
ኢትዮጵያ የቆየ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከመሠረተችባቸው ሀገራት አንዷ ፈረንሳይ ነች። የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከ125 ዓመታት በላይ የዘለለ ሲሆን በእነዚህ ዓመታትም ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን አድርገዋል። በአሁኑ ወቅትም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጠንካራ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህንኑ በማስመልከትም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች ፈረንሳይ ኤምባሲ በመገኘት ነባር በሆነው በሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ ከክቡር አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን፡- ክቡር አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ ለቃለ ምልልሱ ጊዜዎን ስለፈቀዱልን በጣም አመሰግናለሁ። ለመጀመር ያህል ከመቶ ዓመታት በላይ ስላስቆጠረው አጠቃላይ የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የረዥም ጊዜ ግንኙነት ሊነግሩን ይችላሉ? ዛሬ ይህ ግንኙነት የደረሰበትን ደረጃ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- አመሰግናለሁ፣ ወደ ፈረንሳይ ኤምባሲ እንኳን በደህና መጣችሁ። ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች ጋር በመነጋገሬም በጣም ክብር ይሰማኛል። የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ግንኙነት በጣም ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ነው። ዕድሜው ከ125 ዓመት በላይ ነው። ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት ሁለተኛ ሀገር ነን፤ በዚህም በጣም እንኮራለን። ረጅም የጋራ ታሪክ አለን።
ከ78 ዓመታት በፊት ከፈረንሣዊው ሊሴ ገብረ ማርያም በጋራ ያቋቋምናቸው በርካታ ተቋማት አሉን እና በጣም እንኮራለን። እኔ በጣም አስፈላጊ የምለው ይህ ግንኙነት ታሪክ ብቻ አይደለም። እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሕያው ግንኙነት፣ በጣም ጥልቅ የሆነ እና የዳበረ ግንኙነት ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው መሪዎቻችን በጣም ሰፋ ያለ እና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ውይይት ማድረጋቸው ነው። ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ታኅሣሥ ወር ከስድስት ወራት በፊት ይህቺን ሀገር የጎበኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ከስድስት ሳምንታት በፊት ወደ ፈረንሳይ ሄደው ነበር።
ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያለው ነው። ግን እሱ ብቻ አይደለም፣ ግንኙነታችንን በጣም ጠንካራ እና አስፈላጊ የሚያደርገው በኩባንያዎች፣ በሕዝብ እና፣ በአካዳሚክ ተቋማት መካከል ያለን ግንኙነት ነው። የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ስኬታማ የሚያደርገውም ያ ነው።
ለእኛ፣ ይህንን ግንኙነት በሕዝብ፣ በኩባንያዎች፣ በሲቪል ማኅበራት ደረጃ ማጠናከር እንደምንችል ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማበረታታት እንሞክራለን። በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር አብረን እንሠራለን። በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ እና በፈረንሳይ የሲቪል ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግም እንሠራለን።
