
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከትግራይ የተውጣጡ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል። ንግግሩን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገራችን የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ታሪክ እና የአስተዳደር ሥርዓት ብሄራዊ እርቅ፣ ብሄራዊ ምክክርና የፖለቲካ ውይይት የሚባሉትን ማኅበራዊ ጽንሰ ሃሳቦች በይፋ ያስተዋወቀው አሁን ያለው መንግሥት መሆኑ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥት ችግሮችን በማጣራት በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ እንደሚሰጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተግባር ማሳየቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትርምስ ትርምስ ይፈጥራል፣ ግጭት ግጭትን ይፈጥራል እናም በችግር ከበባ ውስጥ እንድንኖር ያደርገናል፤ በረከት ሰላምም ሊያመጣ አይችልም። በታሪካችን ዘላቂ ሰላም በግጭት እና በጦርነት አልመጣም፤ ሊመጣ አይችልም። በአንፃሩ በድርድር፣ በመግባባት እና በሀሳብ ልውውጥ የሚመጣው ሰላም መሰረቱ ጠንካራ ነው ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት መንግሥታቸው ኢትዮጵያ እያካሄደች ለምትገኘው ሀገራዊ ምክክር ሁሉንተናዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ከየትኞቹም ኃይሎች ጋር ለመወያየትና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው።
ለመሆኑ በሀገራችን የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ታሪክ እና የአስተዳደር ሥርዓት አልነበሩም የተባሉትን ብሄራዊ እርቅ፣ ብሄራዊ ምክክርና የፖለቲካ ውይይት አቅፎ የያዘውና በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሀገራዊ ምክክር ፍሬው ጣፋጭ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት ?
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም ከኋላ የመጣንባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት ሁለት መሰረታዊ መፍትሔዎች አሉ ብዬ አምናለሁ ሲሉ ይጀምራሉ። አንደኛው እስከዛሬ ድረስ ከሀገረ መንግሥት ምስረታ ጀምሮ ሳያግባቡን እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቆም ብለን ተነጋግረን በጋራ መንገዳችንን እንድንተልም የሚያደርገን ሀገራዊ ምክክር ነው። ሁለተኛው ከኋላ የመጡ የፍትህ መጓደሎችን መፍታት የምንችልበት የሽግግር ፍትህ እንደመሳሪያ መቀመጡ ነው ይላሉ።
በጦርነት ውስጥ አልፈናል ከውድመት በቀር የፈየደልን ነገር የለም የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ እስካሁን ባልሞከርነው መንገድ መሄድ አለብን። በሀገራዊ ምክክሩ ተስፋ ሰንቀን በንቃት እና በነጻነት መሳተፍ አለብን። ያን ማድረጋችን ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንድንችል ያደርገናል። እየተካሄደ በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ የተነሱት ሀሳቦች ብንነጋር ለመግባባት እንደማንቸገር የሚሳዩ ናቸው ነው የሚሉት።
በመነጋገር ለማንኛውም ጉዳይ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመው፣ ልዩነቶችን ቁጭ ብሎ በንግግር የመፍታት ባሕል ብናዳብር ኖሮ ሀገራችን በብዙ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ውስጥ አታልፍም ነበር። አሁንም ቢሆን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በ21ኛው ክፍለ ዘመን እዲህ ያለው አካሄድ እንዳበቃለት በመረዳት አሉ የሚባሉ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ጠረጴዛ ላይ ማቅረብ መቻል ይገባል ሲሉ መክረዋል።
አክለውም ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራችን ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባሕል እንዲገነባ በር የሚከፍት ነው። ኮሚሽኑ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ እያስተላለፈ የሚገኘው ትልቁ መልዕክት ይህ ነው። ኢትዮጵያውያን ተነጋግረው የራሳቸውን ችግሮች ራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ነው ባይ ናቸው።
በሀገራዊ ምክክሩ ገና ከጅምሩ ብዙ ስጋቶች ያደሩባቸው ወገኖች እደነበሩ ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፣ የምክክር ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት ነጻና ገለልተኛ መሆኑን አስመስክሯል። በርካቶችም ሂደቱን በመመርመር ወደተሳትፎ መጥተዋል። እኔም እንደ አንድ ዜጋ በነበረኝ ተሳትፎ ያረጋገጥኩት ይሄንኑ ነው። ኮሚሽኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጽ በነጻነት እንዲሰማ እያደረገ መሆኑን ተረድቻለሁ በማለት የሀገራዊ ምክከሩን ስም ለማጠልሸት የሚራገበው አሉባልታ መሰረት የሌለውና ሀገር እንድትገነባ የማይፈልጉ የአፍራሾች የፈጠራ ወሬ መሆንን ይናገራሉ።
በምክክሩ አብዛኞቹን ችግሮቻችንን እንፈታለን፤ ልዩነቶቻችንን እናጠባለን ብዬ ጠብቃለሁ። ስምምነት ላይ ያልደረስንባቸው ጉዳዮች ካሉም በቀጣይ እያየናቸው እንሄዳለን። በሀገራዊ ምክክር ውጤት ዙሪያ የሚታየን ብሩህ ተስፋ ነው። ስኬታማ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ከማንም በላይ ከዚህ ምክክር ተጠቃሚ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው። ይህች ሀገር የወጣቶች ናት። ነገ የሚረከቡን እነሱ ናቸው። ለልጆቻችን የምናስረክባት ሀገር ምን አይነት መሆን አለባት የሚለው ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ይቋጫሉ።
ፕሮፌሰር አለማየሁ ካነሷቸው ሀሳቦች አንዱ ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለችው ሀገራዊ ምክክር ከማንም በላይ ተጠቃሚ ወጣቶች ናቸው የሚለው ነው። ወጣቶች ስለሀገራዊ ምክክሩ ምን ያስባሉ እንዴት ባለ መንገድስ እየተሳተፉ ይገኛሉ ስንል የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወጣት ዮሴፍ አበራን ጠይቀነዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚው ከሀገራችን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 70 ሚሊየን ያህሉ ወጣቶች መሆናቸውን ጠቁሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ከ10 ሚሊየን በላይ አባላት እንዳሉትና 79 ተቋማት በስሩ እንደሚኙ ይናገራል።
ፌዴሬሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ ከመነሻው ጀምሮ ትልቅ አሻራ እያኖረ መምጣቱን አመላክቶ፣ ምክክሩ ሲጀመር የነበረው ሁኔታ እና አሁን የደረሰበት ደረጃ ትልቅ ለውጥ ታይቶበታል። በእኛ በኩል ከወጣቶች የሰበሰብናቸውን አጀንዳዎች በአዲስ አበባ በተካሄደው የፌዴራል የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ ማስረከብ ችለናል። ወጣቶች ያነሷቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ አድርሰናል ይላል።
የምክከሩ ሂደቱን “ሀገሬ ነገ የምትደርስበትን ደረጃ የሚያንጸበርቅ የተስፋ ጉዞ ነው” ሲል የገለጸው ወጣት ዮሴፍ፤ 130 ሚሊየን ከሚጠጋው ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ወጣት ነው። ዛሬ ያለችውን ኢትዮጵያ ነገ የሚረከበውና ለቀጣዩ ትውልድ የሚያቀብለው የዛሬው ወጣት ነው። በምክክር ሂደቱ የብዙኃኑ ወጣት ሀሳብ መካተቱና የነቃ ተሳትፎ ማድረግ መቻላችን ትልቅ ትርጉም አለው። የወጣቶች ድምጽ ካልተደመጠ ሀገር ወደ ነገ መሻገር አትችልም። ስለዚህ ሀገራዊ ምክክሩ ከየትኛውም የሕብረተሰብ ክፍል በላይ ለነገው ወጣት ልዩ ትርጉም አለው ነው የሚለው።
በአዋጅ የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር በየደረጃው ያሉ የወጣቶችን ድምጾች ሰምቷል የሚለው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚው፣ ሀሳባቸውን ተቀብሏል። ኢትዮጵያ ወጣቶቿን ካዳመጥች፤ ወጣቶቿም በሀገራቸው ጉዳይ ያገባኛል ብለው ከተሳተፉ የማይፈታ ችግር አይኖርም። ሀገሬ እየመከረች ተስፋዋን እየገለጠች ነው። ሀገራዊ ምክክሩ እንደሚሳካ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ። የጨለመው ጭጋግ ነገ የማይፈካበት ምንም አይነት ምክንያት የለም በማለት ሀሳቡን ያጠቃልላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከትግራይ የተወጣጡ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጋር ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እርቅ በሀገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖት አባቶች መካከል የሚደረግ ምክክር ሲሆን ፍሬው ጣፋጭ ነው ብለዋል። የሀገራዊ ምክክሩ ውጤትም ፍሬው ጣፋጭ እንዲሆን ዛሬም ድረስ ተቀራርበን እንነጋገር፤ በሰለጠነ መንገድ እንመካከር የሚል ጥሪ እያቀረበ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀና ምላሽ መስጠት ከሁሉም አካል የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ነው።
ከሰሞኑ በይፋ በተደረገ ሌላ መረጃ ሀገራዊ ምክከሩ ለኢትዮጵያ ይዞ የመጣውን ተስፋ የሚያሰፋ ዜና ተሰምቷል። ከምክክር ኮሚሽኑ ራሳቸውን አግልለው የነበሩ ሦስት ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር በተናጠል ባደረጉት ውይይት ወደ ውይይት መምጣታቸውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በምክክር ሂደቱ ለመቀጠል ወደ ውይይት የመጡ ፓርቲዎች መኖሯቸውን ጠቅሰው፣ ሆኖም ግን አንዳንድ ጉዳዮቻቸው ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነት ውጭ ስለሆኑ ውጤት ለማምጣት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ጥረት የሚጠይቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከፓርቲዎቹ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ወደ ምክክር ለመሄድ የሚያስችል ተግባቦት ላይ ለመድረስ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
በቅርቡ ወደ ውይይት የመጡት ፓርቲዎች እናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ ናቸው። ኮሚሽኑ በምክክሩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሌሎች ፓርቲዎችን ወደ ውይይት ለማምጣት በቀጣይም በትኩረት እየሠራ ነው። የምክክር ኮሚሽኑ እምነት አንድም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሳተፍ እንዳይቀር መሥራት እንደሆነ አንስተው፣ ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎችም የራሳቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ከሰሞኑ ወደ ውይይት ለመምጣት ፈቃደኛ የሆኑ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት በኮሚሽኑ ሂደት ላይ ቅሬታ የነበራቸው ናቸው። ሦስተኛ ዓመቱን አገባድዶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕድሜው የተራዘመለት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በእስካሁን ቆይታው ከ63 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሆኑት በምክክር ኮሚሽኑ ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸው ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
የሀገራዊ ምክክሩ ኮሚሽኑ በሂደቱ ላይ ቅሬታ ከነበራቸው ፓርቲዎች ጋር ደብዳቤ በመጻጻፍ እና የተለያዩ ተግባቦቶችን በማድረግ ከምክክሩ በፊት መጀመሪያ አንስቶ ወደ ውይይት እንዲመጡ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ ቢሆንም ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ ሕብር እና መድረክ የሚባሉት ፓርቲዎች አሁንም ድረስ ወደ ውይይት ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም። እነዚህንም ፓርቲዎች ወደ ምክክሩ መድረክ ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ኮሚሽኑ ተናግሯል።
ራሳቸውን ከምክክሩ ያገለሉ ኃይሎች ሁሉ በቀሪው ጊዜ በጠረጴዛው ዙሪያ ሲሰበሰቡ እና ከጠመንጃ ይልቅ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ባሕል ሲሆን የሀገራዊ ምክክሩ ፍሬ ጣፋጭ ይሆነዋል። አሰባሳቢ የጋራ ትርክት ለመቅረጽ እየተደረገ ያለው ፈታኝ ጉዞ በድል ይደመደማል። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ክብሯና ኃያልነቷ ትመለሳለች። ይህ ትውልድም በትውልዶች ቅብብሎሽ የተሻገረ የዘመናት የቤት ሥራን በሚገባ የተወጣ ገናና ባለታሪክ ሆኖ አኩሪ ገድሉ በትውልዶች ሲተረክለ ይኖራል። ፍሬው ጣፋጭ እንዲሆን እንትጋ!
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም