በአገሪቱ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በስኬታቸው ከሚጠቀሱ ዘርፎች መካከል የግብርናው ዘርፍ አንዱ ነው:: ግብርናው የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ ብቻ አይደለም፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ተኪ ምርት በማምረት በኩልም ተጠቃሽ ሆኗል:: ለእዚህም ቡና እያስገኘ ያለውን የውጭ ምንዛሬ በአብነት መጥቀስ ይቻላል:: ባለፈው በጀት ዓመት ከቡና አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር መገኘቱ ይታወቃል፤ ይህም በአገሪቱ የቡና የወጪ ንግድ ታሪክ የመጀመሪያ የተባለ ግኝት ተብሏል:: በ2015 በጀት ዓመት አስር ወራትም ወደ ውጪ ከተላከ ቡና ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል::
በስንዴ ልማቱም ተመሳሳይ ስኬት እየተመዘገበ ነው:: በአገሪቱ ታሪክ በቅርቡ በተጀመረው በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስኬታማ መሆን ተችሏል:: የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የዛሬ ሶስት ዓመት በቆላማው የአገሪቱ ከፍል ሲጀመር ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት ተችሏል:: በቀጣዩ ዓመት ይህን አሃዝ 24 ነጥብ አምስት ሚሊየን ከንታል ማድረስ ተችሏል:: ዘንድሮ ደግሞ 53 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል:: የስንዴው አዝመራም እየተሰበሰበ ይገኛል::
በመኸር፣ በመስኖና በበልግ በስንዴ ልማት ላይ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው:: በዚህም ዓመታዊ የስንዴ ማምረት አቅም ጨምሯል:: ይህን ተከትሎም አገሪቱ ዘንድሮ ስንዴ ከውጭ ማስገባት አቁማለች፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ስንዴ ለጎረቤት አገሮች ወደ መላክ ውስጥ ተሸጋግራለች::
በየግብርና ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ላይ የተመለከተው መረጃም ይህንኑ የግብርናውን ስኬት ያጠናክራል:: በሰብል ልማት በ2014/2015 የምርት ዘመን በአነስተኛ አርሶ አደሮች በመኸር 472 ሚሊየን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 480 ሚ ሊዮን ኩንታል ም ርት ተገኝቷል::
በአገሪቱ ሰብል በዓመት አንዴ ብቻ ይመረት የነበረበትን ሁኔታ ዓመቱን ሙሉ የሚመረትበት ወደ ማድረግ ተገብቷል:: በመኸርና በበልግ ከማምረት በተጨማሪ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስጀመር በዓመት ሶስቴ የሚመረትበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: በአንድ ማሳ ከሁለ ት እስከ ሶስ ቴ ማምረት ውስጥ እየተገባ ነው::
ይህ ሁሉ ስኬት የተመዘገበው በግብርናው ዘርፍ ላይ በትኩረት መሰራቱን ተከትሎ ነው:: መንግስት ከእጅ ወደ አፍ ግብርና ወደ ኮሜርሻል ግብርና ለማሻገር እየሰራ ነው:: ለዚህም በቅድሚያ በኮሜርሻል ክላስተር/ኩታ ገጠም እርሻ/ላይ በትኩረት ተሰርቷል:: ይህ ሁኔታም ግብርናውን በቴክኖሎጂ ወይም በሜካናይዜሽን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል::
የግብርናው ምርትና ምርታማነት እያደገ ለመምጣቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም ቴክኖሎጂ መጠቀም መጀመሩን እንደ ዋና ምክንያት መውሰድ ይቻላል:: የዘርፉ ምርትና ምርታማነት የበለጠ እያደገ የመጣው ቴክኖሎጂ እየጨመረ መምጣትን ተከትሎ ነው::
ቴክኖሎጂ ብዙ ነገር ነው፤ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች ናቸው:: አርሶ አደሮች አስቀድሞም ከምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ጋር ይተዋወቃሉ፣ በእነዚህም በምርታማነት ላይ ለውጦች ሲመዘገቡ ቆይተዋል:: ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ ከዚህም በላይ መሄድን የሚጠይቅ ስለመሆኑ ያለፉት ጥቂት ዓመታት የአገሪቱ ግብርና ስራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው::
አርሶ አደሩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከትራክተር፣ ኮምባይነር፣ ለመስኖ አገልግሎት ከሚውሉ ሌሎች አንደ የውሃ መሳቢያ ፕምፓች፣ አነስተኛ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ጋር እየተዋወቀ ይገኛል:: መንግስት እነዚህን ማሽነሪዎች በተለያየ መልኩ እያቀረበ ነው፤ አርሶ አደሮችም የመግዛት ፍላጎታቸው ጨምሯል:: የማሸነሪ አከራዮችም ተፈጥረዋል:: የአርሶ አደሮች ተከራይቶ መገልገል ፍላጎትም አንዲሁ ጨምሯል::
በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ላይ ቴክኖሎጂ ያመጣው ለውጥ ቴክኖሎጂዎቹን በስፋት በመጠቀም የበለጠ ምርታማ መሆን እንደሚቻል ሁሉንም ወገን አመላክቷል:: ከቤተ ሙከራ ወደ አዝመራ በሚል እየተካሄደ ያለው የግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ኢግዚቢሽንም ይህንኑ ይጠቁማል:: ግብርናውን ቴክኖሎጂ በማቅመስ ይህን ያህል ርቀት መሄድ ተችሏል:: ቴክኖሎጂ በመመገብ ደግሞ የምርታማነት እመርታን ማስመዝገብ ይቻላል::
አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂው የሚያመጣውን ለውጥ በሚገባ በመረዳቱ የቴክኖሎጂው ባለቤት የመሆን ፍላጎቱም ጨምሯል:: መንግስትም ቴክኖሎጂው እንዲስፋፋና የሚፈለገው የግብርና ለውጥ እውን እንዲሆን ጽኑ ፍላጎት አለው:: እነዚህን ፍላጎቶች አስተሳስሮ በመጓዝ በቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይ መስራት ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀው ትልቅ ተግባር ይሆናል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2015