
የዘንድሮው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ”የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል ለ7ኛ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል። የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው 132 ሺህ 144 የመንግሥት፣ የግል እና የህብረት ሥራ ማኅበራት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ችግኞችን አዘጋጅተዋል። ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለተከላ ተዘጋጅቷል። 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የቅድመ-ተከላ ዝግጅቶች በሁሉም አካባቢዎች ተሠርቷል።
25 በመቶ የሚሆነው ችግኝ በዓባይ ወንዝ ተፋሰሶች ላይ የሚተከል ሲሆን 6 ሺህ 200 ተፋሰሶች በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኞች የሚሸፈኑ ይሆናል። ባለፈው ዓመት መርሐ-ግብር 60 በመቶ የጥምር ደን እርሻ ችግኞች፣ 35 በመቶ የደን ችግኞች እንዲሁም 5 በመቶ ለከተማ ውበት የሚውሉ ችግኞች ተተክለዋል።
በእዚህ ዓመት ደግሞ 43 ነጥብ 9 በመቶ ለደን እና ለውበት፣ 56 ነጥብ 1 በመቶ ደግሞ ለጥምር ደን እርሻ (ለፍራፍሬ እና ለመኖ) ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ። ካለፉት ዓመታት አፈጻጸሞች በመማር ዘንድሮ ተከላ የሚካሄድበትን መሬት በካርታ የመለየት ሥራ የተሠራ ሲሆን በዚህም ለ 822 ሺህ 711 ሄክታር መሬት ካርታ (ጂኦ ሪፈረንስ) ተዘጋጅቷል።
ይኸው የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚገልጸው ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለው 90 በመቶው ጸድቋል። በተመድ የአካባቢ ጥበቃ ኮንቬንሽን መስፈርት መሠረት በ 2011 ዓ.ም 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን፣ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በተሠራው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በአሁኑ ጊዜ 23 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል።
በ 2022 ይህን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የደን ውድመት ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 27 ሺ ሄክታር ቀንሷል። የደን ጭፍጨፋን መቀነስ መቻሉ እና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ተጨማሪ መትከል መቻሉ የደን ሽፋኑ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በዘንድሮው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያ የደን ልማት የአረንጓዴ ዐሻራና ሰው ሠራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑት ከአቶ አበሩ ጠና ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች እንደ ሀገር ምን ዓይነት ፋይዳ አስገኙ?
አቶ አበሩ፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ዘንድሮ ሰባተኛ ዓመታችንን ይዘናል ፤ በእነዚህ ጊዜያት 40 ቢሊዮን ገደማ ችግኞችን ተክለናል፤ እነዚህ የተተከሉ ችግኞች ደግሞ በርካታ ሀገራዊ ጥቅሞችን አስገኝተዋል። ከጥቅሞቹ መካከልም ለምሳሌ የአካባቢ ጥበቃና ሥነ ምህዳርን ከማሻሻል ጋር ተያይዞ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የአፈር መሸርሸርና የጎርፍ አደጋ እንዲቀንስ ከማድረግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በሌላ በኩልም የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን በማሳደግ በኩልም ከፍተኛ ሚናን የሚጫወቱ ናቸው። ሌሎች ለውጦች በጥናት የሚመለሱ ቢሆንም እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የሚያሳየው ይህንን ነው። የደን ሽፋንን ከማስፋት የብዝሃ ሕይወት እንዲያገግም ከማድረግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
ሌላው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ለጥምር እርሻ ፋይዳ ያላቸውን ችግኞች በመትከል የማህበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ከመቀየርና ከማሳደግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው ማለት ይቻላል። በተለይም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት መሠረት የምንጥልበት ነው። እንግዲህ ችግኝ በማፍላት፤ በመትከልና በመንከባከብ ሥራዎችም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠሩም ከፋይዳዎቹ ትልቁ ሲሆን በቀጣይም ለእንጨት ኢንዱስትሪ ለፍራፍሬ ማቀነባበሪያና ለሌሎች ሥራዎች ሀብት የምንፈጥርበትና ዝግጅት የምናደርግበት ነው።
ከማህበራዊ ጠቀሜታ አንጻርም በሕዝቡ ዘንድ የአካባቢ ጥበቃ ባህል እንዲዳብር የዓላማ ጽናት እንዲፈጠር የማድረግም እገዛ አድርጓል። በተለይም የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ባህል እንዲሆን አካባቢን ካልጠበቅን ወደፊት የምናስባቸው ሥራዎችና አሁን የኢኮኖሚያችን መሠረት የሆነው የግብርና ሥራውም ውጤት እንደማያመጣ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።
በጠቅላላው ግን እስከ አሁን የተተከሉት ችግኞች የአካባቢን ገጽታ ከመቀየርና ሥነ ምህዳሩን ጤናማ ከማድረግ አንጻር የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥም ሌላው ሲሆን ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራም መሆኑ በማህበራዊ መስኩ ያበረከተው ፋይዳ ነው።
ሀገራዊ አንድነትና ሕዝባዊ ተሳትፎን በማጠናከር በኩልም የሚኖራቸው ሚና ቀላል ካለመሆኑም በላይ ይህንንም በባለፉት 6 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዓመታት ያየነው ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ኢትዮጵያ ግዙፍ ወደ ሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እንድትገባ አስገዳጅ የሆኑ ምክንያቶች ምንድነው ናቸው ይላሉ?
አቶ አበሩ፦ በእኛ ሀገር ደረጃ አስገዳጅ ምክንያቶቹ በጣም ብዙ ናቸው። አንዱና ዋናው በሀገር ውስጥ ያለው ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ እሱን ተከትሎ የሚፈጠረው የደን መራቆት የአየር ንብረት ለውጡ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እነዚህ ነገሮች ለመጀመሩ ምክንያት ናቸው።
በሀገራችን 54 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በጣም የተጎዳ ነው ተብሎ ይታሰባል ፤ይህንን መመለስ ካልቻልን ደግሞ ቀጣዩ ትውልድ ለአደጋ ይጋለጣል። ስለሆነ ወደ አረንጓዴ ዐሻራ የልማት ሥራ ለመግባት አንዱ አስገዳጅ ምክንያት ነው።
የአፈር ለምነት በጣም እየቀነሰ ሲሄድ የምርትና ምርታማነትን እየጎዳ በኢኮኖሚው ላይም ትልቅ ጫና እያሳደረ መሄዱ አይቀርምና ይህንን መመለስ ትልቅ ሥራ ነው። ሌላው አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች የድርቅ መከሰት የጎርፍ አደጋ እያስከተሉ በመሆኑ የተጋጋጡ አካባቢዎችና ተራሮች እንዲያገግሙ ማድረግ አማራጭ የሌለው ሥራ በመሆኑ ይህንንም እንደ ምክንያት መያዝ ይቻላል።
ሌላው ዋና ነገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። አብዛኛው አካባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በድርቅ ምክንያት እየተሰደዱ ወደ ከተማ የሚፈልሱበት ሁኔታ አለና እነዚህን ነገሮች ልናስቀር የምንችለው አካባቢውን በማልማት መሆኑም እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
በጠቅላላው እነዚህና ሌሎች ገፊ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ትልቅ ወደ ሆነ አረንጓዴ ዐሻራ ሥራ እንድትገባ ምክንያት ሆኗል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ እስከ አሁን በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ምን ያህል ችግኞች ተተከሉ፤ በዘንድሮ ዓመት መርሃ ግብርስ ምን ያህል ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል?
አቶ አበሩ ፦ የዓባይ ተፋሰስ በኦሮሚያ፤ አማራና ቤኒሻንጉል ክልሎች መካከል ላይ ያለ እንደመሆኑ ሶስቱም ትልልቅ ክልሎች የሚተክሏቸው ችግኞች እንደ ክልሎቹ ስፋት የሚወሰንና በጣም ብዙ ከመሆኑ አንጻር የዓባይ ተፋሰስ ላይ በርከት ያሉ ችግኞች እየተተከሉ ነው ያሉት። ነገር ግን እስከ አሁን ይህንን ያህል ተተክሏል ብሎ በቁጥር ለማስቀመጥ በጣም አስቸጋሪ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም የዓባይ ተፋሰስን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ላይ አተኩሮ ይሠራል። በመሆኑም አካባቢው ላይ በስፋት ሥራዎች እየተሠሩ ነው በሚለው ቢያዝ መልካም ነው። የዘንድሮውም መርሃ ግብር እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ለአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ትኩረትን የሰጠ ነው።
በነገራችን ላይ ሥራዎች የሚሠሩት በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ የግልገል ጊቤ ተፋሰሶችም በራሱ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው። የተፋሰሶቹን እድሜ ከማቆየት አንጻር ተራሮቹ በደንብ መልማት አለባቸው በማለትም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በተለይም ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ በዚህ መጠን ችግኝን መትከል የሚያስገኘው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል ?
አቶ አበሩ፦ ከላይም እንደገለጽኩት በግድቦች ዙሪያ የሚተከሉት ችግኞች የህዳሴ ግድቡን በደለል ከመሞላት ለመታደግ በጣም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በመሆኑም ይህንን በመሥራትም የአፈር መሸርሸርን መከላከል ይቻላል። በሌላ በኩልም የሚተከሉት ችግኞች እዛ አካባቢ ያለውን አፈር በመቀነስ ንጹህ ውሃ ወደ ግድቡ እንዲገባ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ ነው።
በሌላ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ የደን ሽፋኑ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ወደ ግድቡ የሚገባው የውሃ መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይሄዳል። የእኛ ሀገር ኢኮኖሚ ሙሉ ተጽዕኖው ያረፈው በዋናነት ግብርና ላይ ሲሆን ሌላው ደግሞ ሃይል ነው ይህንን በአግባቡ ለመጠቀም ደግሞ ተራሮችን ማልማት የተፋሰስ አካባቢዎችን በአግባቡ መጠበቅ ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም። በዛ መሠረትም እየተሠራበት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ዘንድሮ “በመትከል ማንሰራራት ” በሚል መሪቃል ነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ እየተከናወነ ያለው ይህ መነሻው ምንድን ነው?
አቶ አበሩ፦ ሀገራችን በርካታ ተግዳሮቶች አሉባት። እነዚህን ነገሮች ለማለፍ በተለይም ደግሞ ችግኝ በመትከል ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለማለፍ ተራሮቻችንና የተራቆቱ አካባቢዎቻችንን ችግኝ በመትከል እንዲለሙ ስናደርግ በኢኮኖሚያችን በሥነ ምህዳራችን በሌሎችም ነገሮች ማንሰራራት ይቻላል ለማለት ነው።
ሌላው ኢኮኖሚያዊ ማንሰራራት ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ለብዙ ዜጎች የሥራ እድልን በመፍጠር የዜጎችን ኢኮኖሚና የሀገርን አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ ማንሰራራት በመሆኑ ይህ መሪ ቃል ገላጭ ነው ለማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች ስብጥር ምን ይመስላል?
አቶ አበሩ፦የዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታትም የሚተከሉ ችግኞች የተለያዩ ጥቅሞችን በሚሰጡ ሀገር በቀል ዛፎችን ጨምሮ የውጭ ሀገር ዛፎችም ሲተከሉ ነበር፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የቀርቀሃ ችግኞች ይተከላሉ፤ ለእንስሳት መኖ እንዲሁም አካባቢን ለማስዋብ የሚሆኑ ችግኞች ሁሉ ተተክለዋል፤ ይተከላሉም። 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኙም እነዚህን ሁሉ ያካተተም ነው።
ባህር ዛፍን ለመተካት የሚለው ሃሳብ በተለየ መንገድ ነው መታየት ያለበት። ባሕር ዛፍ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው በተለይም ለሃይል ምንጭነት በመዋል ለማገዶ ለኮንስትራክሽን ግንባታዎችና ከሌሎችም ጥቅሞች አንጻር የማይተካ ሚናን የሚጫወት ነው። ነገር ግን ባሕር ዛፍ የት ቦታ ይተከል የሚለውን ነገር መለየት ግን ያስፈልጋል። ባሕር ዛፍ ፈጣን እድገት ያለው በአጭር ጊዜ ውስጥም የምንፈልግበትን አገልግሎት ሊሰጠን የሚችል ነው፤ በመሆኑም አገልግሎቱን ሳናሳንስ የት ይተከል የሚለውን ግን መመልከት ይገባል።
ምናልባት ባሕር ዛፍ ውሃን ስለሚመጥ የአፈር ለምነትን ስለሚጎዳ በሀገር በቀል ዛፎች መተካቱ አግባብነት ያለው ነው። ስለዚህ ከእነዚህ ችግሮች አንፃር አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሀገር በቀል ዝርያዎች መተካት ተጀምሯል። የሀገር በቀል ዝርያዎች ሥነ ምህዳርን ከመጠበቅ አንፃር ተመራጭ ናቸው።
የአካባቢውን ኢኮሎጂ ባዮ ዳይቨርሲቲ በማመጣጠን ረገድ የማይተካ ሚና ያላቸው ናቸው። ከእዚህ አንፃር የሀገር በቀል ዝርያዎችን የት ቦታ ነው መትከል ማልማት ያለበት የሚለውን መለየት ያስፈልጋል።
ዝም ብሎ በዘፈቀደ በየቦታው መትከል ሳይሆን እዛ አካባቢ ምን መተከል አለበት የሚለውን መለየትና ከተተከሉስ በኋላ ምን ያስገኛሉ የሚለውን በደንብ መለየት ከቻልን ውጤቱንም በዛው ልክ እናየዋለን።
ባሕርዛፍ ሙሉ ለሙሉ ይጠፋል ማለት አይደለም። ለኮንስትራክሽንና ለሃይል ፍጆታ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሥነ ምህዳሩን በማይጎዳ ቦታ የማልማት ሥራ ይቀጥላል፤ ተገቢም ነው። ባህር ዛፍን በሀገር በቀል ለመተካት ሲታሰብ አካባቢው ላይ ያለውን ሥነ ምህዳር ወይም ባዮ ዳይቨርሲቲን አጥፍቷል ወይ የሚለውን ማሰብ ተገቢ ነው። ምናልባትም የእርሻ አካባቢን የአፈር ለምነት ስለሚያጠፋ አካባቢው ላይ በተፈጥሮ ዛፍ መተካት አለበት። ውሃ አካላት አካባቢ ያለውን እርጥበት የመምጠጥ በተወሰነ መልኩ የማድረቅ ሁኔታ ስለሚኖር እሱንም ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ መትከል አለብን የሚል ሃሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ በዘንድሮ የችግኝ ተከላ ምን ያህል አካባቢን ለመሸፈን ታቅዷል?
አቶ አበሩ፦እንደ አጠቃላይ በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ የሚተከል ሲሆን ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬትንም ለመሸፈን ታስቧል። ይህ ማለት ደግሞ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚተገበረውን ጨምሮ ነው። በዚህ መሠረት የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ በታቀደው ልክ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በሚቀጥለው ነሃሴ አጋማሽ ድረስ በተለይም ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በችግኝ የሚሸፈኑ ሲሆን አንዳንድ ክልሎች ደግሞ በተለይም ምስራቁ አካባቢ አፋር፤ ሱማሌ፤ ሀረርን ጨምሮ ዝናብ የሚያገኙት መስከረምና ከዛ በኋላ በመሆኑ የችግኝ ተከላ ሥራውም በዛው ልክ ገፋ ብሎ የሚጀመር ይሆናል።
በጠቅላላው ግን የክረምቱ ወራት እንዳመቸና ዝናቡ እስካለ ድረስ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በሁሉም ክልሎች የችግኝ ተከላውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።
በነገራችን ላይ አራቱ ደቡቦች ከፊል ኦሮሚያና ሲዳማ ከዚህ ቀደምም ችግኝ ተከላ ጀምረዋል።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ ዓመት የችግኝ ተከላ ምን ያህል ሰው ለማሳተፍ እቅድ ተይዟል?
አቶ አበሩ ፦ እንግዲህ እአንደ እኛ ዝግጅት ከባለፉት ዓመታትም የተሻለ የሕዝብ ቁጥር ወጥቶ በፕሮግራሙ ይሳተፋል የሚል ግምት ነው ያለን፤ ነገር ግን ይህንን ያህል ሰው ተሳትፏል ማለት የምንችለው ፕሮግራሙ ሲያልቅ በሚመጣ ሪፖርት ነው።
እንደ አጠቃላይ ግን በዘንደሮው ችግኝ ተከላ ሁሉም ሰው ወጥቶ በሃላፊነት ችግኝ ቢተክል ጠቀሜታው የጋራ ነው። በከዚህ ቀደሙ ልምዳችን እንዳየነው ችግኞች በብዛት ከመትከል ባሻገር የመጽደቅ መጠናቸውንም መጨመር እንደሚያስፈለግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየነና ለእሱም የሚሆን ሥራ እየተሠራ ነው። እዚህ ላይ ገን ሁሉም ሰው እንዲያውቀው የምፈልገው ነገር ቸግኝን በነቂስ ወጥቶ ከመትከል ባሻገር ችግኞች እንዳይፀድቁ ሊያደርጉ ከሚችሉ ምክንያቶች ለምሳሌ በሥርዓት ካለ ማጓጓዝ ከነላሰቲኩ በመትከል፤ በተገቢው መልኩ አለመንከባከብና በሌሎች ችግሮች በመሆኑም ችግኝ ለመትከል ስንወጣ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ታሳቢ በማድረግ ሊሆን ይገባል።
ሌላው ደግሞ የሚተክለው አካል የመጨረሻ ግቡ ማድረግ ያለበት የተተከለው ችግኝ ፀድቆ ለሚፈለገው አገልግሎት መዋሉን በመሆኑ ችግኞቹ ሲተከሉ በቀጣይ ስለሚያደርገው እንክብካቤ አቅዶ የመንከባከብና የማፅደቅ ሃላፊነት መውሰድ አለበት። በእዚህ ክረምት ላይ የተዘጋጁ ችቸግኞች በሙሉ እንዲተከሉ ሁሉም ሰው ሃላፊነት መውሰድ እንዳለበት እንደ ተቋም መናገር እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፦ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ
አቶ አበሩ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም