመራቸው ዶክተር ነጋሶ ሲያስረዱ «መጀመሪያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት አልገባሁም፡፡ ደምቢ ዶሎ የቤተል ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት ተቋቁሞ ስለነበር ስድስት ዓመት ሲሞላኝ እዚያ ገባሁ፡፡ በትምህርት ቤታችን የጉራጌ፣ የአማራ፣ ትግሬ፣ የኤርትራውያንና ሌሎችም ልጆች ነበሩ፤ ልዩነት አልነበረም፡፡»
ሀ ሁ… ያስተማሯቸው አባታቸው ናቸው:: አባታቸው ዶክተር ነጋሶን ብቻ ሳይሆን የልጅነት ጓደኞቻቸውን እነደገመኝ ዳቃ፣ ክፍሌ ወሰኑን ፊደል አስተምረዋቸዋል፡፡ ዶሎ የቤተል ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት እየተማሩ ባሉበት ወቅት ጃነሆይ ይመጣሉ ተብለው ተሰልፈው ወደ አውራጃ ጽሕፈት ቤት ሄዱ፡፡ ሁኔታውን ሲያስረዱ ‘ኃይለሥላሴ ድል አድራጊው ንጉሣችን…’ እያልን በስሜት እየዘመርን ከስድስት ሰዓት በፊት ደረስን፡፡ ንጉሡ ግን ሳይመጡ ቀሩ፤ እኛም እግራችን እስኪቃጠል ድረስ ከጠበቅናቸው በኋላ ወደ ቤታችሁ ሂዱ ስለተባልን ንጉሡን ሳናገኝ ተመለስን።»
ትምህርት ቤቱ ሲዘጋ የእርሳቸውም ትምህርት አብሮ ተዘግቶ እንደነበር በዛው መጽሐፍ ላይ ገልጸዋል። ከወራት በኋላ ግን ብርሃን ኢየሱስ የሚባል ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ በዛም ሁለተኛ ክፍል እየተማሩ ሳለ አባታቸው ከአዲስ አበባ ተመልሰው መጡ፡፡ በወቅቱ ሚዛን ተፈሪ የአሜሪካን ሚሲዮኖች ሥራ ጀምረው ስለነበር ቤተክርስቲያን ለማቋቋም ቄስ ፈልገው ለቤተክርስትያኒቱ ደብዳቤ ጽፈው «ቄስ ላኩልን» አሉ። በዚህ አጋጣሚ አባታቸው ወደ ማጂ ዞን የድሮ ጊሜራ ዞን ዋና ከተማ ሚዛን ተፈሪ እንዲሄዱ ተመረጡ፡፡
ሚዛን ተፈሪ የቤንች ማጂ ዋና ከተማ ነበረች፤ አማርኛ ይነገርባታል። እናም ከአባታቸው ጋር ወደዛ ያቀኑት ዶክተር ነጋሶ በቆይታቸው አማርኛ እየለመዱ መጡ፡፡ ከቋንቋው ጋር ብቻ ሳይሆን የቤንችንና ከፊቾን ባህል ተላመዱ፡ ፡ከሌሎችም ጋር መግባባት ጀመሩ፡፡ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት አኗኗር ማህበረሰብን የሚያስተሳስር ገመድ ነውና በዚህ መካከል ተሳስረው ይኖሩ ነበር፤ መለያየት አልነበረም፡፡
«ደምቢ ዶሎ እያለሁ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ኤርትራዊና ሌሎችም ነበሩ፡፡ቤተሰቦቼ መጀመሪያ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡ የአባቴ የክርስትና ስም ወልደ ገብርኤል፣ የእናቴ ደግሞ ወለተ ገብርኤል ነበር፡፡ የእህቴና የእናቴ ክርስትና እናት እታፈራሁ የሚባሉ ጎንደሬ ናቸው፡፡» ብለዋል።
ዶክተር ነጋሶ ስምንተኛ ክፍል ፈተና እስከሚፈተኑ ድረስ አባታቸው በሄዱበት እየተዘዋወሩ ነው ትምህርታቸውን የተከታተሉት፡፡ ከዘጠነኛ እስከ አሥራ አንደኛ ክፍል እየሰሩ እንደተማሩም ይናገራሉ። ከዚያም አሥራ ሁለተኛ ክፍል የመግቢያ ፈተና በመፈተን በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት መግባት ቻሉ፡፡
«የአባቴ ልጅ ነኝ፤ በእርሳቸው ነው የወጣሁት» የሚሉት ዶክተር ነጋሶ፤ ስለያዙት ስብዕና፣ ባህሪና ጥንካሬ ሲያብራሩ ከአባታቸው ከቄስ ጊዳዳ ሶለን እንዳገኙት ይገልጻሉ፡፡ ገና በአምስት ዓመታቸው ዓይነስውር በመሆን የህይወትን ከባድ ፈተና የተቀበሉት ቄስ ጊዳዳ ከልመና ወጥተው የታወቁ ቄስ ሰባኪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በቄስ ጊዳዳ ስብዕናና ብርታት የተደመሙ የውጭ አገር ዜጎች ታሪካቸውን ፅፈው አሳትመውላቸዋል፡፡ የዶክተር ነጋሶ አባት ቄስ ጊዳዳ ሶለን የታወቁ የፕሮቴስታንት ቄስ ነበሩ፡፡ የቤቴል ቤተክርስቲን መስራቾች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡
የፖለቲካ ሀ ሁ …
ዶክተር ነገሶ በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል ማግኘታቸው ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር የመገናኘትና የመወያየት ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ ስለዓለም ታላላቅ አብዮቶች የተማሩትም በዚህ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የስነ ግጥምና ሌሎች ፕሮግራሞች ላይ ይገኙ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ወጣቱ ነጋሶን ከፖለቲካ ጋር በማስተዋወቅ የላቀ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ከፖለቲካ ሕይወት ጅማሮ ጋር በተያያዘ እዚያው በዕደማርያም ትምህርት ቤት ውስጥ አስተዳደር እና ሌላ ኃላፊነት ውስጥ የሚሰሩ ዶክተር ጥላሁን ገሞታ ፤ ጉታ ሰርኔሳ እና ሌሎች ተማሪዎች እንደነበሩ ዶክተረ ነጋሶ ስለህይወት መንገዳቸው በተጻፈው መጽሐፍ አንስተዋል፡፡
«የተማሪዎችን አልጋና ምግብ ቤት ንፅህናውን ይቆጣጠራሉ። አንድ ቀን ጉታ ሰርኔሳ ወደ ቢሮው ይጠራኛል፡፡ ጉድፍ የሚፈልግ ይመስል ፊቴ ላይ ዐይኑን ተከትሎ ‘ነገ እሁድ ነው!’ አለኝ፡፡ ‘አዎን’ አልኩት ‘ነገ አንድ ትልቅ ስብሰባ በጉለሌ ይካሄዳል፤ በዛ ስብሰባ ተማሪዎች እንዲገኙ ጋብዘናል፡፡ ሁሉም ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ አንተስ ብትገኝ?’ አለኝ:: ሌላ ጥያቄ ሳላስከትል ‘ምናልባት እሄድ ይሆናል’ አልኩት። ከጉታ ጋር ፒያሳ ተገናኘንና አብረን ሄድን፡፡
ቦታው ጉለሌ ሙስሊም መቃብር ፊት ለፊት ነበር፡፡ የስብሰባው ቦታ ስንደርስ ግቢው በትርና እርጥብ ሳር የያዙ ሽማግሌዎች፣ ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ወታደሮች… ሁሉ ነበሩ:: መግቢያው ጋር ባለች ጠረጴዛ ላይ ሰዎች ስም ይመዘግባሉ፡፡ ድንኳኑ ውስጥ በኃይል የሚያስተጋባ ድምፅ ይሰማኛል፡፡ ተናጋሪው ማና እንደሆነ አይታየኝም፡፡ ለካ ያ ስብሰባ የተዘጋጀው በሜጫና ቱለማ ማህበር ኖሯል፡፡ ተናጋሪው ጄኔራል ታደሰ ብሩ ናቸው፡፡ አንድ ብር ከፍዬ መታወቂያ ተሰጠኝና አባል ሆኜ ተመለስኩ፡፡»
የፖለቲካ ሀ ሁ ሌላኛው ትውውቅ ነው፡፡ ታዲያ በዕደማርያም ትምህርት ቤት ያላቸውን ቆይታ አጠናቀው የመግቢያ ፈተና በመውሰድ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርታቸውን በ1963 ዓ.ም አጠናቀቁ፡፡
የተማሪዎች ንቅናቄ
በ1960ዎቹ ዓ.ም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአጠቃላይ በዓለም ላይ የተማሪዎች ንቅናቄ ተነስቶ ነበር፡፡የተማሪዎች እና የወጣቶች የለውጥ ፍላጎት የወጣበት ጊዜ ነው፡፡ የዓለም ሕዝቦች፤ የፊውዳል ስርዓት የሚጨቁኑበትና የሚበዘብዙበት ስርአት እንደሆነ በመገንዘብ «ለውጥ መምጣት አለበት፤ በጥቂት ገዥ መደቦች መጨቆንና መበዝበዝ አይገባም፤ ፍትህ ሊኖር ይገባል» የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ ሲታይ ኢምፔሪያሊዝም የሰፈነበት ወቅት ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ስለነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ዶክተር ነጋሶ በመጽሐፋቸው ሲያስታውሱ «ንቅናቄውን የሚመራው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማህበር ምክር ቤት ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ለመግባት ከፍተኛ ውድድር ይካሄዳል፡፡ ብቃትና ንቃት ያለው ሰው ነበር የሚመረጠው፡፡ አንዴ ጥላሁን ግዛው ተወዳድሮ ነበር፡፡አርአያ የሆነ ድንቅ ልጅ ነበር:: እርሱን የሚፎካከረው ደግሞ መኮንን ቢሻው የተባለ ልጅ ነበር፤ አሁን ዶክተር ነው:: እና ጥላሁን እንዲመረጥ ስለምንፈልግ ሳያሸንፍ ሲቀር አለቀስን፡፡ይህ ከተከናወነ ሁለት ዓመት በኋላ ጥላሁን በታኅሳስ ወር ተገደለ፡፡ እንቅስቃሴው የሚመራው በምክር ቤቱ ነበር፡፡ ትግሉን የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲ አልነበረም፡፡ ተወካዮቹ አብዮተኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል::»
ታዲያ ዶክተር ነጋሶም ካሉበት ፋካሊቲ ከአንድ ጓደኛቸው ጋር በመሆን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ህብረት ማህበር ምክር ቤት አባል ሆኑ፡፡ በወቅቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ዓላማ የነበረው ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት ሀገር ማድረግ፤ ፈጣን አብዮት ተካሂዶ ለውጡ እንዲመጣ ለጭቁኑ ህብረተሰብ መታገል ነበር::
በወቅቱ ጭቁን የሚባሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ላብአደሮች፣ አርሶአደሮች፣ ሴቶች፣ ጭቁን ብሔረሰቦች፣ ጭቁን ሃይማኖቶች… ሲሆኑ ዶክተር ነጋሶ እና ጓደኞቻቸው ይህንን ጭቆናን ለማስወገድና የነበሩባቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸው ከፈለጉ ተደራጅተው መታገል አለባቸው፤ ሲሉ ነበር።
የቤተሰብ ህይወት
ዶክተር ነጋሶ ጥቅምት 1967 ዓ.ም ወደ ጀርመን ሲጓዙ ቤተሰባቸውን ይዘው ለመሄድ አስበው ነበር፡፡ሆኖም ለመውለድ አንድ ወር የቀራቸውን ባለቤታቸውን በአውሮፕላን ማሳፈር ስለማይቻል ከወለዱ በኋላ ከነልጆቻቸው ይዘው ወደ ጀርመን የሚመጡበትን ሁኔታ አመቻችተው ወደ ጀርመን አቀኑ። ባለቤታቸውም ጃለሌን እንደወለዱ በወሩ ሁለቱን ልጆቻቸውን ኢብሳንና ጀለሌን ይዘው ወደ ጀርመን ሄዱ፡ ፡ ኑሯቸውን የጀመሩት ቦሁሞ በምትባል ግዛት ነበር፤ በኋላም በ1968 ዓ.ም ወደ ፍራንክፈርት መጡ፡፡
ዶክተሩ ስለመጀመሪያ ትዳራቸው ሲናገሩ «… ከባለቤቴ ጋር መስማማት አልቻልንም:: ሁልጊዜ በትንሽ በትልቁ ሥራችን ፀብ ሆነ:: አንዴ ተጣልተን ለየብቻ መኖር ጀምረን ነበር:: በሌላኛው ጊዜም እንዲሁ እኔ ከቤት ወጥቼ የኦነግ መሪዎች ዶክተር ታደሰ ኤባና አቶ ታደሰ ዋቅጂራ አስታረቁን፡፡ ብቻ መስማማት እና በሰላም መኖር አልቻልንም፤ ጀርመን አገር ደግሞ የሴቶች መብት በጣም የሚከበርበት አገር ነው፡፡ የጀርመን ፍርድ ቤት ዳኞች ጉዳያችንን በተገቢ መንገድ ከተመለከቱት በኋላ የፍች ወረቀታችንን ሰጡን፡፡» ሲሉ ያስታውሳሉ።
ከዚያም እዚያው ጀርመን «ሦስተኛ ዓለም ቤት» የተሰኘ ድርጅት ውስጥ እየሰሩ ሳለ የአሁኗ ባለቤታቸው በሩዋናዳ በአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአዋላጅ ነርስነት ሲሰሩ ቆይተው ለትምህርት ወደ ፈራክፈርት ተመለሱ፡፡ ታዲያ ለአፍሪካ ፍቅር ያላቸው እኚህ ሴት ምንም እንኳ ጀርመን የትውልድ አገራቸው ብትሆንም ከአፍሪካውያን ጋር መስራት ውሎ ማደር ሆነ ኑሯቸው፡፡ እናም ይህ ፍቅር እና ውሎ ከዶክተር ነጋሶ ጋር እንዲገናኙ አደረጋቸው፤ተላመዱም። ከ1978 ዓ.ም ጀምሮም አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ተሊሌ የተባለች አንዲት ሴት ልጅም ወልደዋል፡፡
የተማሪዎች አመፅ በጀርመን
ጀርመን እንደነማርክስ ያሉ ዓለማችንን የዘወሩ ፖለቲከኞችን ያፈራች ምድር ናት፡ ፡ የሦስተኛው የዓለም አገራት አብዮተኞች መሰብሰቢያ ማዕከልም ነበረች፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ ትንታግ ወጣቶች ሰልፈኛ የነበሩት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ፤የፖለቲካ ትኩሳት በሚንቀለቀልባት የአመፅ ትግል በሚጠነሰስባት አያሌ ርዕዮተ ዓለም ሃሳቦች በሚፋጩባት ጀርመን ሲከትሙ የአገር ቤቱ የተማሪዎች አብዮት በደርግ እየተዳፈነ ሄደ፡፡ ነጋሶ የለኮሱትን አብዮት ጥለው ባህር ማዶ የተሸገሩት ከትግሉ ሜዳ ለመሸሽ የሚመስላቸው አይጠፉም፡፡ነገር ግን ጀርመንም ቢሆን አብዮቱን እያጧጧፉት ነበር፡፡
ለነገሩ አያሌ የዘመኑ ወጣት አብዮተኞች የአገር ቤት ትግል አላዋጣ ሲላቸው በአየርም በምድርም እያሉ አሜሪካ እና አውሮፓ ሲሰደዱ ትግላቸውንም የመቀጠል ትልማቸውን በልባቸው በመሰነቅ ነበር፡፡ ዶክተር ነጋሶም በአንድ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያን ምድር ለቅቄ ወደ ጀርመን ስበር በአንጎሌ ሻንጣ ውስጥ ብዙ ሃሳቦችን ጠቅጥቄ ነበር ብለዋል፡፡
ኢህአፓ ይበትናቸው የነበሩ ወረቀቶች፣ የአብዮት እንቅስቃሴ በመቋቋም ላይ የነበሩት መኢሶንና ኦነግ በሃሳብ አብረዋቸው ባህር ማዶ ተሻግረዋል፡፡ የተማሪዎች አብዮትን መነሻ በማድረግ የመንግሥት ስልጣንን የተረከበው የደርግ አስተዳደር አፍታም ሳይቆይ ወደ አምባገነንነት መለወጡ ዶክተር ነጋሶን ብቻ ሳይሆን የአገር ቤት ታጋዮችን ሳይቀር ተስፋ ማስቆረጡ አልቀረም፡፡ ይህንን ክፉ ዜና ደግሞ ከአገር ርቆ መስማት ስቃዩን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡
በጀርመን የነበሩ የፖለቲካ ማህበራትን የዶክተር ነጋሶን ያህል አበጥሮ የሚያውቅ እምብዛም አይገኝም፡፡በጀርመን ለቁጥር የሚያዳግቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተዋል፤ ፈርሰዋልም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ፍጭት ከባድ ነበር፡፡ ታዲያ ዶክተር ነጋሶም አንጀታቸውን የሚያርስ የፖለቲካ ፓርቲ አጡ:: ያልገቡበት ፖለቲካ ድርጅት ፣ሊያስማሙ ያልሞከሩት ማህበር የለም፡፡ በዚህ ላይ የውጭ አገር ኑሮ ሰልችቷቸዋል፡፡ አገር ቤት ወደነበረው ተጨባጭ ትግል ለመግባት ቋምጠዋል፡፡
የአገራቸውን ምድር ለመርገጥ ድልድይ የሆናቸው ታዲያ ኢህአዴግ ነበር፡፡ ዶክተር ነጋሶ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ በመሻገር ከኢህአዴግ ጋር ተቀላቅለው ለአገራቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ተጣድፈዋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ጥቂት ፈተናዎችና መሰናክሎች ይጠብቃቸዋል፡፡ በአውሮፓ ሲወራ የሰሙትን «ኦህዴድ የህውሃት አሽከር ነው» የሚል አሉባልታውን ራሳቸው ፈትሸው ማረጋገጥ ነበረባቸው፡፡ የኦነግና ኦህዴድ ፍጥጫም የፖለቲካ መንገዳቸውን ቀና አያደርግላቸውም:: ወደ ፊትም የሚጠብቃቸውን የፖለቲካ ሕይወት እሾህ የበዛበት ቢሆንም ወደ ፈተናው የገቡት ግን በደስታ ነበር፡፡
በኩረ ስልጣን
በ1983 ዓ.ም የመጀመሪያ የመንግሥት ሥራቸውን በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርነት የጀመሩት ዶክተር ነጋሶ ለአንድ ዓመት በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርነት ካገለገሉ በኋላ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስትር ተዘዋወሩ፡፡ እዚያም ቢሆን ከችግር እና ውጣ ውረድ አልዳኑም፡፡
ዶክተር ነጋሶ ነገሩን ሲያስታውሱ «በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ያሉ አብዛኛው ኃላፊዎችና ሠራተኞች ታጋይ በመሆኔ ፈተናውን አክብዶውብኝ ነበር» ይላሉ፡፡ ዶክተር ነጋሶ ከሠሯቸው ሥራዎች አንዱ ህገ መንግሥት ማርቀቅ ነው፡፡ በሽግግሩ ዘመን ሕገመንግሥት ሲረቅ በአርቃቂው ኮሚሽን ውስጥ ከተካተቱ ሰዎች መካከል ዶክተር ነጋሶ አንዱ ነበሩ፡ ፡ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ የኃይለ ሥላሴንና የደርግን እንዲሁም የዳበረ ዴሞክራሲ ባህል አላቸው የሚባሉ አገራት ሕገ መንግሥቶች እንደተመለከቱት የሚናገሩት ዶክተር ነጋሶ፤ በሕገ መንግሥት ዙሪያ ዕውቀት ያላቸው የውጭ ባለሙያዎች ጽሑፍ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ፡ ፡ በፓርላማም ውይይት ክርክርም ተደርጓል፡፡
ሕይወት በቤተ መንግሥት
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው እንደተሾሙ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በአጀብ ወደ ቤተ መንግሥት ገቡ። ከቤተሰቦቻቸው ጋር የቤተ መንግሥት ህይወትን ገና ሀ ብለው ሲጀምሩ መኖሪያ ቤታቸው ዝናብ ሲጥል በማፍሰሱ አይጥ ወደሚንሸራሸርበት ቤት መዘዋወራቸውን የህይወት ታሪካቸው በተጻፈበት መጽሐፍ ላይ ገልጸዋል፡፡ የቤተ መንግሥቱ መኖሪያ ከአንድ የእንግሊዝ ባለሀብት መኖሪያ እንደማይበልጥ የሚናገሩት ዶክተር ነጋሶ፤ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ አዲስ የፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት እንዲሰራ አዲስ ዲዛይን የወጣ ቢሆንም ሲጀምር እንደተስተጓጎለ ይገልጻሉ፡፡
ዶክተር ነጋሶ አሉ «እኔ ቤተ መንግሥት ብገባም ግቢው ሙሉ ለሙሉ የማዝበት አልነበረም፡፡»
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሠሩ የኢትዮጵያን አምባሳደሮች መሾም፣ የውጭ አገር አምባሳደሮች ሲመጡ መቀበል ፤የሥራ ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ ደግሞ መሸኘት ነበር። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ልዑካንን ማነጋገር ከአገሪቱ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲመሰርቱ በማድረግ ጥረት አድርገዋል፤ ነገር ግን ብዙ ፈተናዎች ገጥሟቸዋል፡፡
ነጋሶ ስለ ሕይወታቸው በተጻፈው መጽሐፍ ራዕያቸውን ተናግረዋል፡፡ «የእኔ ራዕይ ኢትዮጵያ የነጻ ዜጎች አገር እንድትሆን ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ የተከበረላቸው፣ የስልጣን ባለቤትነታቸው በምንም ዓይነት መንገድና ሁኔታ ያልተገደበ ዜጎች፣ አስተዳደራዊ፣ ህጋዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በየትም ቦታ በሚገባቸው ቋንቋ የሚያገኙ ዜጎች፣ በየትምህርት ቤቱ ከአፍ መፍቻ በተጨማሪ ከሌሎች ጋር ለመግባባትና ለኑሮ ይረዱኛል የሚሉትን ቋንቋዎች ሁሉ በፍላጎታቸው የሚማሩበት ዕድል ያላቸው የነፃ ዜጎች አገር እንድትሆን ነው፡፡» እናም እኛም የእኚህን ቅንና ጀግና የአገር ባለውለታ ራዕይ የሚያሳካ ትውልድ እንዲፈጠር ምኞታችን ነው፡ ፡
ዶክተር ነጋሶ በጀርመን ሀገር ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ከሰማን ቀናት ተቆጥረዋል። ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ርዕስ ብሄር በመሆን በ1987 የተሾሙ ሲሆን፤ ለ7 ዓመታትም ማገልገላቸው ይታወሳል። በታሪክ ትምህርት ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፤ እንደ ምሁርነታቸው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራትም የተለያዩ ግልጋሎቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል። በተማሩት ትምህርትም የኦሮሞን ባህል፣ ታሪክ እና እሴት የሚያንፀባርቁ እና የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ጥናቶችን አካሂደዋል። ስርዓተ ቀብራቸው ዛሬ በጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ይካሄዳል፡፡ እኛም የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን እየገለጸን አፈሩን ያቅልላቸው እንላለን:: ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
በአብረሃም ተወልደ