የሲቪል ማኅበረሰብ በሀገሪቱ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በፈረንሣይ እና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ግንኙነት ላይም ለመሥራት እንሞክራለን። ይህም ግንኙነታችን ጠንካራ፣ ጤናማ፣ ዘላቂ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ምርጡ መንገድ እንደሆነ እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ባለቤትነትን ጉዳይ እያነሳ ነው። ታዲያ ይህን ጥያቄ እንዴት ያዩታል? በተለይም ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን እንደገና ለመገንባት ከፍተኛ ፍላጎት ያላት ሲሆን ለዚህም ቀደም ሲል ፈረንሳይ ትልቅ ድጋፍ አድርጋለች። በዚህ ዙሪያ እየተካሄደ ያለ ነገር አለ?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- አንደኛ፣ ምናልባትም በአኅጉሪቱ ትልቋ ወደብ አልባ ሀገር፣ የባሕር መዳረሻ እንዲኖራት መፈለጓ ፍጹም ሕጋዊ ነው። ያ ከዓለም አቀፍ ሕግጋት እና ከጎረቤቶች ጋር በመመካከር እስከተሠራ ድረስ ፍጹም ሕጋዊ የሆነ ነገር ነው። ይህ ፈተና የሆነው እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር ብቻ አይደለም። በአውሮፓ ብዙ የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች አሉን ስለዚህ አስቸጋሪ አይደለም ምክንያቱም በውይይት፣ ከጎረቤቶች ጋር በመመካከር እና በዚህ አይነት የዕለት ተዕለት ግንኙነት በጎረቤቶቻቸው ወደቦች ወደ ባሕር ይደርሳሉ ።
ግን ለማንኛውም እኔ እንዳልኩት የዚህን ጥያቄ ሕጋዊነት በሚገባ ተረድተናል፣ እና በእርግጥ ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው የውይይት አካል ነው፣ እናም ይህ ምኞት በጥሩ ትብብር፣ ከጎረቤቶች ጋር በመመካከር፣ በሰላማዊና ግልጽ በሆነ መንገድ ሊፈታ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ።
የባሕር ኃይልን በተመለከተ የባሕር ኃይል አቅምን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ የቀረበ ጥያቄ ስለነበር ለባሕር ኃይል የተወሰነ ሥልጠና በመስጠታችን ደስተኞች ነን። የባሕር ኃይል ለፈረንሳይ መገለጫዋ የሆነ በጣም አስፈላጊ ተቋም ነው። መጠነኛ ትብብር ነው፣ ነገር ግን በጣም እንኮራበታለን፣ እናም ይህ ውሎ አድሮ ኢትዮጵያ በባሕር ላይ ደኅንነትን በተመለከተ የበኩሏን እንድትወጣ የሚፈቅድላት ይመስለኛል። ስለዚህ አሁን ያለን ግንኙነት ሥልጠና ነው። ይህም አስደሳች ትብብር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም አንዳንድ የኢኮኖሚ ዘርፎቿን ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ አድርጋ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይም ለውጭ ሀገራት እንደ ባንክ እና ቴሌኮም ዘርፎች ከፍታለች። ፈረንሣይ ይህንን እንዴት ታየዋለች?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- በጣም አስፈላጊ ነው። ታሪክ እንደሚያሳየው የሞኖፖሊ አሠራር ለኢኮኖሚው ጥሩ አይደለም። ለተጠቃሚውም ጥሩ አይደለም። ስለዚህ የሞኖፖሊ አሠራር ማብቃቱ ለተለያዩ ተዋናዮች ዘመናዊ እንዲሆኑ፣ የአገልግሎታቸውን ጥራት እንዲያሻሽሉ፣ ዋጋ እንዲቀንስ የተወሰነ ማበረታቻ ይሰጣል።
ስለዚህ በጣም አስፈላጊ እና ጤናማ ሂደት መሆኑን በሁሉም ዘርፎች ውስጥ ማለትም በቴሌኮም፣ በባንክ ጉዳይም ቢሆን በተግባር ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። አዳዲስ ተዋናዮች እንዲመጡ መፍቀድ ሁሉም ኢኮኖሚስቶች የሚስማሙበት ነገር ነው። በእርግጥም የዚህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም አካል በመሆኑም እናበረታታለን።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁ የበረራ አገልግሎት አቅራቢ ነው፣ እና የኤርባስ ደንበኛ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ብዙ የኤርባስ አውሮፕላኖችን እየገዛ ነው። ይህስ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚያደርጉት ትብብር ምን አስተዋፅዖ አለው ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- በነገራችን ላይ ኤርባስ የፈረንሳይ ብቻ የሆነ ኩባንያ አይደለም፤ ባለቤትነቱ የአራት የአውሮፓ አገሮች ነው፡ እዚህም ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ስፔን ናቸው። ዋና መሥሪያ ቤቱ ፈረንሳይ ውስጥ በቱሉዝ ይገኛል። በአውሮፓ ውስጥ በጣም አስደናቂ ከሆኑት የኢንዱስትሪ ስኬቶች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለኤርባስ እና ለፈረንሳይ በጣም ጠቃሚ አጋር ነው። በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ፤ በጣም ስኬታማ፣ ለተጠቃሚዎች ከፍተኛ ርካታ ያስገኘ እና እጅግ በጣም ጥሩ አፈጻጸም ያለው አየር መንገድ ነው።
እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረዥም ታሪኩ ውስጥ በአብዛኛው ከቦይንግ ጋር ይሠራ ስለነበር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ገበያውን ለኤርባስ አውሮፕላኖች ለመክፈት በመወሰኑ በጣም ደስ ብሎናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከማገኛቸው ሰዎች ጋር ስንነጋገር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤርባስ ጋር በተደረገው ትብብር በጣም ደስተኛ ናቸው። በዚህ ዓመት ኤርባስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የተላከውን ኤርባስ A350-1000 ለኢትዮጵያ አበርክቷል። በእውነቱ በመክፈቻ በረራ ላይም ተሳፋሪ የመሆን ክብርም አግኝቼ ነበር፣ ስለዚህ በጣም የሚገርም ተሞክሮ ነበር። አየር መንገዱ አሁን ሦስቱን ኤርባስ A350-1000 ባለቤቶች ነው። ሌላው እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ።
እስከዚያው ድረስ፣ እንዲሁም ጥቂት ተጨማሪ ግዢዎች ለተጨማሪ A350-900 ታዘዋል። ስለዚህ እኔ እንደማስበው በዚህ ረገድ በጣም ታማኝ እና ተስፋ ሰጪ ግንኙነት ነው ያለው፣ እናም የእዚህ አስደናቂ ፍጻሜ አካል በመሆናችን በጣም ኩራት ይሰማናል።
አዲስ ዘመን፡- ለአንድ ዓመት ያህል ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስታደርግ ቆይታለች። ማሻሻያው ቀደም ሲል በጣም የተፈራ ነበር። ነገር ግን መንግሥት ይህንን ሪፎርም ተግባራዊ ለማድረግ ቆራጥ ርምጃ ወስዷል። እስካሁን ያለውን አተገባበር እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- እነዚህ ተሐድሶዎች በጣም ትልቅ እና አስደናቂ ናቸው። በዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አይኤምኤፍ፣ የዓለም ባንክ ርዳታ ያገኛሉ። እናም እነዚህ ተቋማት እያደረጉት ያለው ግምገማ በጣም አስደንቆኛል። ኢትዮጵያ እነዚህን ማሻሻያዎች ወደ ትግበራ ስታስገባ ያሳየችውን ፖለቲካዊ ፍላጎት በተመለከተ በጣም ተደንቄያሁ። ለዚህም ነው ተግባራዊነታቸውን ለመደገፍ የወሰነው።
ከዚህ ቀድሞ (ከስድስት ዓመት በፊት) መንግሥት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚተገበርበት ወቅትም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ድጋፍ ነበር፣ እኛም በዚህ ድጋፍ እየተሳተፍን ነበር። እንደ ብቸኛ የሁለትዮሽ ለጋሽ ወደ 100 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ብድር ለኢትዮጵያ አበርክተናል። በሁለተኛው የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነን።
ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር (እ.አ.አ) ለበጀት ድጋፍ 25 ሚሊዮን ዩሮ ርዳታ ሰጥተናል፣ እናም በዚህ መሠረት ለመቀጠል አስበናል። እስካሁን ድረስ በዚህ ረገድ ብቸኛው የሁለትዮሽ ለጋሽ ነን። ግን በዚህ ብቻ አያቆምም።
በቡድን 20 የጋራ ማሕቀፍ ውስጥ ከቻይና ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ዕዳ መልሶ የማዋቀር ሥራ ላይ በትጋት ተሳትፈናል። ዕዳውን መልሶ በማዋቀር ሂደቱ ገፍተንበት ባለፈው ሳምንት የመግባቢያ ስምምነቱ (MOU) ተቀባይነት ማግኘት ችሏል። ይህ በቀጥታ የኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል አይደለም ግን በጣም አስፈላጊ ማነቃቂያ ነው፣ ምክንያቱም ብዙ ሀገሮች ለኢትዮጵያ እንደገና ብድር መስጠት እንዲጀምሩ ያስችላቸዋል። ይህም ሀገሪቱ አስፈላጊ ከሆነ ከሌሎች አጋሮች እንደገና መበደር እንድትጀምር ያስችላታል፤ እናም በዚህ ረገድ ድጋፍ በማድረጋችን ደስተኞች ነን።
በሌላ በኩል ደግሞ በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ መረቡን በማደስ እና በማስፋፋት ላይ ያለው RISED በተባለው እጅግ ታላቅ ፕሮጀክት ትግበራ ላይ የተወሰነ ድጋፍ እናደርጋለን። ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር የምናደርገው ይህ ድጋፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማርሽ ቀያሪ ሊባል የሚችል የግሎባል ጌትዌይ ፕሮጀክት ነው።
ምኞታችን እንደ እኛ ላለ አጋር ኢኮኖሚው ከሞኖፖሊ ወደ ክፍት ኢኮኖሚ እንዲሸጋገር፣ የግል ኩባንያዎች ወደሚያድጉበት አሠራር እንዲመጣ ይህችን ሀገር መደገፍ ተገቢ ነው። ይህ ደግሞ ልንደግፈው የምንፈልገው አካሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ፈረንሳይ በኪነ ሕንፃ ታዋቂ ነች። የፈረንሳይ አርክቴክቸር በኢትዮጵያም የበለፀገ ዐሻራ አለው። ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ ከተሞችን በማደስ እና ቅርሶችን በመጠበቅ ረገድ እንዴት ይተባበራሉ?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- በሥነ ሕንፃ ጥበብ ረገድ እዚህ ሀገር የረዥም ጊዜ ታሪክ አለን። ባለፈው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መሪዎች በርካታ ፈረንሳውያን አርቲስቶችን፣ አርክቴክቶችን፣ መሐንዲሶችን፣ አርኪኦሎጂስቶችን ሳይቀር ጠርተው ለዚህ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ አስችለዋል። እዚህ የሠሩ ጥቂት ታዋቂ የፈረንሳይ አርክቴክቶች አሉ።
ከመካከላቸው አንዱ ሄንሪ ሾሜት ይባላል። ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ዘመናዊ ዲዛይን አስተዋፅዖ አበርክቷል። በቸርችል መንገድ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት አርክቴክት ነበሩ። ሾሜት እንደ ብሔራዊ ቴአትር፣ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት የሚገኘውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት እና ሊሴ ገብረ ማርያምን የመሳሰሉ ሌሎች ጠቃሚ ሕንጻዎችን የነደፈ ሰው ነበር። በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉት የሥነ-ሕንፃ ምልክቶች ጥቂቶቹ ናቸው። በዚህ የኢትዮ-ፈረንሳይ ጉዞ በጣም እንኮራለን።
በዚህ ውብ ከተማ ውስጥ እንደ ጳውሎስ ባርያስ ያሉ ሌሎች አርክቴክቶችም ነበሩ። እዛው አካባቢ የሚገኘውን ላ ጋርን የነደፈው አርክቴክት እሱ ነው፣ ያ በ1920ዎቹ ነበር። እና በ1955 የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ስለሠራው ፈረንሳዊው የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ሞሪስ ካልካ ሰምተህ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።
ወደ አርክቴክቸር እና ሥነ ጥበባት ስንመጣ በሁለቱ ሀገሮቻችን መካከል የረጅም ጊዜ ታሪክ አለ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርስ ዘርፍ፣ ብሔራዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ረገድ በጋራ ለመሥራት ያቀረቡትን ጥያቄ የተቀበሉት። የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳትን የመሳሰሉ በጣም ጠቃሚ እና ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶች አሁን ተጠናቋል። ሰዎች ሊጎበኙት ይችላሉ፣ እና አስደናቂ ስኬት ነው። ስለዚህ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት የነበረው ቤተ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ታድሷል። እናም ጎብኚዎች በዚህ በጣም ታሪካዊ ሕንፃ ሊደሰቱ እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ።
ከዚህ ባለፈም እንደ ላሊበላ ባሉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ስንሠራ ቆይተናል። እድሳት ለማድረግ፣ በተደራሽነት እና በሕንፃው ዘላቂነት ላይ ለመሥራት ከካህናቱ፣ ከቤተክርስቲያን፣ ከአጥቢያው ማኅበረሰብ ጋር በጋራ ለመሥራት ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጀመሩ ጥቂት ፕሮግራሞች አሉ። ይህም በጣም የተሳካ እንደነበር ተረድቻለሁ። አሁን ከላሊበላ አልፈን ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅርሶች በተጨማሪ ወደ ኢንዱስትሪያዊ ቅርሶች፣ የእስልምና እምነት ቅርሶችን ለማካተት እና እስከ ትግራይ ድረስ በመሄድ ለመሥራት ሰፊ ፕሮግራም አለን።
በዚህ አዲስ አበባ የሚገኘው የፈረንሣይ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከልም ተግባራዊ በሆነው ይህ ትብብር በጣም ረክተናል፤ በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብረን ለመሥራት በጣም ጓጉተናል።
በአጠቃላይ ያለፈውን ክፍለ ዘመን ታሪክ ስንመለከት በጣም የሚያስደንቅ መሆኑ እውነት ነው፣ የቦታዎች ብዛት ምን ያህል መቀራረባችንን በትክክል አሳይቷል።
አዲስ ዘመን፡- አፍሪካ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራች ነው። ስለዚህ ይህን የነፃ ንግድ አካባቢን ለመፍጠር በምን መልኩ ትደግፋላችሁ?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- ይህ ለአፍሪካ አንድነት ግንባታ በጣም አስፈላጊ ርምጃ ነው። እንደ አውሮፓውያን ያለንን ልምድ ልናገር። ፈረንሳይ የአውሮፓ ኅብረትን ከመሠረቱት ሀገራት አንዷ ነች። በመሠረቱ አንድነታችንን የገነባነው በኢኮኖሚና በነፃ ንግድ ነው። ብዙ ጊዜ ወስዷል። በብረት እና በከሰል ድንጋይ ጀምረን እና በትንሽ በትንሹ እያልን ተጉዘን ይህንን ልዩ አካል ማለትም የአውሮፓ ኅብረት መፍጠር ችለናል።
ከአፍሪካ ኅብረት ጎን በነዚህ መስመሮች ላይ ለመሥራት የሚያስችል ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳለ ስናይ የወሰነው ውሳኔ ይህንን መደገፍ ነበር። በአውሮፓ ኅብረት ደረጃም ሆነ በፈረንሳይ ደረጃ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የምናደርገው ውይይት አካል ነው። እና በቴክኒካል ድጋፍ፣ ልምዳችንን ለማካፈል አንዳንድ ድጋፎችን ለመስጠት እንሞክራለን። የአፍሪካ ኅብረት አጋሮቻችን ከልምዳችን ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለጉ፣ ለማካፈል በጣም ደስተኞች ነን። ልምድ ማካፈል በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ምን አይነት ሂደት እንዳለፍን ማካፈል እንችላለን፤ ያጋጠሙንንን ችግሮች ያለፍንባቸውን ዘዴዎች ልምድ ማካፈል እንችላለን። አንዳንድ ስኬቶች ካሉ ያንን ማጋራት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ፈረንሳይ ከአፍሪካ ጋር የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖ ለማሸነፍ እየሠራች ያለችው እንዴት ነው?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- የአየር ንብረት ለውጥ ሁላችንንም እየጎዳ ነው። ባለፈው ሰኔ ወር በአውሮፓ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሞቃታማ ወር አሳልፈናል። በሁላችንም ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ሁላችንም እናውቃለን። በአፍሪካ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፣ ኢትዮጵያም ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ግልጽ የሆነ አሳሳቢ ሁኔታ አለ፣ እና ሁላችንም ይህን የአሳሳቢነት ስሜት መጋራታችን አስፈላጊ ነው። ከአሥር ዓመት በፊት፣ በፓሪስ የ COP21 ስምምነት ፀድቋል።
ስለዚህ እኛ የምንሠራው የመጀመሪያው ነገር፣ እንደ አየር ንብረት ጉዳይ በጣም ቁርጠኛ መንግሥት፣ ሁለቱም ሀገሮች ተመሳሳይ የፍላጎት ደረጃ እንዲኖራቸው ማበረታታት፣ ሁለተኛ፣ ተግዳሮት ያለባቸው ሀገሮች ችግራቸውን እንዲፈቱና ወደፊት እንዲሄዱ መርዳት ነው። ለዚህም ነው ፈረንሣይ በ2009 በኮፐንሃገን ታዳጊ ሀገሮች የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲጋፈጡ ለመደገፍ ቃል የገባነውን 100 ቢሊዮን ዶላር እያዋጣን ያለነው።
በአሁኑ ወቅት ፈረንሣይ ችግሩን ለመከላከል በሚል በዓመት 7 ቢሊዮን ዶላር ትሰጣለች። በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ ሀገሮች እነዚያን አደጋዎች እንደ ክትር ግንባታ፣ የውኃ መሸርሸርን መከላከል፤ መገደብና የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖ ለመከላከል ሊደረጉ የሚገባቸው ልዩ ልዩ ሥራዎችን ማላመድ ያስፈልጋል። ስለዚህ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምንሠራው አንዱ አስፈላጊ አካል ነው።
ድጋፋችን የታላቁ አረንጓዴ ግንብ አፋጣኝ የምንለውን ያጠቃልላል። ከአራት ዓመት በፊት በፕሬዚዳንት ማክሮን የተጀመረው የአፍሪካ ኅብረትን ታላቁን አረንጓዴ ግንብ የመደገፍ ነው። ዓላማውም አፍሪካ ለታላቁ አረንጓዴ ግንብ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ከተለያዩ ለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝ መፍቀድ ነበር። Just Energy Transition Partnerships፣ JETP ብለን በምንጠራው ነገር ላይም እየሠራን ነበር። ታዳጊ ሀገሮች ከቅሪተ አካል ነዳጆች እንዲያወጡ ለመርዳት ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጀመረ ነው። ይህም በደቡብ አፍሪካ እና በሴኔጋል የተጀመረ ሲሆን ሁለቱም ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።
በተጨማሪም የባሕር ዳርቻን መሸርሸርን ለመዋጋት፣ የውቅያኖስ ጥበቃን፣ ዘላቂ ሰማያዊ ኢኮኖሚን በመደገፍ ላይ ተሰማርተናል። እናም ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውቅያኖስ ኮንፈረንስ በፈረንሳይ በኒስ ከተማ አዘጋጅተን እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ያነሳንበትን እውነታ መጥቀስ እፈልጋለሁ።
በቴክኒካል ድጋፍም ሆነ በዲፕሎማሲው በኩል ይህንን አንገብጋቢ ጉዳይ ለመፍታት ሞክረናል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለወሰደችው ጅማሮ አክብሮቴን እገልጻለሁ። በመስከረም ወር ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ታስተናግዳለች። ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በተለይም የአፍሪካ ሀገራትን ለማሰባሰብ እና በብራዚል የሚካሄደው COP30 ስኬታማ እንዲሆን ዕድሉን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ስለሚፈጥር በጣም ጠቃሚ ወቅት ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አፍሪካ 30 በመቶው የዓለምን የኃይል ሽግግር የሚደግፉ ወሳኝ ማዕድናት እንዳላት ይታመናል። አፍሪካ ከዚህ ሽግግር ምን ትጠቀማለች ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡- የኃይል ሽግግር በተለያዩ ሀገራት መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ ብዙ ነገሮችን ይቀይራል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ ሀገሮች ብርቅዬ መሬቶችን ወይም ወሳኝ ማዕድናት አሏቸው። ታሪክን መሠረት በማድረግም ስናየው ዋናው ቁም ነገር እነዚህ ማዕድናት ሲለሙ በቅድሚያ ጠንካራ አስተዳደር እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። እንደ አልማዝ፣ የነዳጅ ዘይት ጉድጓድ ያሉ ቀደምት ያልተለመዱ ሀብቶች ያሏቸው ሀገሮች በጠንካራ አስተዳደር እጦት ምክንያት ሀብታቸው ርግማን እንደሆነባቸው ከልምድ እናውቃለን።
ይህ ደግሞ ሙስናን እና ግጭትን ያቀጣጥላል። እና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ከሁሉም ልምድ በመነሳት ጠንካራ አስተዳደር፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ጠንካራ ተቋማት መኖር አስፈላጊ ነው። እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ወደ ጥቅም እንዲለወጡ መልካም አስተዳደር፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ጠንካራ ተቋማት መኖር ነው። ሀገሪቱ ከሀብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን እና ማዕድናትም ሀገሪቱን ለማልማት ወሳኝ ግብዓት እንዲሆኑ ከተፈለገ ይህ ወሳኝ ርምጃ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አፍሪካውያን በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ላይ ምንም ውክልና የላቸውም። ፈረንሳይ ደግሞ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን አላት። ታዲያ የአኅጉሪቱን የቋሚ መቀመጫ ጥያቄ እንዴት ይደግፋሉ?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፤– በጣም ጠቃሚ ጥያቄ ነው። በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ሀገሮች ‘የፀጥታው ምክር ቤትን ማሻሻል፣ አዳዲስ አባላት ቋሚ አባል እንዲሆኑ ለማስቻል ማሳደግ አለብን’ ሲሉ ከ30 ዓመታት በላይ ሲወያዩ ቆይተዋል።
ፈረንሳይ ከአምስቱ ቋሚ አባላት አንዷ ቋሚ አባል ነች። ይህንን የተሐድሶ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ከደገፍን የመጀመሪያዎቹ ቋሚ አባላት አንዱ ነበርን። ለዚህ ጉዳይ በጣም ቁርጠኛ ከሆነችው እንግሊዝ ጋር፣ ይህንን የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ በብርቱ እንደግፋለን። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እኛ ከአፍሪካ ኅብረት አቋም ጋር ሙሉ በሙሉ እንስማማለን።
በአሁኑ ወቅት የፀጥታው ምክር ቤት አምስት ቋሚ አባላትን ጨምሮ 15 ተለዋጭ አባላት አሉት። ተጨማሪ ስድስት ቋሚ አባላትን መጨመር አለብን ብለን እናምናለን። እናም በዚህ ረገድ እንደ ብራዚል፣ ጃፓን፣ ጀርመን እና ሕንድ ያሉ ሀገራት ቋሚ አባል እንዲሆኑ እንደግፋለን ነገርግን ሁለት የአፍሪካ ቋሚ አባላትን መጨመር አለብን ብለን እናምናለን። የትኞቹ ሀገሮች ይሁኑ የሚለውን መወሰን የአፍሪካውያን ጉዳይ ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት በቋሚ አባልነት አፍሪካዊ ሀገር ስለሌለች ይህ መታረም አለበት። ስለዚህ ውይይቱ በኒውዮርክ የቀጠለ ሲሆን በዚህ ረገድ ድጋፋችንን ገልጸናል። እናም እንዳልኩት የአፍሪካ ኅብረትን አቋም ሙሉ በሙሉ እየደገፍን ነው።
ድምፅን በድምፅ መሻር (ቬቶን) በተመለከተ፣ በአሁኑ ወቅት፣ እኛ ቋሚ አባል ነን፣ ስለዚህ ቬቶ የመስጠት ዕድል አለን። ግን ያንን አናደርግም። እኛ የፀጥታው ምክር ቤት በበርካታ ሀገራት በድምፅ ቬቶ አጠቃቀም ምክንያት ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር ብለን እናምናለን፤ ይሁን እንጂ አንድ ሀገር ቬቶ የምትጠቀምበትን ዕድል መዝጋት አለብን እያልኩ አይደለም። እኔ እያልኩ ያለሁት የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀል፣ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ወይም የጅምላ ግድያ ወንጀሎች ሲፈጸሙ በአንዳንድ ሁኔታዎች ቬቶ ላለመጠቀም የፖለቲካ ስምምነት ማድረግ አለብን። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ወቅት አገሮች ቬቶአቸውን ላለመጠቀም መወሰን አለባቸው፤ ምክንያቱም ይህ ካልሆነ አጠቃቀሙ ኢ-ፍትሐዊ ይሆናል። ስለዚህ ከሜክሲኮ ጋር አንድ ተነሳሽነት ጀምረናል፤ እናም አሁን ከ 100 በላይ ሀገሮች ይህንን የveto አጠቃቀም የሚወስን ጥሪ ተነሳሽነት ይደግፋሉ። በእኛ በኩል እስካሁን ድረስ ለ40 ዓመታት ያህል የቬቶ መብታችንን አልተጠቀምንበትም።
አዲስ ዘመን፡-ስለዚህ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የማግኘት ዕድሏ የሰፋ ነው ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፡– በእርግጠኝነት። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ 54 አፍሪካውያን አባላት አሉ። ይህ ቁጥር ከሩብ በላይ ነው፣ ማሻሻያ ለማፅደቅ የሚያስፈልገው ደግሞ ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ነው። ስለዚህ የአፍሪካ ሀገሮች ይህንን የፀጥታ ማሻሻያ በመደገፍ ሙሉ በሙሉ ቢሳተፉ፣ በውይይት መድረኩ ላይ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ቢያስቀምጡ፣ ሊያልፍ እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ። እኛም በእርግጥ እንደግፋለን።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ጉዳዩ በአፍሪካ ሀገሮች እጅ ነው ማለት ነው….?
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፤-ለአፍሪካ ሀገራት ብቻ ሳይሆን የሁላችን ጉዳይ ነው፡ አፍሪካ ግን ቀዳሚ ልትሆን ትችላለች እናም ድምፅ እንደሚኖራቸው እርግጠኛ ነኝ። ይህንን ተነሳሽነት እንደግፋለን።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ጊዜ እና ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን!
አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ፤-አመሰግናለሁ!
ዘካርያስ ወልደማርያም
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም