የክርክሩ መነሻ
ክርክሩ የተጀመረው በባህርዳር ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። ዮቴክ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በደል ደርሶብኛል ሲል በነገረ ፈጁ በኩል ለፍርድ ቤት አቤት ብሏል። አቶ ገብሬ በላይነህ፣ አቶ ግርማ ስንታየሁ፣ አቶ አበጀ ካሴ፣ አቶ መጣለም ገነት እና ወይዘሮ ገበያነሽ መኮንን ደግሞ በዚህ መዝገብ በዳይ ተብለው በመዝገብ ቁጥር 87338 የክስ ፋይል ተከፍቶባቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ችሎቱም ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም የመጨረሻውን ፍርድ የሚሰጥ በመሆኑ የችሎት ታዳሚዎች እና ባለጉዳዮች ግራ ቀኝ ከችሎቱ ፊት ለፊት ተቀምጠዋል። ጉዳዩም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት የቀን ሰራተኛ ሆነው የተቀጠሩ ሰራተኞች የሳምንት እረፍት ቀናት የዓመት እረፍት ቀናት እና የህዝብ በዓላት ቀናት ክፍያ ሊያገኙ የሚችሉበት ሕጋዊ አግባብ እያለ መብታችን ተነፍጓል በሚል የተጀመረ ክርክር ነው።
የክሱ ይዘት
የክስ ይዘትም በአመልካች ድርጅት በተለያየ ጊዜ በግንበኝነትና በአናፂነት ስራ ተቀጥረው በመስራት ላይ መሆናቸውንና ያገለገሉበትን ጊዜ ጠቅሰው በስራ ላይ በቆዩባቸው ጊዜያት ያልተጠቀሙበት የዓመት ፈቃድ የነበራቸው ከመሆኑም በተጨማሪ የሳምንት እረፍት የህዝብ በዓላት የሰሩበት ታስቦ ያልተከፈላቸው መሆኑን፣ ካሌንደሩ የማይዘጋቸው ቀናትም ያላአግባብ ተዘግተው ስራ ሳይሰሩ የቀሩ መሆኑን ጠቅሰው ለእያንዳንዳቸው ገንዘቡ እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
ዮቴክ ኮንስትራክሽንም ለክሱ በሰጠው መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና የፍሬ ነገር ክርክር አቅርቧል። ዮቴክ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ገልፆ የተከራከረው ጉዳዩ የወል የስራ ክርክር በመሆኑ በፍርድ ቤት ሊታይ የሚገባው አይደለም፣ ይህ ከታለፈም ክሱ በይርጋ የታገደ ነው የሚል ነው። በፍሬ ነገር ረገድም ተጠሪዎች በቀን የሚከፈላቸው ክፍያ በክሳቸው ላይ ያቀረቧቸው የክፍያ ጥያቄዎችን ክፍያ ከግምት ውስጥ አስገብቶና አጠቃልሎ የያዘ በመሆኑ የተለየ ክፍያ ሊኖር የሚችል ስለመሆኑ የሚሰራበት መሆኑንና በቅጥር ውሉ ላይ የተለየ እንደማይደረግ እና ክፍያ የሚፈፀምላቸው በካርዳቸው ላይ ስራ የተሰራባቸው ቀናት ተቆጥረው ስራ ለተሰራበት ቀን ብቻ እንደሚከፈል የተስማሙ ስለሆነ ጥያቄው አግባብነት የለውም በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ በአመልካች በኩል የቀረቡትን መከራከሪያ ነጥቦችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረገ። ድርጅቱ ለከሳሾች የሳምንት እረፍት፣ የሕዝብ በዓላት እና የዓመት እረፍት ክፍያ በገንዘብ ተለውጦ እንዲከፍል ሲል ወሰነ። በዚህ ውሳኔ ዮቴክ ኮንስትራክሽን ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪዎች በቀን በሰሩት ስራ መጠን ታስቦ ክፍያ የሚፈፀምላቸው በመሆኑ የጠየቁትን የክፍያ ዓይነቶች ሊያገኙ አይችሉም በማለት የወረዳው ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ይሽረዋል። እንግዲህ የሥር ፍርድ ቤት የቀን ሰራተኞቹ ያቀረቡት ቅሬታ አግባብነት አለው፤ ሲል ዞኑ ደግሞ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር የተለያየ ውሳኔ ያሳልፋሉ። ይህ ነገሩን የበለጠ እንዲካረር አደረገው።
በዚህን ጊዜ የቀን ሰራተኞቹ የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ ክርክሩ የግል የስራ ክርክር በመሆኑ በመደበኛ ፍርድ ቤት መታየቱ ተገቢ መሆኑን፣ ተጠሪዎች በቀን በሰሩት ታስቦ በወር የደመወዝ ክፍያ የሚከፈላቸው መሆኑ የተረጋገጠ መሆኑን በምክንያትነት ይዞና የሕጉ ጥያቄ ከኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ሆነ ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንፃር ሲታይ ለክሱ መሰረት የሆኑትን የመብት ጥያቄዎች ተጠሪዎች ለመጠየቅ የማይችሉበት ሕጋዊ ምክንያት የለም የሚለውን አስቀመጠ።
በመቀጠል የቀን ሰራተኞቹ የሳምንት እረፍት ጊዜ፣ የሕዝብ በዓላትና በካሌንደሩ ላልተዘጉት ቀናት ክፍያ እንደሚገባቸው፣ የዓመት የረፍት ጊዜያት ግን የስራ ውሉ ባልተቋረጠበት ሁኔታ በገንዘብ ተቀይሮ ይከፈልን በማለት መጠየቅ የማይችሉ መሆናቸውን ዘርዝሮ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የወረዳው ፍርድ ቤት የሠጠውን ውሳኔ በማሻሻል ሊስማማ ወይንም ሊያቀራርብ የሚችል ውሳኔ አስተላለፈ።
ሰበር
ጉዳዩ ወደ ሰበር አቤቱታ ያመራው ከላይ የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ በማሰብ ነበር። የሜቴክ አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የቀን ሰራተኞቹ ጥያቄ ከራሳቸው አልፎ ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተቀጥረው የሚሰሩትን በርካታ ሰራተኞችን ተመሳሳይ ጥያቄ እንዲያነሱ የሚያደርግ ሆኖ እያለ ክርክሩ የግል የስራ ክርክር መባሉ ያላግባብ ነው ሲል ተቃወመ። የቀን ሰራተኞቹ በስራ ላይ በቆዩባቸው ከሦስት ዓመታት የሚበልጥ ጊዜ ለሰሩባቸው ቀናት ብቻ እየታሰበ ሲከፈላቸው የነበረ መሆኑን፣ በቀን ታስቦ የሚከፈለው ገንዘብ የእሁድና የበዓላት ቀናትን የሚያጠቃልል መሆኑን ስራ ሲጀምሩ በተደረገው የስራ ውል ተስማምተው ክፍያው በዚሁ መልክ ሲፈፀም እና እየተሰራበት ያለ ሆኖ የቀን ሰራተኞቹ የተጠየቁት ክፍያዎች እንዲከፈሉ መወሰኑ ያለግባብ ነው በማለት አቤቱታ አቀረበ።
የጉዳዩ አመጣጥ ከስር መሰረቱ የመረመረው ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች እና በሁለቱም ወገኖች ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መረመረው።
ችሎቱም በምርመራው ከሳሾች የተጠየቁት የበአላት፣ የሳምንት እረፍትና የዓመት እረፍት ክፍያዎች አመልካች በስራ ላይ ተጠሪዎች ላሳለፉት ቀናት ብቻ እንጂ እነዚህን ክፍያ ሊፈጸም አይገባም፣ ተጠሪዎች ከሶስት ዓመት በላይ በሰሩበት ጊዜም እነዚህን ጥቅማ ጥቅሞች ጠይቀው አያውቁም በማለት ያቀረበው ክርክር ውድቅ መደረጉ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን መረመረ።
በክርክሩ ሂደትም መገንዘብ የተቻለው ዮቴክ በኮንስትራክሽን ሥራ የተሰማራና ተጠሪዎችን ቀጥሮ ሲያሰራ የነበረው በግንበኝነትና በአናፂነት ስራ መሆኑን፣ አመልካች ለተጠሪዎች ለቀን ስራ የሚያስበው የደመወዝ መጠን የተለያየ ሆኖ አከፋፈሉ ግን በወር ተጠቃልሎ በፔሮል የሚከፈል መሆኑን ተደረሰበት። በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ ሲታይ ደግሞ በአጠቃላይ የቅጥር ውል አይነቶች ለተወሰነ ሥራ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ሊደረግ የሚችሉ ናቸው። ከዚህ አኳያ ሕጉ የቅጥር ውል አይነቱ ቋሚም ይሁን ጊዜያዊ ለሰራተኛው በሕጉ የተፈቀዱ ጥቅሞችና ከለላዎች የቅጥሩ አይነት መሰረት ተደርጎ ልዩነት ማድረግ የማይቻል መሆኑን ያብራራል። በመሆኑም ጊዚያዊ ሰራተኞችም ሆነ ቋሚ ሰራተኞች በሕጉ የተጠበቁላቸውን ጥቅማጥቅሞችንና ከለላዎችን እንደሚያገኙ የህጉ ይዘትና መንፈስ ያሳያል ሲል የምርመራ ውጤት ግኝቱን አስቀመጠ።
የአገሪቱ ሕገ መንግስት አንቀጽ 42(2) ድንጋጌ ሲታይ ደግሞ ሰራተኞች በአግባቡ የተወሰነ የስራ ሰዓት እረፍት፣ የመዝናኛ ጊዜ፣ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የእረፍት ቀኖች፣ ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በዓላት እንዲሁም ጤናማና አደጋ የማያደርስ የስራ አካባቢ የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኖ ተገኘ። ይህ ህግ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግስት ድንጋጌ እነዚህን ጥቅሞችና ከለላዎችን የሚያገኙትን ሰራተኞች ብሎ በጥቅሉ ከማስቀመጥ ባለፈ የቅጥር አይነቱን ለይቶ አላሰፈረም።
በመሆኑም ጊዜያዊ ሰራተኞችም ቢሆኑ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡትን ጥቅሞችና ከለላዎች ተጠቃሚ የማይሆኑበት አግባብ የለም ሲልም አስረግጦ የህግ ክፍተት አለመኖሩን አስቀመጠ። ዮቴክ ኮንስትራክሽን አምስቱን ግለሰቦች የቀጠረው በኮንስትራክሽን ስራ መሆኑ ከተረጋገጠ የቅጥሩ ዓይነት ለተወሰነ ሥራና ጊዜ የተቀጠሩ መሆናቸው ግልፅ ቢሆንም በሕጉ የተጠበቁላቸውንና የተቀመጡላቸውን ጥቅሞች ከለላዎች ተጠቃሚ የማይሆኑበት ምክንያት የለም።
ከዚህ አንፃር ሲታይ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ፤ ‹‹አምስቱ ግለሰቦች የመብቶቹ ተጠቃሚ የማይሆኑበት ሕጋዊ ምክንያት የለም በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ሕጋዊ ሆኖ አግኝተናል›› ሲል ደመደመ። ሌላኛው ከጊዜ ጋር በማያያዝ የሚያሳየው ክርክር ሲታይ አምስቱ ግለሰቦች በአመልካች ድርጅት ከሦስት ዓመታት በላይ ሲሰሩ የጥቅማ ጥቅሞችን ጥያቄ አንስተው ያለማወቃቸው የሚገልፅ ሲሆን እንዲህ መሆኑ ተጠሪዎች ጥያቄውን ከነጭራሹ እንዳይጠይቁ የማድረግ ሕጋዊ ውጤት የለውም በማለት ጉዳዩ በሦስት ዓመት ውስጥ በይርጋ የማይታለፍ መሆኑን አመላከተ። ምክንያቱም ደግሞ በሕጉ ተለይቶ የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ጥቅማ ጥቅሞችን ከማግኘት የሚያግዳቸው ከሚሆን በስተቀር የአመልካችን እርምጃ ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ ሊያደርግ የሚችልበት ሕጋዊ አግባብ የሌለ መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 162 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻል መሆኑንም በዝርዝር አስቀመጠው።
በመሆኑም ዮቴክ ኮንስትራክሽን የቀን ሰራተኞቹ ለሦስት ዓመታት ያህል ጥያቄውን አላቀረቡም የሚለው ክርክር ተጠሪዎች ጥያቄውን ለማንሳት አይችሉም ለማለት የማያስችለው ህጋዊ መሰረት የለም። ይህም ብቻ ሳይሆን የሥር ፍርድ ቤቶችም በይርጋ የማይታገዱትን ክፍያዎች ለይተው የወሰኑ በመሆኑ በዚህ ረገድም የሕግ ስህተት የለም ሲል ቅልብጭ አድርጎ አስቀመጠ።
የዓመት እረፍትን በተመለከተም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ለተጠሪዎች እንደሚገባቸው፣ ግን የዓመት እረፍቱን መጠቀም ሲገባቸው በስራ ላይ እያሉ በገንዘብ ተቀይሮ እንዲከፈላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 77(5) ድንጋጌ አንፃር ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልፆ መወሰኑ ሕጋዊ እንጂ የሚነቀፍ አለመሆኑንም አስረግጦ አስቀመጠ።
ተከሳሾች ስራ ለመስራት ዝግጁ ሆነው ሳለ ዮቴክ ኮንስትራክሽን ስራ የመስጠት ግዴታውን ያለመወጣቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ለእነዚህ ቀናት ደመወዝ የመክፈል ሕጋዊ ኃላፊነት የሚያስከትልበት ስለመሆኑ ከላይ ከተጠቀሰው አዋጅ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም በዚህ ረገድ የተሰጠው ውሳኔም ነቀፌታ የሚቀርብበት አይደለም ሲል የሥር ፍርድ ቤቶቹ ያሳለፉትን ውሳኔ አግባብነት ያለው ስለመሆኑም በድጋሚ አረጋገጠ።
በአጠቃላይ የድምር ውጤት ሲታይም አምስቱ የቀን ሰራተኞች ለተወሰነ ስራ የተቀጠሩና ደመወዝ በቀን ሂሳብ ታስቦ በወር የሚከፈላቸው ቢሆንም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 ለማንኛውም ሰራተኛ የተጠበቁትን ጥቅማጥቅሞችንና ከለላዎች የማግኘት መብታቸውን የሚነፈጉበት ሕጋዊ መሰረት የሌለ መሆኑን ሰበር በይፋ አስቀመጠ። በይርጋ ያልታገዱትን ጥቅማ ጥቅሞችን ብቻ በመለየት አምስት ተከሳሾች (ተጠሪዎች) እንዲያገኙ ተብሎ በተሰጠው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሌለበት መሆኑ ሰበር በማያወላዳ በማስቀመጥ ውሳኔ አስተላለፈ።
ውሳኔ
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 24912 ጥር 06 ቀን 2005 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ በፍትሃብሄር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 348(1) መሰረት የታየ ሲሆን፤ አምስት ግለሰቦች በቀን ሂሳብ ታስቦ በወር ደመወዝ የሚከፈላቸው ለተወሰነ ስራ የተቀጠሩ ሰራተኞች ቢሆንም የሳምንት እረፍት፣ የሕዝብ በዓላት እረፍት ደመወዝ ክፍያ የማግኘት፣ የዓመት እረፍት የማግኘትና ያለካሌንደር የተዘጉ ቀናት ክፍያ ደመወዝ የማግኘት መብት አላቸው ተብሎ መወሰኑ ተገቢ ነው ሲልም የመጨረሻውን ውሳኔ አስተላለፈ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015