ባልና ሚስቱ ለአዲሱ ጎጇቸው ሌት ተቀን ይለፋሉ:: ትዳራቸው በአብሮነት ከቀጠለ ጊዚያት ተቆጥረዋል:: ወዳጅ ዘመድ የሁለቱ ጎጆ በልጅ ፍሬ እንዲባረክ እየተመኘ ነው:: እነሱም ይህን እውነት አጥብቀው ይሹታል:: ልጅ ወልደው፣ ዓይናቸውን በዓይናቸው ለማየት ጓጉተዋል::
የገጠር ህይወት እንደከተማ አይደለም:: የማጀቱ፣ ጎዶሎ የቤተሰቡ ሆድ በጉልበት ዋጋ ይለካል:: የገጠር ሰው ወግ ባህል አክባሪ ነው:: የጥንት አሻራው ዘንድሮም አይጠፋም:: ዘመናዊነት ይሉት ከቶ አያሞኘውም:: ነውርነትን ይሸሻል:: በበጎነቱ ያድራል:: ይህ ማንነት የአብሮነቱ መመሪያ ነው:: ሁሌም በያዘው ጥብቅ ዕምነት ትውልድን ይሻገራል፣ ልምዱን ወጉን ያቆያል::
ባልና ሚስቱ የገጠር ልጆች ናቸው:: የአገሬውን ወግ ባህል፣ የኖሩበትን ዕምነት ያውቁታል:: ነውርና በጎውን በእኩል ሲጋሩት ኖረዋል:: የእናት አባታቸው የአካባቢው ባህል የእነሱ ጭምር ነው:: እስከዛሬ መልካሙን ተዋርሰው፣ ነውር ያሉትን ሲያርቁ ነበር:: አሁንም ከማንነታቸው ዝቅ አይሉም:: ከባህላቸው አይወጡም::
የታሰበው እንደታሰበ …
አሁን የወይዘሮዋ አካላዊ ለውጥ ሚስጥሩ ታውቋል:: ነፍሰጡር ሆናለች:: ከወራት በኋላ ለእሷና ለባሏ ስጦታ፣ ለወዳጅ ዘመድ ጥያቄ መልስ ታገኛለች:: ይህን ስታስብ ፊቷ በደስታ ይፈካል:: ዛሬ ላይ ቆማ ነገን ታያለች:: እናት ስትሆን ለልጇ፣ የሚያሻትን አታጣውም:: ኃላፊነቷ ይበዛል:: ድርሻዋ ይሰፋል:: ወይዘሮዋ ይህ እውነት ቀን ቆጥሮ እንደሚሆን ይታያታል:: ይህ ሲገባት ፊቷ በፈገግታ ይፈካል::
ወይዘሮዋ የመውለጃ ወሯ ገብቷል:: የዘጠኝ ወራት እርግዝና፣ የውጣውረዱ ድካም ከፍጻሜው ቀርቧል:: አንድ ቀን ድንገቴ ህመም ተሰማት:: ውስጧን አስጨንቆ ወገቧን ያሰራት ምጥ መሆኑ ታውቋል:: ዘመድ ጎረቤቱ ከጎኗ ነው:: እናቶች አብረው ያምጣሉ:: ወንዶቹ ከደጅ ሆነው ያደምጣሉ::
የወይዘሮዋ ምጥ በርትቷል:: አሁንም ጥርሷን ነክሳ ትጮሀለች:: ሴቶቹ፣ እናቶቹ ከመንደሯ አዋላጅ አልራቁም:: በካሯን ሴት እያገዙ፣ ከጭንቀቷ ይጋራሉ:: እንደዋዛ ጊዜው ነጉዷል:: የጭንቅ ሰዓታት ተቆጥረዋል:: እስካሁን ወላዷን ‹‹ከሀኪም እንውሰድ፣ እናድርስ ›› ያለ የለም:: ሁሉም ጭንቀቱን ተቀባብሎ በዝምታ ተውጧል:: ህክምናው ከአካባቢው የራቀ ነው:: ከገጠሩ ወጥቶ ከሀኪም ለመድረሰ ሰዓታትን ይጠይቃል::
ምጡ ገፍቶ ህመሙ ሲበረታ ብዘዎቹ ደነገጡ:: በዚህ ከቀጠለ እናቲቱ ትደክማለች፣ ህጻኑም ይታፈናል:: ጥቂት ቆይቶ ድንገቴ የምስራች ሆነ:: በጭንቅ የቆየችው ወይዘሮ በሰላም ሴት ልጅ ተገላገለች:: ዕልልታው ቀለጠ:: እፎይታው፣ ምስጋናው ቀጠለ::
ባልና ሚስቱ የመጀመሪያ ልጃቸውን በስጦታ ተቀብለዋል:: እርጉዝ ሳለች ‹‹የሆድሽ በጀርባሽ ይሁን›› ያሏት ምኞታቸው ሰምሯል:: አሁን እራሷ ልጇን በክንዷ ታቅፋለች:: ነገ ደግሞ በጀርባዋ አዝላት ትሄዳለች:: አንዳንዶች የልጅቱን ሴት መሆን በበጎ መንዝረው ዕድለኝነቷን አውጀዋል:: ሌሎች ደግሞ ልጁ ወንድ ቢሆን ሲሉ ተመኝተዋል::
አሁን ወይዘሮዋ ጠንክራለች:: እንደባህል ወጉ፣ እንደቤቷ አቅም አራስነቷ አብቅቶ ለስራ ተነስታለች:: እናት ነግቶ በመሸ ቁጥር የሚያሳስባት ጉዳይ ዛሬም ከእሷ ጋር ነው:: ህጻኗ ዕድሜዋ ጨምሯል:: አካሏ ግን እንደጫጫ ነው:: መልኳ ያምራል፣ ሰውነቷ ያሳሳል:: እንደልጅ ግን እያየች አታጫውታትም::
እናት ልጇን አተኩራ እያስተዋለች ሁሌም አንዳች ነገር ታስባለች:: የሆነችው ባይገባትም ሁኔታዋ አስጨንቋታል:: ቆንጅዬዋ፣ ትንሽዬዋ ጨቅላ እንደምታስባት አልሆነችም:: እየዳሰሰች፣ ዓይንዓይኗን ታያታለች:: ቀን በጨመረ ቁጥር ስጋቷ አይሏል:: አገሬው ውሎ አድሮ ስለ ልጇ ጤና የሚላትን ታውቀዋለች::
አባወራው የሚስቱን ጭንቀት ይካፈል ከያዘ ሰንብቷል:: ለቤት ለትዳሩ፣ ትርጉም ሰጥታ በረከት የሆነችው ህጻን የጤናዋ ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል:: አሁንም እንደ እኩዮቿ አትስቅም፣ አትጫወትም:: ይህን ባየ ቁጥር ውስጡ ይጨነቃል:: በአካባቢው እንዲህ አይነት ልጆች እንደ ርግማን ይቆጠራሉ:: በወላጆቻቸው፣ ዘር ማንዘራቸው ሀጢያት ይለካሉ:: ይህን ሲያስብ ከልብ ይበሳጫል፤ ይናደዳል:: አንዳንዴ የውስጡ ስሜት ለሚስቱ ተርፎ ከቅያሜ ያደርሰዋል::
የፈሩት ይደርሳል…
አሁን ትንሽዬዋ ልጅ ሁለት ዓመቷን ደፍናለች:: እናት አባት ‹‹ፋንታነሽ›› ሲሉ የሰየሟት ህጻን ጎረቤት እያያት፣ ወዳጅ ዘመድ እያወቃት ነው:: በዕድገቷ የታየው እንከን ለአገሬው በጎ ትርጉም አልሰጠም:: የልጅቷ መታመምና ጤና ማጣት ከዘር ማንዘር የእርግማን ጥግ አድርሶ እያነጋገረ ነው:: ዛሬ ላይ የእናት አባት ስጋት ዕውን ሆኗል:: ሲፈሩት፣ ሲሸሹት ከቆዩት ሀቅ ተጋፍጠዋል::
እነሆ ! ቀናት እየገፉ፣ ጊዚያት እየነጎዱ ነው:: ጥንዶቹ ከጀርባቸው የሚሰሙት ሹክሹክታ የቤታቸውን ሰላም ማናገት ከያዘ ሰንብቷል:: አባወራው ትዕግስት ይሉት አጥቷል:: በሆነው ሁሉ ባለቤቱን እየወቀሰ፣ እየከሰሰ ነው::
ሁለተኛዋ ልጅ…
በአገሬው ሹክሹክታ፣ በአካባቢው ባህል ልማድ የተሸማቀቁ ነፍሶች ዛሬም በጭንቅ ቀናት እየተራመዱ ነው:: በጥንዶቹ ጎጆ ሰላም ከጠፋ ሰንብቷል:: የመጀመሪያ ልጃቸው ጤና ማጣት ከአካባቢው የእርግማን ስጦታ ተዳምሮ ኑሮ ህይወታቸው ተቃውሷል:: አሁን ደግሞ ወይዘሮዋ ሁለተኛ ልጅ አርግዛለች:: እንዲህ መሆኑ ለጠፋው የቤቱ ሰላም መፍትሄ ነው ያሉ በጎነትን ሰንቀዋል::
ባልና ሚስት የመጀመሪያ ልጃቸውን ታቅፈው ሁለተኛውን መጠበቅ ይዘዋል:: አካባቢው ከከተማ ይርቃል:: በስፍራው ህክምና የለም:: ዛሬም ጥንዶቹ ሀኪም ማየት የፈቀዱ አይመስልም:: እናት ጊዜው ሲደርሰ እንደአገሬው ወግ ልማድ በቤቷ ትወልዳለች:: ይህ እውነት በአካባቢው ብዙዎቹ የሚያደርጉት ልማድ ነው::
ወይዘሮዋ የታሰበው ሆኖ በቤቷ አምጣ፣ ወልዳ ሴትልጅን ታቅፋለች:: ይህ በሆነ ማግስት አባወራው ዓይኑን በልጁ ጥሏል:: በአዲሷ ልጅ መወለድ ተስፋው ለምልሞ ታሪክ እንዲለወጥ ይሻል:: አምና ካቻምና የተሳቀቀበት እውነት ዛሬ እንዲደገም አይፈልግም:: አዲሷ ጨቅላ ጤነኛ ሆና፣ እንድትሮጥ፣ እንድትስቅ፣ እንድትጫወት ይመኛል::
ውሎ አድሮ የቤቱ ሰላም ዳግም ተናጋ:: አባወራው በትንሸዋ ልጁ ያየው ምልክት አስደንግጦ አበሳጭቶታል:: እሷም ከታላቅ እህቷ የተለየች አልሆነችም:: ህጻኗ እያየች፣ እየሰማችው አይደለም:: መላ አካሏ ከእንቅስቃሴ ታቅቧል:: የልጅ ልማድ፣ የህጻን ወግ ከእሷ ጠፍቷል::
አስደንጋጩ ውሳኔ …
ከሁለት ዓመት በኋላ ለቤቱ ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ጨቅላ ለጎጆው ሰላም መደፍረስ ምክንያት ሆና ሰንብታለች:: አራሷ ወይዘሮ ዛሬም በዕንባ ታጥባ በሀዘን እየተከዘች ነው:: ስለሆነው ሁሉ ፈጣሪዋን አብዝታ ታማርራለች::
አሁን የአባወራው ባህርይ ከወትሮው ተለይቷል:: ሁለተኛዋ ልጅ ከመጀመሪያዋ ያለመለየቷ የሚስቱ ችግር መሆኑን አምኗል:: ለልጆቹ ጤና ማጣት፣ ‹‹ምክንያት ነሽ›› የተባለችው እናት አንገቷን ደፍታለች:: እርግማኑ የእሷና የቤተሰቦቿ ብቻ መደረጉ ይበልጥ ሰብሯታል:: አሁንም እያነባች ባሏን ትማጸናለች::
እሱ እየሰማት፣ እየተረዳት አይደለም:: አሁንም ለልጆቹ መታመም መነሻ ምክንያት የእሷና የቤተሰቧ ሀጢያትና እርግማን መሆኑን በእርግጠኝነት እየነገራት ነው:: ወሬው በመንደሩ ሲዛመት ለእርግማንና ሀጢያቱ ይበልጥ ማረጋገጫ ሆኗል::
ባል ከቁርጥ ውሳኔ የደረሰ ይመስላል:: አሁን ትዳር፣ ጎጆና ልጆችን አያስብም:: የሀሳቡ መጨረሻ ቤቱን ጥሎ ከመሄድ አድርሶታል:: አንድ ማለዳ ከቤት የወጣው አባወራ ምሽቱን ሳይመለስ በዛው ቀረ:: ተስፋ ያልቆረጠችው ሚስት በር በሩን እያየች ጠበቀችው:: አልመጣም፣ አልተመለሰም::
በአራስ ጎኗ ሁለት ህመምተኛ ልጆችን ታቅፋ ባዶ ቤት የቀረችው እናት በእጅጉ ከፋት:: አምርራ እያዘነች፣ እያለቀሰች አርቃ አሰበች:: የዛሬው ሀዘኗ ከእስከዛሬው ይለያል:: አሁን ብቸኛ ሆናለች፣ ማንም አይዞሽ፣ አለሁሽ የሚላት የለም:: ባሏ፣ ግማሽ አካሏ ትቷት ሄዷል:: ዓይኖቿ በዕንባ እንደተሸፈኑ መልስ የማይሰጧት፣ የማያጫውቷት ልጆቿን አስተዋለች፤ የቀራት ኢምንት ተስፋ ከዓይምሮዋ ተጠራርጎ ሲወጣ ተሰማት::
