የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የንግዱ ማህበረሰብ ውይይት ዋነኛ ትኩረት ምን ነበር?

ባሳለፍነው ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ የትኩረት ማዕከል ሆነው ከከረሙት ጉዳዮች አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት ነው። አንድ ሰዓት ከ13 ደቂቃ የፈጀው ውይይት ሙሉ ክፍል በመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢዎች ለመላው ሕዝብ እንዲደርስ ተደርጓል።

በዛሬው ወቅታዊ ትንታኔ አምዳችን ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ያነሷቸውን ጥያቄዎች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡትን ምላሽ ማብራሪያ ተዳስሷል።

በንግዱ ማህበረሰብ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ከእነዚህም መካከል ሕገወጥ ንግድ ሕጋዊ ነጋዴዎች ከሥራ ጫና እንዲወጡ ጫና ማሳደሩ፤ መንግሥት ከነዳጅ አቅርቦት እጥረት እና ከተተመነው የመሸጫ ዋጋ ውጪ ጨምሮ የመሸጥ ሁኔታ መኖሩ፣ የፋይናንስ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው ገደብ ባንኮች የንግድ ሥራን በደንብ መደገፍ የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦት እንዳይኖር ማድረጉ፤ እንዲሁም የባንኮች የማበደር አድማስ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ መወሰን በተለይም ታችኛው ደረጃ ላይ የሚገኘው ነጋዴ ኮላተቶራል ማቅረብ ስለማይችሉ በቂ ገንዘብ እያገኙ አለመሆናቸው ተጠቃሽ ናቸው።

መንግሥት ዘላቂ ሰላም ከማስፈን አኳያ ምን እያሰበ ነው? የግል ዘርፉ እንደ የቤት ሥራ መውሰድ ያለበት ነገር ምንድን ነው ? ሕገወጥ ኬላዎች በተለያዩ ቦታዎች ተዘርግተው ያሉ የተለያዩ ቀረጦች በደረሰኝ ያለደረሰኝ ገንዘብ የመቀበል እና የኮቴ ተብለው የሚጠየቁ ክፍያዎች የንግዱ ማህበረሰብ ራስ ምታት በመሆናቸው መፍትሔ ይሰጣቸው፤ እንዲሁም የኢኮኖሚክስ ዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ተጠይቋል።

በተጨማሪም ቢሮክራሲና መልካም አስተዳደርን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርበዋል። የሙያ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ዝቅ ብለው መንግሥትና ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት የሚወጡ በትክክል አገልጋይ የሆኑ በጣም ብዙ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ኃላፊዎች ቢኖሩም በጣም ጥቂቶቹ ገንዘብ ቢሮ ውስጥ እስከ መቀበል ድረስ ይደርሳሉ። ከፍተኛ የእውቀትና የልምድ እጥረት ያለባቸው ባለሙያዎች አሉ። በእዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሠራ ነው የሚል ጥያቄ ተነስቷል።

ከተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ አምስት መሠረታዊ ችግሮች አሉባት ብለዋል። የወረስነው ድህነትና ድህነትን ለመውረስ የተዘጋጀ ትውልድ መኖሩ ከአምስቱ ችግሮቻችን የመጀመሪያው ነው ብለው፤ ድህነትን ወርሰን ለማውረስ ያለን ፍላጎትና መሻት ከፍተኛ መሆኑን በካሳንቺስ በተግባር ታይቷል ሲሉም ገልጸዋል።

ሁለተኛው ችግር መዋቅራዊ መሆኑንና እንደሀገር ጠንካራ ተቋም አለመኖር መሆኑን ጠቅሰው፤ ጠዋት የሰጠውን አገልግሎት ከሰዓት መድገም የሚችል ተቋም አለመኖሩ ለእዚህ ችግር ማሳያ ነው። ችግሩን ለመፍታት ሪፎርም ሲጀመር በዘርና በሃይማኖት ስም ታርጋ የመለጠፍ ባሕል በስፋት ታይቷል ነው ያሉት።

ከአራሹ ይልቅ ተኳሹን፤ ከሠራተኛው ይልቅ አጥፊውን የሚያወድስ የአመለካከት ችግር መስተዋሉ ሦስተኛው ችግር መሆኑን ጠቁመው፤ ጀግና ጠዋትና ማታ ሠርቶ ልጆቹን የሚያሳድግ ሳይሆን ክላሽ አንግቶ ሰውን የሚሳደብ ሰው ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ችግር መኖሩን አንስተዋል። በአራተኛነት ያስቀመጡት ግብርናን በመጀመር ረጅም ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ከእርሻ ጀማሪዎች መሀል ብትሆንም፤ እስካሁን ምርታማ አለመሆኗ የስልተ ምርት ችግር መኖሩን ማሳያ ነው። ከችግሩ ለመውጣትም የተሻለ ውጤታማ መሆን የምንችልባቸው መንገዶችን ማሰብና መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የአገልግሎት ችግርን በአምስተኛው ረድፍ ላይ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሥራ ሠርተው ምን ችግር እንዳለበት የማይረዱ፤አገልግለው የማያውቁ ሰዎች ናቸው ስለ ሥራ የሚናገሩት፤ ይህም የማገልግል ችግር ስለመኖሩ አመላካች ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ የሚስተወሉ ስር የሰደዱ የአመለካከት ችግሮች ካልተፈቱ ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት ከባድ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።

ገበያን ለአንድ ሀገር የሕልውና መሠረት እንደ መሸጋገሪያና እንደ መሠልጠኛ መውሰድ ካልተቻለ ሀገር መገንባትም ሆነ ማፅናት እንደማይቻል ገልጸዋል። ገበያና ንግድ ለአንድ ሀገር እድገትና ውድቀት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ገበያ ሀገር ይገነባል፤ ገበያ እውቀት ያሸጋግራል፤ ገበያ ሥልጣኔ ያመጣል፤ የአኗኗር ዘይቤን ይቀይራል ነው ያሉት።

ገበያ ለነጋዴዎች ትርፍ ማግኛ ብቻ ሳይሆን ሥልጣኔ ማግኛ፤ የሀገር መገንቢያ፤ ለአንድ ሀገር ሕልውና ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ የከረመ እና አዲስ ፈተናዎች እንዳሉባት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የከረመውን ፈተና እየጠገኑ ብቻ ሳይሆን አዲሱንም ፈተና እየፈቱ መሄድ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች በሥራችሁ ዓለምን ለማየት እድል ስላላችሁ ነገን ታሳቢ ያደረጉና ክፍተት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት ይገባችኋል ሲሉ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡትን የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብ ተወካዮች አሳስበዋል።

ሀብታም ነጋዴም ይሁን ባለሥልጣንም ይሁን ተራ ሠራተኛ፣ የሆነች አጋጣሚ ሲያገኝ አታልሎ መውሰድን ብልጠት አድርጎ ነው የሚወስደው፤ ይህ መታረም አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማታለል በመበራከቱ ምክንያት ስፍር ቁጥር የሌለው ኮንትሮባንድ ስለመኖሩ ተናግረዋል።

ነዳጅን ብቻ ብንመለከት ከውጭ ገዝተን ነው የምናመጣው፤ የእኛ ሰዎች ግን አስበውና አቅደው በድጎማ የገባውን ነዳጅ ወደ ሁሉም ጎረቤት ሀገራት አውጥተው ይሸጣሉ ብለዋል። ድጎማ አድርገን የምናመጣው ነዳጅ ኢትዮጵያን ሳይሆን ጎረቤት ሀገራትን ነው እየጠቀመ ያለው። ወርቅ፣ የቁም እንስሳትና ስንዴም በተመሳሳይ በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እየወጡ ነው ብለዋል።

ማጭበርበር ልክ እንደ እውቀት ስለሚታይ እንደፈጠራ ይወሰዳል፤ የጋራ ሕልምና ራዕይ የሌለው ሀገር እንደ እዚህ ነው የሚያደርገው ሲሉ ነው የገለጹት። በሁሉም ሰፈር መስረቅና ማጭበርበር ልማድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይሁንና መንግሥት የሚያመጣውን እያንዳንዱን ገንዘብ የሚያውለው ለልማት መሆኑን ተናግረዋል።

የሙስና በር የሚከፈተው የንግዱ ማህበረሰብ ራሱ በሚሰጠው ጉቦ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ዘመናዊ አሠራርን መዘርጋት ሌብነት ይቀንሳል፤ ውጤታማነት ይጨምራል። በፌዴራል ደረጃ አብዛኛው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጣቸው ወደ አውቶሜሽን እየገባ ነው። በአብዛኞቹ የክልል ከተሞችም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የማገልገል ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችል የአውቶሜሽን ሥራ ከፌዴራል ጀምሮ በአርባ ምንጭ፣ በሀዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ ለመጀመር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

መንግሥታዊ ሌብነት አለመኖሩን ጠቁመው፤ ለአብነትም በአዋሬ መንደር የተገነባውን የኮሪዶር ልማት ከመጽሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ መገንባቱን አውስተዋል። ሌቦችን ለመቀነስ የንግዱ ማህበረሰብ ጥቆማ በማድረግ እገዛውን እንደሚያደርግ በመተጋገዝ ሙስናን በብዙ መቀነስ እንደሚቻል አመላክተዋል።

ዲጂታል አገልግሎትን ማጠናከር የሌብነት በር የሚዘጋ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራበትም ተናግረዋል። ሌብነትን በተመለከተ በመረጃ የተደገፈ ጥቆማ የሚቀርብ ከሆነ የትኛውም አመራር ተጠያቂ ይሆናል። ሕገወጥ የኮቴ ክፍያዎችን ለማስቀረት ክፍያ የሌለበት ፍተሻ የተጠናከረበት የኬላ ቁጥጥር ሥርዓት እንዘረጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የአገልግሎት ጥራትና ፍጥነትን ለመጨመር እንዲያስችል የተማረ የሰው ኃይላችን የጥራት ችግር ከትምህርት ፖሊሲ ችግር ጋር የሚያያዝና የቆየ በመሆኑ ልምድ እስኪያገኝ ድረስ እርስ በርስ እየተደጋገፉ መሥራት ይጠይቃል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በኢንዱስትሪ የመስክ ልምምድ የማድረግ ግዴታ እንደሚጣልባቸውና ይህም ነባራዊ ሁኔታን የተረዳ ገበያውን የሚመጥን የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚያስችል ገልጸዋል። በእዚሁ መሠረት ከተመረቀ በኋላ ለአንድና ሁለት ዓመት በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሠራ እያደረግን ወደ መደበኛ ሠራተኛነት በማምጣት ላይ ነን ብለዋል።

ሰላምን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ተናግረው፤ መንግሥት የሚያልመውን ብልፅግና ያለ ሰላም ማሳካት አይችልም ብለዋል። መንግሥት የሰላምን ዋጋ እና የማይተካ ሚና በውል እንደሚገነዘብ አጽንኦት ሰጥተውም አብራርተዋል። አሁን ላይ ሰላም እየተባለ ያለው ቢዝነስ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኮንትሮባንድ እና ሰውን አግቶ ብር አምጡ የሚሉ አካላት የሰላም እሳቤን ለእኩይ ዓላማ እያዋሉት ነው። ሕገ ወጥ የንግድ ተግባራት የሰላም ጠንቅ መሆናቸውን ገልጸው፤ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝና በእዚህም ለውጦች መምጣታቸውን አመልክተዋል።

አያይዘውም፤ መንግሥት ሰላም እንዲመጣ ከሚፈልግ ማንኛውም አካል ጋር በትብብር ለመሥራትና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ ነው። መንግሥት ሁሌም ለሰላም በሩ ክፍት እንደሆነም ነው። የንግዱ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ገንቢ ሚና በመወጣት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይገባዋል ነው ያሉት።

በዲፕሎማሲ መስክም የንግዱ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው የግንኙነት መስመሮች መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል። ለውጥ ለማምጣት መራር ወቅቶችን ማለፍ የግድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የጋራ ርዕይ ካለን እንወጣዋለን ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ገበያ ብር የሚገኝበት ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገር የሚገነባበት እና ለአንድ ሀገር ሕልውና ወሳኝ ሚና ያለው ነው ብለዋል። በእዚህ ረገድም የንግዱ ማህበረሰብ ካለው ሰፊ ተደራሽነት አንጻር በሀገር ግንባታ እና እድገት ላይ ጉልህ ድርሻ አለው ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የከረሙ እና አዲስ ፈተናዎች ያለባት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ የከረሙ ፈተናዎችን ፈትቶ የወደፊቱ ላይ መሥራት ካልተቻለ ትውልድ የተጠገነ ትናንት ያልተሠራ ነገን ስለሚረከብ መከራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አክለውም ያለፈውን መጠገንና የመጪውን የመሽቀዳደም ዘመን ሚዛን ጠብቆ መሄድን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባም ነው ያስረዱት። ኢትዮጵያውያን ከዕለት ጉዳዮቻችን ባለፈ በዋና ሀገራዊ ጉዳዮችና ፈተናዎቻችን ላይ የመምከር ባሕላችን መሻሻል እንደሚያስፈልገውም አንስተዋል። በነገ የሀገር እጣ ፈንታ ያለ መምከር ችግር በሁሉም ዘርፍ የሚታይ ጉዳይ ነው ብለዋል። የንግዱ ማህበረሰብ ባለው ሰፊ አቅም እና ተደራሽነት ያለፉ ችግሮችን የመፍታትና ነገን የመገንባት ሥራ ላይ ማህበረሰቡን የማስተማርና የማንቃት ሥራ ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ለውይይት ከመቀመጣቸው በፊት ለሦስት ቀናት ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል። በየደረጃው ካሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተደረገው ውይይት ችግሮችን በየደረጃው መፍታት እንዲቻል ዕድል የሚሰጥ ነው። በውይይቶቹ የንግዱ ዘርፍ ያሉበት ተግዳሮቶች ተነስተው የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ጋር ያካሔዱት ውይይት ከዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ከተካሔደው የቀጠለና ያልተፈቱ አንኳር ችግሮች ላይ በስፋት ውይይቶች የተካሔዱበት ሆኗል።

በተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You