ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ይባላሉ። የተወለዱት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በዚያው በምዕራብ ሸዋ፤ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጊንጪ እና በአዲስ አበባ ተምረዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዕፅዋት ሳይንስ ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ተመርቀዋል። በዚሁ ሙያም ወደሥራ ዓለም በመሠማራት በተለያዩ ተቋማት አገልግለዋል። መልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከልም ለ14 ዓመታት ያህል ሠርተዋል።
የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በአግሮኖሚ የተከታተሉ ሲሆን፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ዶክትሬታቸው) ደግሞ ከሀገር ውጭ በማሌዥያ ፑትራ ዩኒቨርስቲ በጀኔቲክስና በፕላንት ብሪዲንግ (Genetics & plant Breeding) ሠርተዋል።
ዶክተር ማንደፍሮ በስንዴ እና በበቆሎ ላይ ሰፊ ምርምር አድርገዋል። እንደ ሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደገፉ የምርምር ፕሮጀክቶችን መርተው ውጤታማ አድርገዋል። በመንግሥት ኃላፊነትም በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፤ በግብርና ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታነት አገልግለዋል። አዲስ ዘመንም እኚህን ልምድ ያካበቱ ተመራማሪን የዛሬ እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ወደ ኢንስትዩትነት ሲያድግ አብሮ የተሰጠው ኃላፊነት ምንድን ነው ?
ዶክተር ማንደፍሮ፡– ቀደም ባለው ጊዜ /ኤጀንሲ በነበርንበት ወቅት/ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ስንሠራ ቆይተናል፤ አሁን ላይ /ኢንስቲዩት ከሆንን በኋላ/ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ጥናት የማድረግ ኃላፊነት ተጨምሮልናል።
የመጀመሪያው በግብርናው ዘርፍ፤ በአጠቃላይ ከእርሻ እስከ ገበያ ድረስ ያለው እሴት ሰንሰለት ውስጥ ግብርናችን እንዳይሻገር ማነቆ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚሉ ጥናቶችን ማካሄድ ነው። ለዚህም ወደ 48 ተመራማሪዎች አሉን። ጥናቱ ከተሠራ በኋላ ግብረ መልስ ይቀርባል፤ ግብረ መልሱም ታሳቢ ባደረገ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል።
ሁለተኛ ሥራችን ደግሞ የአቅም ድጋፍ ማድረግ ነው። ምክረ ሐሳቡን ለመተግበር የሚያስችል ድጋፍ እንሰጣለን።
ሦስተኛ ሥራችን ድጋፍም ተደርጎ ትግበራው ሊያስቸግር ስለሚችል በትግበራው ላይ እንሳተፋለን፤ ውጤታማ መሆኑን ስናረጋገጥ የሚተገብረው አካል ተሞክሮውን እንዲያስፋፋው እናደርጋለን።
ለአብነት የኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ወይም ኩታ ገጠም እርሻን እንውሰድ። ኢንስትቲዩቱ በመስክ ሥራው ከአርሶ አደሩ ጋር አብሮ ይሰለፋል፤ ሥራውን በተግባር እየሠራም ያሳያል። ኢንስትቲዩታችን ወደ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆን የአርሶ አደር ቤተሰቦች ይዟል። እነዚህ አርሶ አደሮች 85 ሺ ኩታ ገጠም እርሻዎች አሏቸው።
አንድ ኩታ ገጠም የሚባለው ቢያንስ 30 ሔክታር ሊሆን የሚችል መሬት ነው። ከዛ በላይ 100 እና 200ም ሊሆን ይችላል። አንድ ኩታ ገጠም በራሱ ድርጅት እንደማለት ነው። የየራሱ አመራር እንደ ሊቀመንበር፣ ገንዘብ ያዥ የመሳሰሉት አሉት።
ከዚህ በተጨማሪ ግብርና ሚኒስቴር በራሱ መዋቅር 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአርሶ አደር ቤተሰቦችን በስሩ ይዟል፤ በአጠቃላይ እኛ ከያዝነው ጋር ሲደመር ወደ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአርሶ አደር ቤተሰብ (household) በኩታ ገጠም እርሻ የሚያርስ አለ ማለት ነው። ይህ የሚቀጥል ይሆናል።
በተበጣጠሰ ሁኔታ የሚደረገው የእርሻ ሥራ ምርታማነትን ይቀንሳል። ከዚህ አንጻር በአንድ ላይ ተዘርቶ፣ አስፈላጊው ግብዓት ተካቶና ተመርቶ በጥንቃቄ ተከማችቶ ለፍጆታና ለሽያጭ የሚቀርብበት አሠራር ተመራጭና የተሻለ ነው።
በሒደት እርሻውን ወደ አክሲዮን በመለወጥ እያንዳንዱን አርሶ አደር ባለአክስዮን በማድረግ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር መፍጠር ይቻላል። ለዚህም በሙከራ የተያዙት 14 ፕሮጀክቶች አሉ። ይህ በሒደት እየተስፋፋ የሚሄድ ይሆናል።
አራተኛው ኃላፊነታችን ማስተባበርና ማስተሳሰር ነው። በዚህ አግባብ የምንሠራው ከእርሻ እስከ ሱፐርማርኬት ነው። ምክንያቱም ማምረት ብቻ ሳይሆን እስከገበያ ተሰናስሎ መሄድ ይኖርበታል። ይህ የእሴት ሰንሰለቱን የሚያስተሳስር መዋቅር ነው።
አዲስ ዘመን፡- አርሶ አደሮችን የምታስተሳስሩት ከማን ጋር ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ፡- አርሶ አደሮችን የምናስተሳስረው ኤክስፖርት ከሚያደርጉ፣ በሀገር ውስጥ ገበያ ከሚሸጡ ነጋዴዎች እንዲሁም ከኢንዱስትሪዎች ጋር ነው። ለአብነት ያህል ሲዳማ ክልል ውስጥ ለአቡካዶ እርሻ በኩታ ገጠም የተደራጁ አርሶ አደሮች አሉ፤ እነሱን አቦካዶን ለግብዓትነት ከሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች ጋር እናስተሳስራለን።
ኢንዱስትሪው ደግሞ አቦካዶ ዘይት ይመረትና ለሀገር ውስጥም ለውጭም ይሸጣል ብለን ብናስብ፤ ኢንዱስትሪውን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ምርቱን ከሚያቀርቡ ነጋዴዎች ጋር እናስተሳስረዋለን።
ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፤ እንደ ሀገር የቢራ ብቅል የሚያመርቱ አራት ፋብሪካዎች አሉን፤ ለእነዚህ ፋብሪካዎች አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ተደራጅቶ የብቅል ገብስ እንዲያመርት ይደረጋል። በአማራ ክልልም አኩሪ አተር በኩታ ገጠም በማምረት ለግብዓትነት ለሚፈልጉ ፋብሪካዎች ይቀርባል። ይህን አይነቱን ትስስር በመሥራት ላይ ነን።
ከማስተባበር ጋር ተያይዞ የምንሠራቸው ሥራዎች፤ አንደኛ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ላይ ክለሳ ማድረግ ነው ፤ ይህንን አሁን ላይ ተግባራዊ አድርገነዋል። ሁለተኛው በኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ለውጥ ላይ መሥራት ሲሆን፣ ሦስተኛ ዲጂታል አግሪካልቸርን እውን ማድረግ ናቸው።
አሁን ላይ በእነዚህ ሦስቱ ላይ እየተንቀሳቀስን ነው። ሥራዎቹን በቀጣይ በሰፊው ለመሥራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተን በ2016 ዓ.ም ወደ ሥራ ለመግባት እየተንቀሳቀስን ነው። በፍኖተ ካርታ ዝግጅቱ ወደ 22 መሥሪያ ቤቶች ተሳትፈውበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ሌሎች ኢንሼቲቮች አሉን፤ አስቀድሜ እንደገለጽኩት ኩታ ገጠም ከሆነ በመካናይዜሽን ነው። 10 የመካናይዜሽን ማዕከላትን አቋቁመናል። እነርሱም አገልግሎት በኪራይ ሰጥተው ገንዘብ ያገኛሉ። ሁለተኛ የጋራዥ አገልግሎት ይሰጣል። ከመካናይዜሽን አገልግሎት በተጨማሪ ማዕከሉ ሥልጠና ሰጥቶ በሰርተፍኬት ያስመርቃል። የተለያዩ የእርሻ ማሸነሪ አንቀሳቃሾችን በኦፕሬተርነት ያሰለጥናል።
አዲስ ዘመን፡- በዝናብ ላይ መሠረት ያደረገውን ሀገራዊ የእርሻ ሥራ በዚህ ልክ ወደፊት ማስኬድ ይቻላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፡- ዝናብ ተከትለን አጠቃላይ ሀገሪቱ ውስጥ ያለ የከርሰ ምድር ውሃ የት ቦታ ምን ያህል አለ የሚለውን ሠርተናል። በመቀጠልም ሁሉም ቦታ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለማይኖር በፀሐይ ብርሃን ኃይል በማመንጨት አርሶ አደሮች ውሃን ከከርሰ ምድር እያወጡ እርሻ እንዲያርሱ የሚያስችሉ ሥራዎችንም እየሠራን ነው።
በርካታ ቤተሰቦች በዚህ ተደራጅተው ትላልቅ ገቢ አግኝተው የተለወጡ ነው። በፀሐይ ብርሃን ኃይል የማመንጨቱ ሥራ ቦታ ይፈልጋል፤ የሚመነጨው ኃይል ለብዙ ሄክታር መሬት ይሆናል። ይህንን ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም ተጨማሪ የሚለማ መሬት ሊያስፈልግ ይችላል። በዚህም ሦስቴ ማምረት የሚቻልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። በዚህ ደረጃ 9 ወረዳዎች ላይ ሙከራ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር ማሳካት በአስር ዓመቱ የልማት ግብ ትልቁ ሥራ ሆኖ ቀርቧል፤ ይህ ምን ያህል እየተተገበረ ይገኛል?
ዶክተር ማንደፍሮ፡- መዋቅራዊ ለውጥ የምንለው ከእርሻ ወደ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚያችን እንዲሸጋገር ለማድረግ አስቀድሜ የጠቀስኩት የኩታ ገጠም አመራረት ሥርዓት ነው። ከዛ የሚገኘው ትርፍ ምርት ገቢ ማስገኘቱ ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሄድ ያደርገዋል። መካናይዜሽን ስንጠቀም ሰው ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሄድ ያደርጋል።
በመካናይዜሽን ስናመርት ብዙ ትርፍ ምርት አለ፤ ይህ ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ እንዲሄድ ያደርገዋል። አምርቶ ከመመገብ ለገበያ ወደ ማምረት ደረጃ ያደርሳል። እንደሱ ሲሆን፣ አጠቃላይ እርሻ ላይ የሚቆየው የሰው ኃይል በመካናይዜሽን እየቀነሰ ይመጣል። ስለዚህ የሰው ኃይሉ ወደ ኢንዱስትሪ እየሄደ ይመጣል።
ኢንዱስትሪው ከእርሻ ሁለት ነገሮችን ያገኛል። አንደኛ ግብዓት ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ የሰው ኃይል ነው። እነዚህ ሁለቱ የስትራክቸራል ትራንስፎርሜሽን የሚያመጡ ኃይሎች ናቸው። ከዚህ ላይ የሚጨምረው ካፒታል ብቻ ነው። ካፒታል ሲጨመርበት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር እውን እየሆነ ይሄዳል። ይሄንን በደንብ አይተናል።
ለምሳሌ ስንዴን ብንወስድና ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት በስንዴ ዙሪያ የሠራነው ተሞክሮን ብናይ ትርፍ ማምረት እንደምንችል የሚያሳየን ነው፤ በትርፍነት ያመረትነው ደግሞ ብዙ ተዋናዮችን የሚያካትት ነው።
ተጨማሪ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በመስኖ የሚመረተው ስንዴ በአንድ ሄክታር ላይ የሚኖረው የሰው ጉልበት በጣም ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ሰዎችም በቀጥታ ሥራ ያገኛሉ። ምክንያቱም በክረምት ብቻ አምርቶ ለስምንት ወር ቁጭ ይል የነበረው የሰው ኃይል ወደ ሥራ ገባ ማለት ነው።
ይህ ማለት በቀጥታ እርሻ ላይ የሚፈጠረው ሥራ ብቻ ሳይሆን እርሻ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች ምግብና መሰል ነገሮችን ስለሚፈልጉ ያንን የሚሠራና እነሱ የሄዱበት ቦታ እየሄደ የሚመግብ ሁሉ የሥራ እድሉ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው።
በተጨማሪም ምርትን በማጓጓዝ ሒደት ውስጥም ሥራው እየተሳለጠ ይሄዳል። ይህ አይነቱ አካሄድ ነው ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽኑን እውን የሚያደርገው። ለምሳሌ ከዚህ ጋር ተያይዞ ቲማቲም በብዛት ከተመረተ ቶሎ እንዳይበላሽ የሚያደርጉ ብዙ ኢንዱስትሪዎች ሰለሚኖሩ በቀላሉ እየታሸጉ የሚሸጡበት ሁኔታ ይፈጠራል።
አሁን እየተሠራ ያለው በተለይም ደግሞ ትኩረት ሰጥን በፕሮግራም ደረጃ የያዝናቸው የገቢ ምንጮች አሉ። እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ የአኩሪ አተርና መሰል ተጠቃሽ ናቸው። ለምሳሌ አኩሪ አተር ይመረታል፤ ወደ ኢንዱስትሪ ይሄዳል፤ ዘይት ይወጣዋል፤ ተረፈ ምርት አለው። ያ ተረፈ ምርት ለዶሮ ወይም ለከብቶች ትልቅ ምግብ ይሆናል። ከሚመረተው ከእያንዳንዱ ምርት የተመጣጠነ ምግብ የሚገኝ ሲሆን፣ ከምግብ ዋስትና በተጨማሪ በሥነ ምግብ የዳበረ የአመጋገብ ሥርዓት እየተፈጠረ ይሄዳል ማለት ነው።
ስለሆነም የመስኖ ልማት በርካታ ነገሮችን የሚያንቀሳቅስ ይሆናል። እኛ አገር ደግሞ የፀሐይ ችግር የለም። ለዘጠኝ ወይም ለአስር ወራት ያህል የፀሐይ ብርሃን እንናገኛለን። ነዳጅ ሳንጠቀም፤ በፀሐይ ብርሃን በሚፈጠር ኃይል አምርተን በርካታ ነገሮችን ማሻሻል እንችላለን።
መሬት ላይ ያለው በተለይም በኩታ ገጠም ተመርቶ የኢንዱስትሪ ግብዓትን ከማቅረብ ብሎም ምርቶችን ኤክስፖርት ከማድረግና የምግብ ደህንነት ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞ ትልቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም ወደ ኢንዱስትሪ ሊያሸጋግረን የሚችለውን መስመር ይዘናል ማለት እንችላለን።
በእርግጥ ያንን አጠናክሮ መሄድና ሽግግሩን እውን ማድረግ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል። ያ ኢንቨስትመንት ካለ ምንአልባትም ከዚያ ባጠረ ጊዜም ሽግግሩን እውን ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሁን ስንዴን በስፋት በማምረት በኩል እየሠራች ትገኛለች፤ ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣናው ካሉ አገራት መካከል ግብጽ ስንዴ በማምረት ላይ ትገኛለች፤ ይህቺው ሀገር በስፋት አምርታ ዋጋውንም አሳንሶ እስከመሸጥ መድረሷ ይነገራልና ይህ አይነቱ አካሄዷ ኢትዮጵያን አይፈትናትም?