አንድ ማለዳ ዝምታ ከዋጠው ጎጆ የደመቀ እሪታና ጩኸት ተሰማ:: ጩኸቱን ሰምተው ስፍራው የደረሱ ምሰኪኗን እናት እንደወደቀች አገኟት:: ቀርበው ትንፋሽዋን ያዳመጡ ለአፍንጫቸው ክፉ ሽታ ደረሰ:: ወይዘሮዋ በእጇ የተባይ ማጥፊያ እንደያዘች ለዘላለም አሸልባለች:: ባይተዋሯ እናት፣ ገለልተኛዋ ወይዘሮ መፍትሄ ባለችው አማራጭ ሞትን ሽታው ዓለምን ተሰናብታለች::
የልጆቹ ዕጣ ፈንታ …
አሁን የወይዘሮዋ እናት የልጅ ልጆች አሳዳጊ ሆነዋል:: የሟች ልጃቸው ልጆቹ እንደ እኩዮቻቸው አይደሉም:: በወጉ የማይሰሙ፣ የማያዩ ህጻናትን ማሳደግ ከብዷቸዋል:: አዛውንቷ በመንደሩ፣ በአካባቢው ወሬ ጆሯቸው እየደማ ነው:: ዛሬም የቤተሰቡ እርግማንና ሀጢያት ደምቆ ይወራል:: ሀዘንተኛዋ ወይዘሮ ኑሮ በእጅጉ ከብዷቸዋል::
ህይወት በተለመደው ሂደት ቀጥሏል:: ትንሽዬዋ ልጅ እንደታላቅ እህቷ ናት:: መልኳ ያምራል፣ ሰውነቷ ያሳሳል:: እሷም እንደልጅ፣ መንፈራገጥ፣ መንቀሳቀስን አትሞክርም:: ሀዘንተኛዋ ወይዘሮ ሸክማቸው ከብዷል:: የሟች ልጃቸው ሞት የእግርእሳት ሆኗቸዋል:: ጥላ የሄደችባቸው ህጻናት ተንከባካቢን ይሻሉ:: ከእሳቸው ሌላ የሚያያቸው ዓይን፣ የሚያነሳቸው እጅ የለም::
የልጆቹ ዕድሜ እየጨመረ ነው:: ትልቋ ፋንታነሽ ስምንት፣ ትንሽዋ ሙሉ ሴት ደግሞ ሰድስት ዓመት ሆኗታል:: በወይዘሮዋ ኑሮ ማህበራዊ ህይወት ይባል የለም:: በእሳቸው ዘንድ ለቅሶ መድረስ፣ ሰርግ መሄድ፣ ጎረቤት ቡና መጠጣት አይታወቅም:: ወጣ ቢሉ የሚተካቸው ‹‹ወድቀሽ ተነሺ ›› የሚላቸው የለም:: ዛሬም የእርግማን ሀጢያቱ ጉዳይ ከሰው አግልሎ ከዕድር ማህበሩ አርቋቸዋል::
ልጆቹ ከፍ ባሉ ቁጥር ጫና የበዛባቸው አያት ህይወት እየከበዳቸው ነው:: እስከዛሬ የሟች ትንሽ ወንድም አርሶ በሚያመጣት ጥቂት አህል አፍ ሲሽሩ ቆይተዋል:: አሁን ግን ዕድሜ ከኑሮ ተጭኗቸው እየተንገዳገዱ ነው:: ወይዘሮዋ አንዷን ሲያቅፉ፣ ሌላዋን ያዝላሉ:: እንዲያም ሆኖ መከራን አላመለጡም:: ልጆቹ ድንገት ከእሳት ወድቀው ክፉኛ ተጎድተዋል::
የጦርነቱ ጉዳይ …
አሁን በአካባቢው የሚሰማው ወሬ በጎ አይደለም:: በሰሜኑ ክፍል ወሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ብዙዎች ከቤት ንብረታቸው ርቀዋል:: ወሎ መካነሰላም ዙሪያ ከዚህ ችግር አልተረፈም:: በየቀኑ ጦርነቱ እየባሰ፣ እየጋመ ነው፤ ይህ እውነት ለአዛውንቷ ወይዘሮ ጭንቅ ሆኗል:: ራሳቸውን የማያውቁ ህፃናትን ይዘው የትም መሸሽ፣ ማምለጥ አይችሉም:: የኑሮ ጫና፣ የህይወት ውጣውረድ፣ የጦርነቱ ጉዳይ ክፉኛ ፈትኗቸዋል::
አንድ ቀን ወደስፍራው የዘለቀ አንድ ወጣት የአዛውንቷንና የልጆቹን አስከፊ ኑሮ በዓይኑ ማየት ቻለ:: ድህነታቸው፣ ገልተኝነታቸው ክፉኛ ልቡን ነካው:: የህጻናቱ ተስፋ አልባ ህይወት እያሳሰበው ስልኩን አንስቶ ቁምነገር ሰራበት:: የወይዘሮዋን የሟች ልጃቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን አሳዛኝ ታሪክ በቪዲዮ ቀርጾ በማህበራዊ ድህረገጽ ‹‹እነሆኝ›› ሲል አጋራው::
በመልካም ዓይኖች ውሥጥ …
ብዘዎች በእጃቸው የገባውን መረጃ አይተው፣ አንብበው አለፉት፣ ሌሎችም ከንፈራቸውን በሀዘን መጠው ተመሳሳዩን አደረጉ:: የአንዲት ሴት ዓይኖች ግን ከሁሉም ተመልካች የተለየ ሆነ:: ያየችውን ታሪክ እንደዋዛ መተው አልቻለችም:: ፈጥና ስልኳን አነሳች:: በተቀመጠው አድራሻ ደውላም ከሚመለከተው አወጋች::
ልበ ቀናዋ ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ የስራ አጋሮቿን አስከትላ ወሎ መካነሰላም ስትደርስ አዛውንቷ ወይዘሮ አንዷን ልጅ አዝለው፣ ሌላዋን ታቅፈው አገኘቻቸው:: ከሁለት ሰዓት በላይ በእግራቸው ተጉዘው ከስፍራው ደርሰዋል:: እማማ ኑሮ አጎሳቁሏቸዋል:: ህይወት ፈትኗቸዋል:: አሁን ለዓመታት በስቃይ ያሳደጓቸውን ህጻናት ሊለዩ ነው:: ይህ ይሆን ዘንድ እርጅናው፣ ጦርነቱ፣ ችግሩ፣ በዙሪያቸው ቆሟል:: ወይዘሮዋ ብዙ መከራና ስቃይ የከፈሉባቸውን የልጅ ልጆች ከሙዳይ እጅ አስቀምጠው በስንብት ተለዩ::
ሁለቱ ህጻናት በተለየ ጥንቃቄ ከሙዳይ ማዕከል እንደገቡ የመጀመሪያው ጉዳይ ወደህክምና ማድረስ ሆኗል:: ልጆቹ ከተወለዱ ጀምሮ የጸሀይ ብርሀንም ሆነ ሀኪም አይቷቸው አያውቅም:: የችግራቸው መንስኤ ከቤት መወለድ ጋር የሚያጋጥም የመታፈን ችግር መሆኑ ታውቋል::
በወቅቱ ትልቋ ፋንታነሽ ዕድሜዋ ስምንት ዓመት ነበር:: የሰውነት አቅሟ የሁለት ዓመት ህጻን ነው:: ትንሽዋ ጥሩ ሴት ስድስት ዓመቷ ቢሆንም ዕድገቷ የአንድ ዓመት ህጻን አቅምን ይጠቁማል:: ሁለቱም ውስጣቸው የጫጫ፣ በሽታ የመቋቋም አቅማቸው በእጅጉ ያነሰ ነበር::
አሁን እህትማማቾቹ በበሙዳይ በጎ አድራጎት ውስጥ ይገኛሉ:: እንደልጅ መሮጥ፣ መናገር ባይችሉም ጤንነታቸው መልካም ሆኗል:: በግል ሞግዚቶችና ሀኪሞቻቸው እየታገዙ ሁለት የእፎይታ ዓመታትን ተሻግረዋል:: ፋንታነሽና ሙሉ ሴት የትናንቱን ጨለማ አልፈው ከዛሬው ብርሀን ደርሰዋል:: ስለነገው መኖርም እስትንፋቸው በመልካም እጆች ውስጥ ነው::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015