ሃገራት ለኢኮኖሚያቸው የሚያስፈልጋቸውን የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት ሆነ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተለያዩ የሥራ መስኮች ዜጎቻቸውን በማሰልጠን እና ባላቸው አቅም ከሃገር ውጪ በሕጋዊ መንገድ ሥራ የሚያገኙበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ያመቻቻሉ ።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በደላሎች ተታለው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ያልተገባ ተስፋ ሰንቀው ከሀገር እንደ ወጡ በዛው የውሀ ሽታ ሆነው የሚቀሩ፤ ለከፋ ስቃይና መከራም የሚዳረጉ ብዙዎች ናቸው። ለዚህ ደግሞ በአብዛኛው ተጋላጭ የሆኑት የድሀ ሀገራት ሕዝቦች ናቸው ።
በእኛም ሀገር ቀደም ባሉት ጊዜያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻችን ኑሯቸውን ለማሸነፍ፤ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰቦቻቸው ለመትረፍ ብዙ ተስፋ ሰንቀው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት በስፋት ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ጉዟቸው በአብዛኛው ሕጋዊ መንገድን ያልተከተለ በመሆኑ ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል ተገደዋል።
አብዛኞቹ ገና በመንገድ ላይ እያሉ/በጉዟቸው ለሞት፣ ለከፋ እንግልት፣ መከራና ስቃይ ተዳርገዋል። ከብዙ ፈተናዎች በኋላ ያሰቡበት ቦታ ቢደርሱም፤ ምናልባት ጥቂት የሚባሉት ዕድል ቀንቷቸው መልካም ነገርን ይገጥማቸው ይሆናል እንጂ፣ አብዛኞቹ ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆን የሕገወጥ ደላሎች የዳጎሰ ጥቅም ማስገኛ ከመሆን ያለፈ ተጠቃሚ አይሆኑም። ለቤተሰቦቻቸው ሰቀቀን ከመሆንም አላመለጡም።
ምክንያቱም እነዚህ ወገኖች የሕገወጥ ደላሎች መጠቀሚያ ከመሆን ባለፈ፣ በአሠሪዎቻቸው ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች፣ የአካል ጉድለት፣ የሥነልቦና ስብራት ሲደርስባቸው ታይቷል፡፡ ከዚህ የተረፉትም ባልተገባ መልኩም በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት እስር ቤቶች ተግዘው በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም።
ይሄ እየሆነ ያለው ደግሞ በአንድ በኩል የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎቻችን በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ፤ ከዚህም በላይ ችግሩን በዲፕሎማሲ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር የሚመጣጠኑ ስላልነበር እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ እንድንከፍል አስገድዶናል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ግን መንግሥት ይህንን የዜጎች እንግልት ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ዜጎች በውጪ አገራት በሚኖራቸው የሥራ ስምሪት ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችላቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ነው።
ሥራዎቹ በውጪ የስራ ስምሪት መሳተፍ የሚፈልጉ ዜጎች ፤በስምሪቱ እንዴት ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማስቻል ጀምሮ፣ በዘርፉ በሃገራት መካከል የተደረሱ ስምምነቶችን እንዲያውቁ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል የሚፈጥሩላቸው ናቸው።
ከዚህም ባለፈ በውጪ ሃገራት የሥራ ስምሪት የሚሳተፉ ዜጎቻችን ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና መርሆችን ታሳቢ ባደረገ መንገድ በተቀባይ ሀገራት ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚያስችሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ በመድረስ ዜጎች እንደቀደሙት ወቅቶች የከፉ በደሎች እና እንግልቶች እንዳይደርስባቸው የሚከላከሉ ናቸው።
የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን ለማዘመን ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ የሰው ኃይል ስምሪት ሥራዎችን ለማሳለጥ ቴክኖሎጂ መር የሆኑ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ለዚህም 19 አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶች ለምተው 12ቱ ወደ ሥራ ገብተዋል። የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂ የሚመራና የሚተዳደር ለማድረግ እየተሠራ ነው።
ወደ አገልግሎት የገቡ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶቹ፤ አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ዜጎችን እንግልት በመቀነስ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ምን አይነት ሥራ የት አለ? ሥራ ፈላጊዎች የት ቦታ አሉ? የሚለውን በመለየት ሥራ ፈላጊዎችን ከሥራ ጋር ማገናኘት የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ዘመናዊ የገበያ መረጃ አስተዳደር እንዲኖራት ከማድረግ አኳያ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ ያስቻሉም ናቸው። በውጪ አገራት የሥራ ስምሪት ዜጎችንና ሀገርን ተጠቃሚ በማድረግ ሂደትም የሚኖራቸው ፋይዳ የላ ቀ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በልጽጎ ሥራ ላይ የዋለውን የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት መረጃ ሥርዓትን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ሥርዓቱ የዜጎችን የመረጃ አያያዝ ዘመናዊ በማድረግ በዜጎች ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮችን በማስቀረትና በውጭ ሀገራት ሥራ ሥምሪት ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላ ት ረገድ የሚኖረው ሚና ጉልሕ ነው›› ማ ለታቸውም ለዚህ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015