ዶክተር ማንደፍሮ፡– አይፈትናትም፤ ኢትዮጵያ እንዲያውም ብዙ ዕድሎች አሏት። አሁን አጠቃላይ የሌላውን አገር ትተን አፍሪካን ብቻ ብንመለከት ከእኛ የተሻለ ስንዴ ምርት ያላት ግብጽ ብቻ ናት። እኛ ወደ 82 ሚሊዮን ኩንታል እንናመርታለን፤ ግብፆች ወደ 100 ሚሊዮን ያመርታሉ። አሁን ባለንበት ሁኔታ እነሱ 100 ሚሊዮን፤ እኛ 82 ሚሊዮን ኩንታል አምርተናል። አሁን ደግሞ በመስኖ የሚመረተው እየተጨመረ ሲሄድ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንበልጣቸዋለን።
እኛ የመስኖ ስንዴ ስንጀምር እጥረታችን 25 በመቶ ነበር። 75 በመቶ ደግሞ ራሳችንን እንችል ነበር። ግብፅ መቶ ሚሊዮን ኩንታል ብታመርትም ተጨማሪ መቶ ሚሊዮን ኩንታል ከውጭ ታስገባለች። ስለምታመርት ራሷን አልቻለችም። ግብፅንም ጨምሮ ሌሎች አፍሪካ አገሮች በሙሉ ለኢትዮጵያ ስንዴ የገበያ መዳረሻ ናቸው። ይህ ትልቅ ዕድል ነው። ስለዚህ ግብፅ ራሷን የምትችለው 50 በመቶ ነው። ሌሎች አገሮች ደግሞ ምናልባት አንድም ሁለትም በመቶ ራሳቸውን የሚችሉ አሉ። ከዛ በታችም የሆኑ አሉ። ስለዚህ 53ቱ አገሮች ለኢትዮጵያ ገበያ ናቸው።
አሁን ያለው ዋጋ ከዓለም ዋጋ ጋር ስናስተያየው የእኛ የስንዴ ዋጋ ይበልጣል። ይህ ትክክለኛ የገበያ ሥርዓት አይደለም። ኤክስፖርት ለማድረግ መወዳደሪያ ነጥቡ ሦስት ነው። በብዛት፣ በጥራና በዋጋ ነው። እኛ በአሁኑ ወቅት በዋጋ ተወዳዳሪ አይደለንም፤ ይህን ዋጋ ማውረድ የሚቻለው አርሶ አደሩ በትክክል ከምግብ ፍጆታ የተረፈውን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ሲችል ነው።
በአሁኑ ሰዓት አርሶ አደሩ አንድ ኩንታል ስንዴን በሶስት ሺ ብር ቢሸጥ ትርፋማ ነው። አንዳንድ ነጋዴዎች ያለአግባብ ለመበልፀግ የሚያደርጉት መደበቅና እያወጡ መሸጥ ይስተዋላል። ከዚህ በተጨማሪ ስንዴ በተለያየ አቅጣጫ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ይወጣል። ይህንን ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ቢገቡና መደበኛ በሆነ መንገድ ቢሸጥ የተሻለ ዋጋ ሊያወጣ የሚችል ነው ።
ትልቁ መወዳደሪያ ደግሞ የምናመርትበት ዋጋ ነው። የምናመርትበት ዋጋ ውድ ከሆነ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም። ግን አሁን ማየት ያለብን አሁን ያለውን የስንዴን ዋጋ ሳይሆን፤ አንድ ኩንታል ስንዴ በስንት ብር አመረትን የሚለውን ነው። ይህን ስናወዳድር እኛ በጣም ጥሩ ተፎካካሪዎች ነን።
ጥራትን በተመለከተ የእኛ ስንዴ ችግር የለበትም፤ ለስንዴ ተስማሚ የሆነ አየር ንብረት አለን። በክረምትም በበጋም ማምረት እንችላለን። ሌላ አገር እንደዚህ የተመቻቸ ዕድል የለም። ስለዚህ ይህ ተጨማሪ መፎካከሪያችን ስለሚሆን ዓመቱን ሙሉ ሕዝባችንን መመገብ እንዲሁም ወደ ውጭ መላክ እንችላለን።
በሌላ ሀገር የሚመረተው አንዴ ነው። በበረዶ የተሸፈነ ስለሚሆን በረዶው እስከሚያልፍ ይጠብቃሉ። በረዶው ካለፈ በኋላ ያለው ወቅት ጠባብ ነው። ትልልቅ አምራች የሚባሉት እንደ ራሺያ፣ ዩክሬን፣ ጀርመን የመሳሰሉት በዚህ የታጠሩ ናቸው። ስለዚህ እኛ ትልቅ ዕድል አለን።
ልክ እንደዚያው ሩዝን ብንወስድ፤ በየዓመቱ እየጨመረ ያለው የሀገር ውስጥ ፍላጎታችን 30 በመቶ ነው። የምናመርተው በጣም ትንሽ በመሆኑ 75 በመቶ የምናስገባው ከውጭ ነው። ይህ ማለት የስንዴው ግልባጭ ማለት ነው። በሩዝም ልክ እንደ ስንዴው ሁሉ ራሳችንን መቻል አለብን፤ ወይም ምርት ወደ መላክ መግባት አለብን። ከዚህ አኳያ ከዚህ ክረምት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ መርሐ ግብር አለ።
አሁን ሦስት ትልልቅ ፕሮግራሞችን ይዘናል። ስንዴ አንዱ ሲሆን፣ ውጤታማ ሆነናል። ይህን ማስጠበቅና ማሳደግ ይገባል። ሁለተኛው ሩዝ ነው፤ ጀምረናል። ሌላው ለምግብ ዘይት የሚሆነው አኩሪ አተር ነው፣ ይህ የዘይት ጉዳይ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስወጣናል። ሰው ስለዚህ ጉዳይ አይናገርም። ስንዴ ከመንግሥት ካዝና ስለሚወጣ ይታያል። ዘይት ግን በተለያየ መንገድ ይገባል። በሕጋዊም በሕገወጥ መንገድም ይገባል።
ይህ ተመዝግቦ ወይንም ከማዕከላዊ ገበያ ዶላር ተወስዶ ስለማይገዛ አይታይም እንጂ ብዙ ብር ያስወጣናል። ስለዚህ አኩሪ አተር ላይ ቢሠራ የምግብ ዘይት ነው። መንግሥት ሩዝ አያስገባም ግለሰቦችና ነጋዴዎች ናቸው የሚያስገቡት። ሩዝን መንግሥት የሚያስገባው ቢሆን ያማል። እነዚህ ሦስቱ አንድ ላይ ሲደመሩ በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያስወጡናል።
አሁን ስንዴን ዘግተናል። የሚቀረን የምግብ ዘይትና ሩዝ ነው። ይህን ካሣካን በየዓመቱ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ይኖረናል ማለት ነው። ስለዚህ ማዳበሪያና ትራክተር መግዛት፣ ፋብሪካ ማቋቋምና ሌሎች ነገሮችን መግዛት እንችላለን። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚያሸጋግረን እነዚህ ላይ ለውጥ ካመጣን ነውና ትልቅ ነገር ይሆናል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የዶሮ ኢንዱስትሪ፣ የወተት ኢንዱስትሪና የእንስሳት ተዋፅዖ ውስጥ ያሉት ደግሞ በጣም በፍጥነት ሊሄዱ የሚችሉ ናቸው። ማር ያልተወራለት፤ ግን ቦታ የማይወስድ ሥራ ነው፤ ዛፍ ባለበት ቦታ ላይ ማር ማምረት እንችላለን። እነዚህ ላይ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በማፍሰስ በትኩረት ከሠራን ብንሠራ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንችላለን።
በስንዴ ውጤታማ የሆንነው ትኩረት አድርገን በዓመት እስከ ሁለትና ሦስት ጊዜ እናምርት ብለን የሰው ኃይልና ገንዘብ መድበን በመንቀሳቀሳችን ነው። ለሩዝም እንደዚህ ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በስንዴ ምርት ላይ የተገኘውን ውጤት የሚያሳንሱ እና ከፖለቲካ ጋር የሚያጠጋጉ አሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ማንደፍሮ፡- ስንዴ በዓለም ላይ የፖለቲካ አንዱ መገለጫ ነው። ገጽታ ይገነባበታል። የሀገር ገጽታ እንዲገነባ የሚፈልግ አካል ደስ ይለዋል፤ ይህን የማይፈልግ አካልም አለ።
ኢትዮጵያውያን ተፎካካሪ ይሆናሉ ሲባል በሰሙት ነገር ብቻ መበለጥን የማይፈልጉ ሀገራትም አሉ። በመሆኑም ይህን የማይፈልጉ አካላት ስም ያጠለሻሉ። ይህ ችግር በእነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ሀገር ውስጥ ባሉ አንዳንድ አካላትም ሲንጸባረቅ ይስተዋላል። ከዚህም የተነሳ ስንጀምርም ብዙ ፈተና ነበር። በተለያየ መድረክ ላይም ብዙ ጭቅጭቅ ነበረው፤ ችግሩ ባልተማሩ ብቻ ሳይሆን በተማሩትም ዘንድ ይታይ ነበር።
መንገዱ የተጠረገው ሥራውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝቡም ለፓርላማም ከገለፁ በኋላ ነበር። ከዚያ በፊት ገንዘብ ለመመደብም ብዙ ችግሮች ነበሩ። ከዚያን በኋላ በሁሉም አቅጣጫ እንደ መመሪያ፣ እንደ አዋጅ ተወሰደ። ሁሉም ሰው ወደ ሥራ ገባ። አሁን ራሱ ያመረትነውን ምርት እያለ እንኳ ምርት የለም የሚሉ አሉ። በእርግጥ የምርት ዋጋ ተሰቅሏል፤ ጥያቄ የለውም። ነገር ግን ይህ የምርት አለመኖር መገለጫ አይደለም።
ኢትዮጵያ ስንዴ ወደውጭ ላከች የሚባለው ዜና በሌሎች ዘንድ አይወደድም፤ እንግዲህ በተለያየ ደረጃ ያንን እንገልጸዋለን እንጂ እንደሀገር ከተሸጠው ስንዴ አብዛኛው የተከፋፈለው ሀገር ውስጥ ነው። የውጭ እርዳታ ሰጪ ሀገራት ስንዴያችንን ከእኛ በዶላር በመግዛት በሀገር ውስጥ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች አከፋፍለዋል።
አንድ አፌን ሞልቼ የምናገረው ነገር ቢኖር ስንዴ አገር ውስጥ አለ። አሁንም በመስኖ እየተመረተ እየገባ ነው። አሁን ደግሞ በክረምት እንሠራለን። ስለዚህ የስንዴ እጥረት የለም። ያለው ያለአግባብ የተፈጠረ የዋጋ ንረት ነው። እኛ ወደ ፊት በስንዴ ንግድ ወደ ዓለም ገበያ ለመግባት ትልቅ ዕድል አለን።
ከብራዚልና ከአውስትራሊያ እያመጡ የሚሸጡ ስንት ሺ ኪሎ ሜትር አቋርጠው የሚመጡ አሉ። እኛ እዚሁ ለጅቡቲና ለኬንያ እንዲሁም ለታንዛኒያም ብንሸጥ ራሱ ትልቅ ገበያ ነው። ግብፆች ራሳቸው ከእኛ መግዛት ይፈልጋሉ። የእኛን ማምረት ይከታተላሉ። ውጤታችንንም ይለካሉ።
ስንዴ ማምረታችንን እንቀጥላለን፤ እያመረትንና ውጤታማ እየሆንን ስለመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ስንዴ ውጤታማ መሆኑን ያረጋገጠው የአፍሪካ ልማት ባንክ ነው። የቡድን ስምንት ስብሰባ ላይ ባንኩ ‹‹ኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ላይ ትራንስፎርም አድርጋለች›› ሲል ለዓለም አብስሯል። የዓለም አቀፉ ሚዲያም የዘገበው ያኔ ነው።
ድሮ የነበረውን የተሳሳተ ፍረጃ ትተው በሀገሪቱ ስላለው የስንዴ ውጤታማነት እያወሩ ነው። ወደ ሰባት እና ስምንት ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከስንዴ ተሞክሯችን ትምህርት ወስደዋል። ይህ የሚሳየው በተለያየ መንገድ ውጤታማ መሆናችንን ነው። በስንዴ የሠራነውን ውጤታማ ሥራ በሌሎቹም መድገም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በስንዴ ማምረት ውስጥ ብዙ ሕፀፆች እየተፈለጉ ሲጠቀሱ ቆይተዋል። የታለፈው ፈተና ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር ማንደፍሮ፡- በርካታ ተግዳሮቶች ነበሩ። የመጀመሪያው የሚደግፍ ሰው ጥቂት ነበር። በገንዘብም ሆነ በቴክኒክ ድጋፍ ሳይሆን በቃል የሚደግፍ ራሱ አልነበረም። ባለሙያዎቹ የሚሠራውን ሥራ፣ የተደረገውንና የተገኘውን ውጤት ሳይሆን መጥፎ ጎኑን የሚያነሱ ነበር። በተለይ በሀገሪቱ ያለው መሬት በጨው ይበላል የሚሉም አልታጡም ነበር። በተለይ በኃላፊነት ላይ ካሉ አካላት ይህን መስማት ከባድ ነገር ነበር።
ሌላው ትልቁ ፈተና የገንዘብ ችግር ሲሆን ፤ማን ይሥራው የሚለው ሌላው ፈተና ነበር። ሥራውን የጀመርነው ምርምር ውስጥ እያለን ነው። ምርምር ውስጥ ሠራተኛውን አሳምኖ ለዚህ ሥራ ማሰማራት ቀላል አይደለም። ‹‹ሥራችን አይደለም፤ እኛ ተመራማሪዎች ነን፤ አይመለከተንም፤ አምራች አይደለንም›› ሊሉ የሚችሉ ሰዎችን አሰባስቦና አሳምኖ ቡድን ሠርቶ፣ ማሰማራት ፈተና ነበር።
ከዛ በኋላ ግን የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሃሳቡን ገዛው። ውጤትም አየበት። እነርሱ ደግሞ ተረባርበው ወደ ሥራ ሲገቡ ቀጥሎ ያለው በተዋረድ ወደ ግብርና በማቅናት የባለሙያዎቹን አመለካከት መቀየር ሌላ ፈተና ነበር። እንደዛ ተደርጎ ውጤቱ እየታየ ሄደ። ይህንን እየሠራን ውጤታማ መሆኑን ሲያረጋግጡ ሌሎችም ገቡበት።
በመቀጠል የፓርላማ አባላቶችን በተለይም ቋሚ ኮሚቴዎችንና ገንዘብ ሚኒስቴርን፣ በሚኒስትር ደረጃ ያሉትን በሙሉ እና የክልል ፕሬዚዳንቶችን ይዘን የተመረተውን ማሳየት ጀመርን። ስናሳያቸው በበጋ ምንም አረንጓዴ በሌለበት ቦታ ስንዴውን ሲያዩ አላመኑም። ሁሉም ነገር ተቀየረ። መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሰጡት። ተጨማሪ ገንዘብ አገኘን። ግብርናም ቡድን አቋቋመ።
ሌላው ፈተና የነበረው አነስተኛ አርብቶ እና አርሶ አደሮች ላይ ነው፤ ይሁንና የተገኘው ምርት አርብቶ አደሮች ዘንድ አነስተኛ ቢሆንም ሁለት ሔክታር መሬት ላይ የዘራ አርሶ አደር ደግሞ ከመቶ ኩንታል በላይ አገኘ። ይሁንና ምርቱን ከገበያ ጋር ማስተሳሰሩ ፈተና ሆነ። በዚህ አካሄድ ደግሞ ከአርሶ አደር እምነት ለማግኘት ያስቸግራል።
የሚመጣው ነጋዴ ደግሞ ከአርሶ አደሮቹ በርካሽ ዋጋ መግዛት ይፈልጋል፤ እናም ገበያ ሁለተኛው ትልቅ ፈተና ነበር። ከዛ የተለያዩ በተለይ የእርዳታ ማስተባበሪያ ተቋማት እንዲገዙ ጥረት ተደረገ። በሒደት የተመረተበት ቦታ እየሄዱ መግዛት ጀመሩ። ዳቦ ቤቶችም ወደግዥው ገቡ። በመጨረሻ የገበያው ችግር ተፈታ።
ለዚህ ውጤታማ ሥራ የተከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሊሸለሙ የሚገባቸው ልጆች አሉ። ለሦስት ወራት ከቤተሰብ ተነጥለው በአርሶ አደሩ ቀዬ ተቀምጠው የሠሩ ልጆች አሉና።
ከዚህ ጋር አያይዤ የማነሳው ነገር ቢኖር በለመድነው አሠራር አዲስ ነገር አናመጣም፤ ለየት ያለ ሐሳብን የምናስተናግድበት መድረክ መኖር አለበት። በዛ መልክ ሐሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ስህተት እንኳ ቢሠሩ መደገፍና መበረታታት አለባቸው። ስለዚህ ከስህተት መማር ይቻላልና ለመሞከር ዕድል መሰጠት አለበት ባይ ነኝ።
ሌላው ደግሞ ከነቀፌታ ይልቅ ብንተጋገዝና ብንተባበር መልካም ነው። ጥሩ የተሠራውን የማበረታታት ሚዛናዊነት ስለሚጎድለን ብንተጋገዝ ጥሩ ነው። መደማመጥም ሌላው ጉዳይ ነው። እርስ በእርስ መደማመጥ፤ ፖለቲከኞችም ኤክስፐርቶችም መተጋገዝ ያስፈልገናል፤ እንደአንድ አገር ዜጋ በያለንበት ብንሠራ ድህነትን እናሸንፋለንና ለትውልድ እንሥራ እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ማንደፍሮ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015